ባለቤትና ተሳቢ
መምህር በትረማርያም አበባው
ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ስሞች በዐሥሩ መራሕያን እንዴት እንደሚዘርዘሩ ዓይተን ነበር፡፡ በዚህም ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ‹‹ባለቤትና ተሳቢ›› በሚል ርእስ እናስተምራችኋለን፡፡ መልካም ትምህርት ይሁንላችሁ!
መልመጃ
የሚከተሉትን ስሞች በዐሥሩ መራሕያን ዘርዝሩ
፩) በካዕብ- ተክሉ (የበግ አውራ)
፪) በካዕብ- ሰድሉ (ሚዛን)
፫) በሣልስ- አካሂ (ጥገት ላም፤ አራስ ላም)
፬) በራብዕ- ሥጋ
፭.በኃምስ- ጽጌ
፮. በሳብዕ- መሰንቆ
ከታች የተጠቀሱትን አፈንጋጭ ቃላት በዐሥሩ መራሕያን ዐርቡ! (እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ቃላት ከላይ በመጣንባቸው የርባታ ሥርዓት (የሰዋሰው ሕግ) መሠረት የሚረቡ አይደሉም፡፡ ስለሆን በጥንቃቄ ለማርባት ሞክሩ!
፩) አብ
፪) አፍ
፫) እድ
መልሾች
፩) በካብዕ ተክሉ- የበግ አውራ
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | ተክሉየ | በጌ |
፪ | ንሕነ | ተክሉነ | በጋችን |
፫ | አንተ | ተክሉከ | በግህ |
፬ | አንትሙ | ተክሉክሙ | በጋችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | ተክሉኪ | በግሽ |
፮ | አንትን | ተክሉክን | በጋችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ተክሉሁ | በጉ |
፰ | ውእቶሙ | ተክሉሆሙ | በጋቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | ተክሉሃ | በጓ |
፲ | ውእቶን | ተክሉሆን | በጋቸው (ሴ) |
፪) በካብዕ ሰድሉ- ሚዛን)
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | ሰድሉየ | ሚዛኔ |
፪ | ንሕነ | ሰድሉነ | ሚዛናችን |
፫ | አንተ | ሰድሉከ | ሚዛንህ |
፬ | አንትሙ | ሰድሉክሙ | ሚዛናችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | ሰድሉኪ | ሚዛንሽ |
፮ | አንትን | ሰድሉክን | ሚዛናችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ሰድሉሁ | ሚዘኑ |
፰ | ውእቶሙ | ሰድሉሆሙ | ሚዛናቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | ሰድሉሃ | ሚዛኗ |
፲ | ውእቶን | ሰድሉክን | ሚዛናቸው (ሴ) |
፫) በሣልስ-አካሂ- (ጥገት ላም፤ አራስ ላም)
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | አካሂየ | ላሜ |
፪ | ንሕነ | አካሂነ | ላማችን |
፫ | አንተ | አካሂከ | ላምህ |
፬ | አንትሙ | አካሂክሙ | ላማችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | አካሂኪ | ላምሽ |
፮ | አንትን | አካሂክን | ላማችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | አካሂሁ | ላሙ |
፰ | ውእቶሙ | አካሂሆሙ | ላማቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | አካሂሃ | ላሟ |
፲ | ውእቶን | አካሂሆን | ላማቸው (ሴ) |
፬) በራብዕ (ሥጋ)
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | ሥጋየ | ሥጋዬ |
፪ | ንሕነ | ሥጋነ | ሥጋችን |
፫ | አንተ | ሥጋከ | ሥጋህ |
፬ | አንትሙ | ሥጋክሙ | ሥጋችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | ሥጋኪ | ሥጋሽ |
፮ | አንትን | ሥጋክን | ሥጋችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ሥጋሁ | ሥጋው |
፰ | ውእቶሙ | ሥጋሆሙ | ሥጋቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | ሥጋሃ | ሥጋዋ |
፲ | ውእቶን | ሥጋሆን | ሥጋቸው (ሴ) |
፭. በኃምስ- ጽጌ (አበባ)
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | ጽጌየ | አበባዬ |
፪ | ንሕነ | ጽጌነ | አበባችን |
፫ | አንተ | ጽጌከ | አበባህ |
፬ | አንትሙ | ጽጌክሙ | አበባችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | ጽጌኪ | አበባሽ |
፮ | አንትን | ጽጌክን | አበባችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ጽጌሁ | አበባው |
፰ | ውእቶሙ | ጽጌሆሙ | አበባቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | ጽጌሃ | አበባዋ |
፲ | ውእቶን | ጽጌሆን | አበባቸው (ሴ) |
፮. በሳብዕ- መሰንቆ– መሰንቆ
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | መሰንቆየ | መሰንቆዬ |
፪ | ንሕነ | መሰንቆነ | መሰንቆአችን |
፫ | አንተ | መሰንቆከ | መሰንቆህ |
፬ | አንትሙ | መሰንቆክሙ | መሰንቆአችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | መሰንቆኪ | መሰንቆሽ |
፮ | አንትን | መሰንቆክን | መሰንቆአችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | መሰንቆሁ | መሰንቆው |
፰ | ውእቶሙ | መሰንቆሆሙ | መሰንቆአችሁ (ወ) |
፱ | ይእቲ | መሰንቆሃ | መሰንቆዋ |
፲ | ውእቶን | መሰንቆሆን | መሰንቋቸው (ሴ) |
ከታች የተጠቀሱትን አፈንጋጭ ቃላት በዐሥሩ መራሕያን አርቡ! (እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ቃላት ከላይ በመጣንባቸው የርባታ ሥርዓት (የሰዋሰው ሕግ) መሠረት የሚረቡ አይደሉም፡፡ ስለሆን በጥንቃቄ ለማርባት ሞክሩ!
፩) አብ
፪) አፍ
፫) እድ
መልሾች
፩) አብ- አባት
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | አቡየ | አባቴ |
፪ | ንሕነ | አቡነ | አባታችን |
፫ | አንተ | አቡከ | አባትህ |
፬ | አንትሙ | አቡክሙ | አባታችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | አቡኪ | አባትሽ |
፮ | አንትን | አቡክን | አባታችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | አቡሁ | አባቱ |
፰ | ውእቶሙ | አቡሆሙ | አባታቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | አቡሃ | አባቷ |
፲ | ውእቶን | አቡሆን | አባታቸው (ሴ) |
፪) አፍ- አፍ
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | አፉየ | አፌ |
፪ | ንሕነ | አፉነ | አፋችን |
፫ | አንተ | አፉከ | አፍህ |
፬ | አንትሙ | አፉክሙ | አፋችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | አፉኪ | አፍሽ |
፮ | አንትን | አፉክን | አፋችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | አፉሁ | አፉ |
፰ | ውእቶሙ | አፉሆሙ | አፋቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | አፉሃ | አፏ |
፲ | ውእቶን | አፉሆን | አፋቸው (ሴ) |
፫) እድ-እጅ
ተ.ቁ | መራሒ | ግእዝ | አማርኛ |
፩ | አነ | እዴየ | እጄ |
፪ | ንሕነ | እዴነ | እጃችን |
፫ | አንተ | እዴከ | እጅህ |
፬ | አንትሙ | እዴክሙ | እጃችሁ (ወ) |
፭ | አንቲ | እዴኪ | እጅሽ |
፮ | አንትን | እዴክን | እጃችሁ (ሴ) |
፯ | ውእቱ | እዴሁ | እጁ |
፰ | ውእቶሙ | እዴሆሙ | እጃቸው (ወ) |
፱ | ይእቲ | እዴሃ | እጇ |
፲ | ውእቶን | እዴሆን | እጃቸው (ሴ) |
ባለቤትና ተሳቢ
በግእዝ ቋንቋ አንድ ቃል ባለቤት ሲሆንና ተሳቢ ሲሆን የተለያየ ቅርጽ ይኖረዋል። ለምሳሌ ‹‹ሀገር›› የሚለው ቃል በዓረፍተ ነገር ውስጥ በባለቤትነት ሲያገለግል ‹‹ሀገር›› የሚል ሲሆን በተሳቢነት ሲያገለግል ግን ‹‹ሀገረ›› ይላል። አንድ ቃል ተሳቢ ሲሆን ሲተረጎም ‹ን› ፊደልን ያመጣል። ለምሳሌ ‹‹እግዚአብሔር ፈጠረ ሰማየ ብንል›› ሲተረጎም ‹‹እግዚአብሔር ሰማይን ፈጠረ›› ማለት ነው። ‹‹ሰማይ›› የሚለው ቃል ተሳቢ ሲሆን ‹‹ሰማየ›› ማለት ልብ ማድረግ ነው። ‹‹ሰማይ ተፈጥረ በእግዚአብሔር›› ብንል ግን ‹‹ሰማይ በእግዚአብሔር ተፈጠረ›› ማለት ስለሆነ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ‹‹ሰማይ›› ደግሞ ባለበት ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ አንድን ቃል ተሳቢ ለማድረግ ስንፈልግ የራሱ የሆኑ ሕጎች አሉ፤ እነርሱን እንመልከት፡፡
አንደኛ አካሄድ
መድረሻ ቀለማቸው ‹‹ሳድስ›› የሆኑ ቃላት ተሳቢ በሚሆኑበት ጊዜ መድረሻ ቀለሙ ወደ ‹‹ግእዝ›› ይለወጣል። ለምሳሌ ‹‹መንግሥት›› የሚለው ቃል ተሳቢ ሲሆን ‹‹መንግሥተ›› ይሆናል ማለት ነው። ሳድስ (‹ት›) ወደ ግእዝ (‹ተ›) መለወጡን አስተውሉ!
ተጨማሪ ምሳሌዎች፦
ባለቤት ተሳቢ
ፍቅር ፍቅረ
ምድር ምድረ
ኅብስት ኅብስተ
ሕይወት ሕይወተ
ለምሳሌ ‹‹ሕይወትን አገኘን›› በሚለው ቃል ውስጥ ‹‹ሕይወት›› የሚለው ቃል ‹ን› ን ተሳቢ ስላመጣ ወደ ግእዝ ሲተረጎም ‹‹ሕይወተ ረከብነ›› ይሆናል። ‹‹ጸጋ ነሣእነ ወሕይወተ ረከብነ›› እንዲል።
ሁለተኛ አካሄድ
መድረሻ ቀለማቸው ‹‹ካዕብ›› የሆኑ ቃላት ተሳቢ በሚሆኑበት ግእዝ መድረሻ ቀለማቸውን ወደ ‹‹ሳብዕ›› ይቀይራሉ። ለምሳሌ ‹‹ቤቱ ያምራል›› ስንል እና ‹‹ቤቱን አሳመረ›› ብንል ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ‹‹ቤቱ›› የሚለው ቃል በባለቤትነት ሲያገለግል በሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ያለው ‹‹ቤቱን›› ያለው ቃል ግን ተሳቢ ነው። በግእዝ ሲተረጎም ‹‹ቤቱ ያምራል›› ያለው ቃል ‹‹ቤቱ ይሤኒ›› እንላለን። ‹‹ቤቱን አሳመረ›› የሚለው ቃል ደግሞ ‹‹አሠነየ ቤቶ›› ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ካዕብ ‹ቱ› ወደ ሳብዕ ‹ቶ› እንደተለወጠ አስተውሉ።
ተጨማሪ ምሳሌዎች፦
ባለቤት ተሳቢ
መንግሥቱ መንግሥቶ
ሀገሩ ሀገሮ
ደሙ ደሞ
ፍቅሩ ፍቅሮ
መንግሥቱን ሰጠን የሚለውን ዓረፍተ ነገር ወደ ግእዝ ለመለወጥ ‹‹መንግሥቶ አወፈየነ›› እንላለን።
አስተውሉ! ‹‹መንግሥቶ›› ብሎ መድረሻ ቀለሙን ‹‹ሳብዕ›› ያደረገው ተሳቢ ስለሆነ ነው። ‹‹መንግሥቱ›› የሚለው በባለቤትነት ሲያገለግም ለምሳሌ ‹‹መንግሥቱ ዘለዓለም ወምኵናኑኒ ለትውልደ ትውልድ›› እንላለን።
ሦስተኛ አካሄድ
መድረሻ ቀለማቸው ‹‹ሣልስ›› የሆኑ ቃላት ተሳቢ ሲሆኑ መድረሻ ቀለማቸውን ወደ ‹‹ኃምስ›› ይለውጣሉ። ለምሳሌ ‹‹ሌባን አታቅርብ›› የሚለውን አማርኛ ወደ ግእዝ ለመተርጎም ብንፈልግ ‹‹ሌባን›› የሚለው ቃል ተሳቢ ነው። በግእዝ ሌባ ‹‹ሰራቂ›› ነው። ይህ ደግሞ ተሳቢ ሲሆን ‹‹ሰራቄ›› ይላል። ስለዚህ ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ ‹‹ኢታቅርብ ሰራቄ›› ይሆናል።
ተጨማሪ ምሳሌዎች፦
ባለቤት ተሳቢ
ጸሓፊ ጸሓፌ
ሠዓሊ ሠዓሌ
ቀታሊ ቀታሌ
ገባሪ ገባሬ
አራተኛ አካሄድ
መድረሻ ቀለማቸው ‹‹ራብዕ፣ ኃምስ፣ እና ሳብዕ›› የሆኑ ቃላት ተሳቢ ሲሆኑ ምንም ዓይነት የፊደል ለውጥ አያመጡም። ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ጽጌ›› የሚለው ቃል መድረሻ ቀለሙ ‹ጌ› ኃምስ ስለሆነ ተሳቢ ሲሆን ያው ራሱ ‹‹ጽጌ›› ይላል እንጂ ምንም ለውጥ አያመጣም ማለታችን ነው። በምሳሌ ለማየት ያህል ‹‹ንብ አበባን ትወዳለች›› ብንልና ‹‹አበባ በንብ ይወደዳል›› ብንል ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ‹‹አበባ›› ተሳቢ ሲሆን ከሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ደግሞ ‹‹አበባ›› ባለቤት ነው። ወደ ግእዝ ቋንቋ በምንተረጉምበት ጊዜ የመጀመሪያው ‹‹ንህብ ታፈቅር ጽጌ›› ይላል። ሁለተኛው ‹‹ጽጌ ይትፈቀር በንህብ›› ይላል። በሁለቱም ላይ ‹‹ጽጌ›› ተመሳሳይ ነው። በአማርኛ ትርጒም ግን ይለያል ማለት ነው።
ተጨማሪ ምሳሌዎች፦
ባለቤት ተሳቢ
መሰንቆ መሰንቆ
ከበሮ ከበሮ
እንዚራ እንዚራ
ትሕትና ትሕትና
ራማ ራማ
ቅዳሴ ቅዳሴ
ዝማሬ ዝማሬ
አምስተኛ አካሄድ
ስሞች ተሳቢ በሚሆኑበት ጊዜ በመድረሻ ፊደላቸው ለወንዶች ግእዙ ‹ሀ› ን ለሴቶች ራብዑ ‹ሃ› ን ያመጣሉ። ይህም ማለት ለምሳሌ አዳም ሔዋንን ወደደ ብንል ‹‹አዳም›› ባለቤት፣ ‹‹ሔዋን›› ተሳቢ፣ ‹‹ወደደ›› ደግሞ ማሠሪያ አንቀጹ ነው። ይህ ወደ ግእዝ ሲተረጎም ‹‹አዳም አፍቀረ ሔዋንሃ›› ነው። በተገላቢጦሽ ‹‹ሔዋን አዳምን ወደደች›› የሚለው ወደ ግእዝ ሲተረጎም ደግሞ ‹‹ሔዋን አፍቀረት አዳምሀ›› ይሆናል ማለት ነው።
ተጨማሪ ምሳሌ፦
ባለቤት ተሳቢ
ኢየሱስ ኢየሱስሀ
ኤርምያስ ኤርምያስሀ
ማርያም ማርያምሃ
ኤልሳቤጥ ኤልሳቤጥሃ
ተጨማሪ ለምሳሌ፡- ‹‹እምኵሉ ዕለት ሰንበተ አክበረ። ወእምኵሎን አንስት ማርያምሃ አፍቀረ›› ብንል ‹‹ከዕለት ሁሉ ሰንበትን አከበረ። ከሴቶችም ሁሉ ማርያምን ወደደ›› ማለት ነው።
ስድስተኛ አካሄድ
ተናባቢ ቃላት ባለቤት ሲሆኑ እና ተሳቢ ሲሆኑ ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ‹‹ተናባቢ ቃላት›› የሚባሉት ሁለት የግእዝ ቃላት አንድ ላይ ተጣምረው በአንድ ትንፋሽ ሲነበቡ ነው። ለምሳሌ ‹‹ቤተ መንግሥት›› የሚለው ቃል ቤት እና መንግሥት ከሚሉት ቃላት የወጣ ‹‹ተናባቢ ቃል›› ነው። ሁለት ቃላት በአንድ ላይ ሲጣመሩ የራሱ የሆነ ሰዋስዋዊ ሕግ አለ ይኸውም ሳድሱ ወደ ግእዝ፣ ሣልሱ ወደ ኃምስ ይለወጣል። ራብዕ፣ ኃምስ እና ሳብዕ ሲናበቡ አይለወጡም። ለምሳሌ ‹‹መንግሥት›› እና ‹‹ሰማያት›› የሚሉ ቃላት ሲናበቡ ‹‹መንግሥተ ሰማያት›› ይሆናል።
አስተውሉ! ‹‹መንግሥት›› ከሚለው ቃል የመድረሻ ፊደሉ ሳድሱ ‹ት› ወደ ግእዝ ‹ተ› ተቀይሯል። ሌላው ‹‹መጋቢ›› የሚለው ቃል እና ‹‹ሐዲስ›› የሚለው ቃል ሲናበብ ‹‹መጋቤ ሐዲስ›› ነው። አስተውሉ! ሣልሱ ‹ቢ› ወደ ኃምስ ‹ቤ› ተቀይሯል። ውዳሴ እና ማርያም የሚሉ ሁለት ቃላት ሲናበቡ ውዳሴ ማርያም ይላል ‹ሴ› ኃምስ ስለሆነ አልተለወጠም። መሰንቆ እና ዳዊት ሲናበቡ ‹‹መሰንቆ ዳዊት›› ይላል። ‹ቆ› ሳብዕ ስለሆነ አልተለወጠም። ትሕትና እና ማርያም የሚሉ ሁለት ቃላት ሲናበቡ ‹‹ትሕትና ማርያም›› ይላም። ‹ና› ራብዕ ስለሆነ አልተለወጠም።
ተጨማሪ ምሳሌዎች፡-
ቃል ፩ ቃል ፪ ሲናበብ
ሊቅ ሊቃውንት ሊቀ ሊቃውንት
ማይ ዮርዳኖስ ማየ ዮርዳኖስ
መጋቢ ብሉይ መጋቤ ብሉይ
ፈጣሪ ሰማያት ፈጣሬ ሰማያት
ዝማሬ መላእክት ዝማሬ መላእክት
እንዚራ ስብሐት እንዚራ ስብሐት
ከበሮ ማኅሌት ከበሮ ማኅሌት
እንግዲህ ተናባቢ ቃላት ተሳቢ ሲሆኑ ምንም የሚለወጥ ፊደል የለም። ለምሳሌ ‹‹ሊቀ ሊቃውንትን አከብራለሁ›› ስንል እና ‹‹ሊቀ ሊቃውንት መጣ›› ብንል። ከመጀመሪያው ያለው ሊቀሊቃውንት ‹‹ተሳቢ›› ከሁለተኛው ያለው ‹‹ባለቤት›› ነው። ሁለቱም ወደ ግእዝ በሚተረጎሙበት ጊዜ ‹‹ሊቀ ሊቃውንት›› የሚለው ቃል ላይ የሚለወጥ ቃል የለም። ይኸውም ‹‹አከብር ሊቀ ሊቃውንት፣ ሊቀ ሊቃውንት መጽአ›› ይላል ማለት ነው።
ሰባተኛ አካሄድ
የስም ዝርዝር በመራሕያን ሲዘረዘሩ እና ተሳቢ ሲሆኑ ሁለት መንገድ አለ። ሁለቱንም ዐይተን የዛሬ ትምህርታችንን እንጨርስ።
ተ.ቁ | መራሒ | ባለቤት | ተሳቢ |
፩ | አነ | ቤትየ | ቤትየ |
፪ | ንሕነ | ቤትነ | ቤተነ |
፫ | አንተ | ቤትከ | ቤተከ |
፬ | አንትሙ | ቤትክሙ | ቤተክሙ (ወ) |
፭ | አንቲ | ቤትኪ | ቤተኪ |
፮ | አንትን | ቤትክን | ቤተክን (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ቤቱ | ቤቶ |
፰ | ውእቶሙ | ቤቶሙ | ቤቶሙ (ወ) |
፱ | ይእቲ | ቤታ | ቤታ |
፲ | ውእቶን | ቤቶን | ቤቶን (ሴ) |
በሳድስ የሚጨርሱ ቃላት ይህንን መስለው ይሄዳሉ። ከሳድስ ውጭ ያሉ ቃላት ግን ባለቤታቸው እና ተሳቢያቸው ተመሳሳይ ነው።
ስምንተኛ አካሄድ
አፈንጋጭ አካሄድ፡- አፉሁ፣ አቡሁ፣ሥጋሁ የሚሉት ቃላት ሲሳቡ አፉሁ፣ አቡሁ፣ ሥጋሁ እንጂ አፉሆ፣ አቡሆና ሥጋሆ አይልም።
ተ.ቁ | መራሒ | ባለቤት | ተሳቢ |
፩ | አነ | ሥጋየ | ሥጋየ |
፪ | ንሕነ | ሥጋነ | ሥጋነ |
፫ | አንተ | ሥጋከ | ሥጋከ |
፬ | አንትሙ | ሥጋክሙ | ሥጋክሙ (ወ) |
፭ | አንቲ | ሥጋኪ | ሥጋኪ |
፮ | አንትን | ሥጋክን | ሥጋክን (ሴ) |
፯ | ውእቱ | ሥጋሁ | ሥጋሁ |
፰ | ውእቶሙ | ሥጋሆሙ | ሥጋሆሙ (ወ) |
፱ | ይእቲ | ሥጋሃ | ሥጋሃ |
፲ | ውእቶን | ሥጋሆን | ሥጋሆን (ሴ) |
ሐዋርያትን የመሳሰሉ ብዛትነት ያላቸው ቃላት ሲዘረዘሩም ተሳቢያቸው በሦስተኛ መደቦች አይለወጥም። ይኸውም ሐዋርያቲሁ፣ ሐዋርያቲሃ፣ ሐዋርያቲሆሙ፣ ሐዋርያቲሆን ይላል። በአንደኛና በሁለተኛ መደቦች ሲሳቡ ሐዋርያቲከ፣ ሐዋርያቲክሙ፣ ሐዋርያትኪ፣ ሐዋርያቲክን፣ ሐዋርያትየ፣ ሐዋርያቲነ ይላል ማለት ነው። ይኸውም ‹ቲ› የሚለው ሣልስ ፊደል ለባለቤትም ለተሳቢም (ለገቢር ተገብሮ) ይሆናልና።
መልመጃ
፩) ለሚከተሉት ቃላት ተሳቢያቸውን ጻፍ።
ሀ) ማርታ
ለ) መንበር
ሐ) ትንሳኤ
መ) ዮሐንስ
ሠ) ቃለ ሕይወት
፪) የሚከተሉትን ሁለት ሁለት ቃላት ተናባቢ አድርግ፦
ሀ) አክሊል እና ጽጌ
ለ) ክብር እና ቅዱሳን
ሐ) ፍካሬ እና ኢየሱስ
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።