በፊትህ ናት
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
በኀምሳኛው ዕለት መንፈስ ቅዱስ ሲያድርባቸው
በ፸፪ የተለያየ ዓይነት ቋንቋቸው
ሲናገሩ ተገረሙ አሕዝቡ ሰምተው
በእግዚአብሔር ሥራ እጅግ ተደንቀው
የወንጌሉን ቃል ሲረዱ ተነክቶ ልባቸው
ሦስት ሺህ ነፍሳትም ተጠመቁ አምነው
እምነት ተራራን ያፈልሳል ባሕርን ይከፍላል
በእሳቱ መካከል በሰይፍ ስለት ላይ መንገድ ይመራሀል
ይኸው የአንተ አባት ሃይማኖት ያጸናው
እየነደደ እንደ ጧፍ መብራት ሆኖ ለከተማው
መስቀል ተሸክሞ በነገሥታት መካከል ማንንም ሳይፈራ
በደብረ ይድራስ ላይ እንደ እህል ተፈጭቶ በነፋስ ተዘራ
በዱር በገደሉ በበረሃ ወድቆ
ንባቡን ተርጒሞ ምሥጢርን አራቆ
ድምፀ አራዊቱን የሌሊቱን ግርማ በጽናት ታግሦ
ሀገርን ጠበቀ ትውልድን አቀና አፈር ጤዛ ልሶ
ልጄ ልጅ ሆኜ የአባቴን ስም እንዳስጠራሁ
እኔም በተራዬ አንተን ወልጃለሁ
እስራኤላዊው ናቡቴ ያ ሰማርያዊው
የወይኑ ፍሬ ናት የማንነቱ መለያው
ቅጥር ቀጥሮ ጠብቆ ከተኩላ
ይጠብቃት ነበር ተግቶ እንዳትበላ
አክአብ ድንበርተኛው በወይኑ ጐምጅቶ
ነቃቅሎ ሊጥላት በጐመን ተክቶ
ያችን መልካም እርሻ ባድማ ሊያደርጋት
ሊገዛት ወደደ በጥፍ ሊለውጣት
ሕይወቱ ናትና ገንዘብ የማይገዛት
አለወጥም አለ የአባቶቹን ርስት
ናቡቴ ልጅ ባይኖረው ርስቱን የሚያወርሳት
ስለ መልካም እርሻው ደሙን አፈሰሳት
ምስኪኑ ናቡቴ ደሙ ፈሷልና
እኔ ግን . . . አልደማም! አልቆስልም!
አንተን ወልጃለሁና
ዓይኔ ዓይኔን ዓይቶት እርጅና ታደሰ
ያ! የጥንቱ ልጅነት ባንተ ተመለሰ
ቢሆንም መቃብሬ የተማሰ ልጤ የተራሰ
አጥንቶቼ ጸንተው ጒልበቴ በርትቶ
የሃይማኖት ፍሬ በአንተ ውስጥ ዓይኔ ዓይቶ
ምግባር ከሃይማኖት በአንተ ላይ ዘርቼ
በቀንና ሌሊት ዘመኔን ተግቼ
ያሳደኩት ተክል የተንዥረገገው
ከፍሬው ላጣጥም ቆርጨ ብቀምሰው
ሆምጣጤ በዝቶበት ምላሴን መረረው
ዘሩ አመንዝሮ ዲቃላ ካፈራ
ለአክአብ ከሸጠው የውርሱን አደራ
ልጁም ልጅ አልሆነ ወይኑም አላፈራ
ዔሳው ብኩርናውን ንቆ ክብሩን ካቃለለው
ያዕቆብ ይነሣል . . . የምድር በረከቱን . . . በሰማይ ሊወርሰው
በመከራ ወራት መስቀል የሚሸከም እግዚአብሔር ሰው አለው
ልጄ አንተ ልጅ ከሆንከኝ ዔሳውን ተክተህ
ብኵርና ይሄ ነው ማተቤን ላውርስህ
በዓለም አሸንክታብ ጉልበትህ ካልዛለ
በጊዜ ሰንሰለት ልብህ ካልታሰረ
በምድር ተድላ ደስታ ዓይንህ ካልባከነ
የእውነት ልጅ ከሆንክ በተወለድክባት
የናቡቴ እርሻ ያንተም ርስትህ ናት
ከትውልድህ ጋራ በልተህ ጠጥተሃት
ዘመንህን ሁሉ እያገለገልካት
ደግሞም በሰማያት የምትከብርባት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይኸው በፊትህ ናት
መንግሥተ ሰማያት ይኸው በፊትህ ናት