በጸሎተ ሐሙስ የተፈጸሙ ተግባራት
በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና
የሊቃውንት ጉባኤ አባል
መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በዕለተ ሐሙስ ከተፈጸሙ ዐበይት ተግባራት አንዱ መድኃኒታችን ክርስቶስ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህ ደሜ ነው፤›› ብሎ አማናዊ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፰)፡፡ እንደዚሁም ይህ ዕለት ሰፊ ጸሎት የተደረገበት የጸሎት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ሐሙስ ዕለት ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም ወርዶ መሬቱን ጭቃ እስኪያደርገው ድረስ መላልሶ ስለ ጸለየ ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን የጸለየበትን ቦታም ወንጌላውያኑ በተለያየ ስያሜ ጠርተውታል፤ ማቴዎስና ማርቆስ – ‹ዐፀደ ወይን›፣ ‹ጌቴሴማኒ›፤ ሉቃስ – ‹ደብረ ዘይት›፤ ዮሐንስ – ‹ማዕዶተ ቄድሮስ›፣ ‹ፈለገ አርዝ›፣ ‹ዐፀደ ሐምል› በማለት ሰይመውታል (ማቴ.፳፮፥፴፮፤ ማር.፲፬፥፴፪፤ ሉቃ. ፳፩፥፴፯፤ ፳፪፥፴፱፤ ዮሐ. ፲፰፥፩)፡፡
በተጨማሪም ይህ ዕለት (ሐሙስ) ያለ እርሱ ፈቃድ ሊይዙት እንደማይችሉ ለማስረዳት ጌታችን በመለኮታዊ ኃይሉ እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ካደረጋቸው በኋላ በይቅርታው ብዛት መልሶ በማስነሣት በፈቃዱ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነው (ዮሐ. ፲፰፥፭-፰)፡፡ በዕለተ ሐሙስ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ የኾነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕገ ኦሪትን እየፈጸመ አድጓልና በኦሪት ሥርዓት የሚፈጸመውን የመጨረሻውን በግዐ ፋሲካ (የፋሲካ በግ) ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መመገቡ አንደኛው ነው፡፡ ይሁዳ እንደሚያስይዘው ለሐዋርያት በምልክት ማስረዳቱ ሁለተኛው ሲኾን (ዮሐ. ፲፫፥፳፩)፤ እንደ አገልጋይ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ደግሞ ሦስተኛው ነው፡፡
ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ምሥጢር
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ ‹‹እናንተ መምህራችን፣ ጌታችን ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፡፡ እኔ ጌታችሁ መምህራችሁ ስኾን ዝቅ ብዬ እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም ዝቅ ብላችሁ የወንድሞቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል፡፡ ምሳሌ ኾኛችኋለሁና፤›› በማለት የትሕትና ሥርዓት ሠርቶ እነርሱም በሥራ እንዲገልጡት አዝዞአቸዋል (ዮሐ. ፲፫፥፲፭)፡፡ በግእዝ የተጻፈ አንድ ትርጓሜ ወንጌል ‹‹እዘርእ ፍቅረ ወትሕትና ውስተ አልባቢክሙ፤ ፍቅርንና ትሕትናን በልባችሁ እዘራለሁ፤›› እንዳላቸው ይናገራል፡፡
ሠለስቱ ምእትም በአንቀጸ መነኮሳት ‹‹ወኢትትሐከይ ኀፂበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትኀሠሥዎሙ ለእለ ያጸርዕዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳተ እስመ እግዚአብሔር ኀፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ ወአዘዞሙ ከማሁ ይግበሩ፤ ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፡፡ ይህችን ሥራ ቸል የሚሏትን ስለዚህች ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና፡፡ ኤጲስቆጶሳትም ቢኾኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ፳፥፳፱፤ ፩ኛ ጢሞ. ፭፥፱-፲)፡፡
የጌታችንን ትሕትና በተናገረበት ክፍል፣ ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ‹‹የማይታዩ ረቂቃን መላእክቱ አደነቁ፤ ከልዑል ዙፋኑ ወርዶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያገለግል ባዩት ጊዜ አገልጋዮቹ መላእክት ደነገጡ፡፡ ትሕትና ወዳለበት ፍቅር የአሕዛብ እግረ ልቡናን ያቀና ዘንድ ግሩም እሳት በትሕትና መገለጡን ባዩ ጊዜ ብርሃናት ደነገጡ፤›› ይላል (ሃይማኖተ አበው ፹፰፥፰)፡፡ ፊልክስዩስም ‹‹ወኅፅበተ ፋሲካ ትትሜሰል በምሥጢረ ትሕትና ፍጽምት፤ የፋሲካ ኅፅበት ፍጹም በኾነ የትሕትና ሥራ ትመሰላለች፤›› ብሏል (መጽሐፈ መነኮሳት)፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹… ጌታችን ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በደረሰ ጊዜ ጴጥሮስም ‹አቤቱ እግሬን የምታጥበኝ አንተ ነህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶ ‹እኔ እግርህን ከላጠብሁህ አንተም ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም› አለው፡፡ ይህም ማለት ‹እኔ በአገልጋይ ምሳሌ እግርህን ካላጠብሁ አንተም ከበታችህ ላሉ ራስህን ዝቅ ማድረግ አትችልም፡፡ ራስህን ዝቅ ካላደረግህም የእነርሱ አለቃ መኾን አትችልም፡፡ በሰማያት ባለው መንግሥቴስ ከእኔ ጋር እንዴት አንድ ለመኾን ትችላለህ?››› በማለት ራሱ ትሑት ኾኖ ጴጥሮስን ትሑት ይኾን ዘንድ አጥብቆ እንደ መከረው ይናገራል፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት መነሻነት ዘወትር በግልጥ ሲከናወን የኖረውን፤ አሁንም ባለ ማቋረጥ እየተከናወነ የሚገኘውን፤ ለወደፊትም የሚከናወነውን ቅዱስ የኾነውን የኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሥርዓት ወደ ጐድን በመተው ግምታዊ ልማድን እየተከተለ ‹‹የሐዋርያት ጥምቀት በኅፅበተ እግር ነው፤ እኛ የዳነው በኅፅበተ እግር ነው፤›› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስታጠምቅም፣ ቅብዐ ቅዱስ ስትቀባም ከራስ ጀምራ ነው፡፡ በመጨረሻም በራስ ላይ እፍ ብላ መንፈስ ቅዱስን በማሳደር ነው እንጂ እግርን በማጠብ አጥምቃ አታውቅም፡፡
ይኸውም ከሐዋርያት የተገኘ፤ ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ ትውፊታዊና ቅዱስ ሥርዓት ነው እንጂ አሁን የተፈጠረ አዲስ ባህል አይደለም፡፡ ስለዚህም የጸሎተ ሐሙስ ኅፅበተ እግር ጥምቀት ሳይኾን ፍጹም ትሕትናን ሠርቶ ለማሠራት ጌታችን የፈጸመው ተግባር ነው፡፡ ይህንም ያለ ጥርጥር ልንቀበለውና ልንተገብረው ይገባል፡፡ ከዚህ ሌላ የሐዋርያት ጥምቀት አንዳንዶቹ ‹‹ተከተሉኝ›› ሲላቸው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ዅሉ አባባል ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት ያልተደገፈ ግምታዊ አሳብ ነው እንጂ፡፡
በዕለተ ሐሙስ በተከናወነው ኅፅበተ እግር ሐዋርያት እንደ ተጠመቁ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ኅፅበት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወሰንና አቻ የሌለው ፍጹም ትሕትናውን የገለጠበት ምሥጢር እንጂ ጥምቀት እንዳልኾነ ብዙ መጻሕፍት ይስማማሉ፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ መጻሕፍት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ፍጹም ትሕትናውን ለመግለጥ እንደ ኾነ በማያሻማ ኹኔታ አረጋግጠዋል፡፡
ሐዋርያት በዚህ ጊዜ (በኅፅበተ እግር) ተጠመቁ የሚል ግን ማኅበረ ሐዋርያት ከባስልዮስ መጽሐፍ አገኘን ብለው ከጠቀሷት አንዲቷ ጥቅስ በስተቀር ሌላ አልተገኘም፡፡ ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ቁም ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖት አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፤›› (ኤፌ. ፬፥፭) ባለው መሠረት ሠለስቱ ምእት በጉባኤ ኒቅያ በተናገሩት የሃይማኖት ጸሎት ‹‹ኀጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› (ሃይማኖተ አበው ፲፯፥፲፪) ከማለታቸውም ባሻገር ጥምቀት እንዳይደገም፣ እንዳይከለስ በፍትሕ መንፈሳዊ ከልክለዋል፡፡
ኅፅበተ እግር በቤተ ክርስቲያን
በየዓመቱ የሕማማት ሐሙስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ ዘወትር በየቀኑ በየገዳማቱና ትምህርት ቤቶች ለሚስተናገዱ እንግዶች ዅሉ ኅፅበተ እግር ይከናወናል፡፡ ኅፅበት ጥምቀት ነው ከተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠለስቱ ምእትም ኅፅበተ እግሩ ባለማቋረጥ ዅልጊዜ ሲተገበር (ሲከናወን) ሰዎች ዅሉ በየጊዜው ይጠመቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሐዋርያትና ሠለስቱ ምእት ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲፈጸም ከወሰኑ በአንድ ምላስ ሁለት ምላስ ያሰኛል፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚጣረሱ ተቃራኒ ሥርዓቶችን ማራመድ አይቻልምና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋር ደግሞ የእግር መታጠብ ጥምቀት ከኾነ ጌታችን እግራቸውን አጥቦ ‹‹እንዲህ አድርጉ›› ብሎ አዞናልና አዲስ ተጠማቂዎችን አብሶም ሕፃናትን መላ አካላቸውን እያጠመቅን ለምን በቅዝቃዜ እናሰቃያቸዋለን? እግራቸውን ብቻ አጥበን ‹‹ተጠምቃችኋል›› እያልን አናሰናብታቸውም? እስኪ በማስተዋል እንመርምረው፡፡
መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ያከናወናቸው አምላካውያት ተአምራት እንዳይገለጡ ‹‹ይህን ለማንም እንዳትናገሩ፤›› እያለ አጥብቆ ይከለክል ነበር (ማቴ. ፰፥፬፤ ፱፥፴፤ ፲፮፥፳፤ ፲፯፥፲፱)፡፡ ይኸውም ገደቡ ካሣ እስከሚፈጸም እስከ ትንሣኤ ድረስ ኾኖ ከዚያ በኋላ ግን ተአምራቱ መነገር እንዳለበት ‹‹ወልደ እጓለ እመ ሕያው ክርስቶስ ከሙታን እስኪነሣ›› ብሎ ግልጽ አድርጎታል (ማቴ. ፲፯፥፲፱)፡፡ ይህንም ‹‹መከራን ከፊት አስቀምጦ፣ ደስታን፣ ክብርን መናገር ስለሚገባ ነው›› ብለው ሊቃውንቱ አትተውታል፡፡
በዚህ አንጻር ጌታችን እስከ መስቀል ሞት ድረስ ከፊቱ ከባድ መከራ ተደግሶለት እያለ ‹‹በኅፅበተ እግር ሐዋርያትን አጠመቀ፤ ልጅነትን ሰጠ›› ማለት አያስሔድም፡፡ ምክንያቱም አንድ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የሚያውጀው፤ ሹመት፣ ሽልማትን መስጠት የሚጀምረው ጠላቱን ድል አድርጎ መንግሥቱን ካደላደለ በኋላ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓለሙን ያዳነውና ልጅነትን የሰጠው ዲያብሎስን በመስቀል ድል ከነሣው በኋላ ነው እንጂ በኅፅበተ እግር አይደለም፡፡
ከኅፅበተ እግር በኋላ ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን ጌታችን እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? ዘወትር ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፡፡ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው፤›› (ሉቃ. ፳፪፥፶፪-፶፫)፡፡ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበበት እና በአትክልት ቦታ ከጸለየበት ከሐሙስ ማታ እስከ ዓርብ እኩለ ቀን ድረስ ለመግለጽ እጅግ የሚከብድና የሚያሰቅቅ ሥቃይና መከራን በፈቃዱ ተቀብሏል፡፡
ከዚህ አሰቃቂ መከራና ሞት በፊት ቅዱሳን ሐዋርያት ተጠመቁ፤ ልጅነትን አገኙ ማለት ከጋብቻ በፊት ልጅ መውለድ እንደ ማለት ከመኾኑም በላይ የዓለም ቤዛ የኾነውን የጌታችንን ሞት ከንቱ ዋጋ አልባ ማድረግ ነው፡፡ እንዴት ቢባል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለ በሙሉ ከሐዋርያት በተገኘ ልጅነት ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በፊት በተከናወነ ኅፅበተ እግር ተጠመቁ ከተባለ ሞቱ ምንም ሥራ አልሠራም ማለት ነውና፡፡ ወገኔ ሆይ! ከዚህ በላይ እንደ ተገለጠው የዳንኸውና ልጅነትን ያገኘኸው በክርስቶስ ሞትና ደም እንጂ በእግር መታጠብ እንዳልኾነ ልታስተውል ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡