‹‹በጒብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› (መክብብ ፲፪፥፩)
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሐምሌ ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በቅዱሳት መጻሕፍት ወጣትነት ጉብዝና አንዳንዴም ጉልምስና እየተባለ ይጠራል፡፡ የወጣትነት ዕድሜ ብያኔ እንደ የማኅበረሰቡና እንደ የሀገሩ ቢለያይም ሰው ሠርቶ ማግኘት፣ ወድቆ መነሣት፣ የሚችልበት ዕድሜው የጉብዝናው ዕድሜ ነው፡፡ ወጣትነት /ጉብዝና/ ከመነሻው አያሌ ባሕርያዊ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ለውጦች የሚከሠቱበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
በመሆኑም የሚመለከታቸውን አካላት የቤተ ክርስቲያን መምህራን፣ ወላጆች፣ የቀለም ትምህርት ቤት መምህራን፣ እንዲሁም ወጣቶችን ማዕከል አድርገው የተቋቋሙ የመንግሥት ተቋማት ወጣቶችን ከሥሩ በተገቢው መልኩ ካላስተማሩ የሚከሠተው ሰብአዊና ሀገራዊ ቀውስ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የሀገር ህልውናዋ የሚወሰነው ወጣቶች ላይ በሚሠራው ሥራ ነውና፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ፍሬያቸው በዋናነት የሚመዘነው ምን ያህል ወጣቶችን በአገልግሎት ምርታማና ውጤታማ እንደሚሆኑና በነፍሳቸውም ለእግዚአብሔር የሚገዙ እንዲሆኑ አድርገዋል? በሚለው ሚዛን ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገልጽ ቅዱስ ጴጥሮስን በግልገል የተመሰሉ ሕፃናትንና በበጎች የተመሰሉ አረጋውያንን አሠማራ ሲለው በጠቦት የተመሰሉ ወጣቶችን ግን ጠብቅ ብሎታል፡፡ (ዮሐ. ፳፩፥፲፮)
ወጣቶች መንገዳቸው ከአምላካቸው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የተስማማ ይሆን ዘንድ በማስተዋል ሊጓዙ ይገባቸዋል፡፡ በማስተዋል መጓዛችን ከሚገለጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን በኑሯችን ሁሉ ማሰብ ነው፡፡
እግዚአብሔርን ማሰብ – ከእግዚአብሔር ጋር መኖር
ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣህን አስብ›› ብሎ የተናገረው ቃል በወጣትነት ወራት ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንኖር የሚያሳስብ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኙ የተሰቀለው ወንበዴ ‹‹ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ብሎ እንደተማጸነው እናስተውል፡፡ ለዚህ የወንበዴው ጸሎት ጌታችን ‹‹እውነት እልሃለው፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› በማለት ‹‹አስበኝ›› ለሚለው ጸሎት ‹‹ከእኔ ጋር ትኖራለህ›› በማለት ከመለሰለት መልስ እግዚአብሔርን ማሰብ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፵፪)
ከእግዚአብሔር ጋር እንኖር ዘንድ የታዘዝን ክርስቲያን ወጣቶች ዛሬ ከማን ጋር እየኖርን ነው? ሐሳባችን፣ ንግግራችንና ተግባራችን የሚገልጸው ከእግዚአብሔር ጋር መኖራችንን ነው? እግዚአብሔርን የሚያስብ ወጣት አኗኗሩ እንደ ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በመፍራትና በኑሮው ውጣ ውረድ ሁሉ እግዚአብሔርን አለመዘንጋት ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የመልካምነትም ሁሉ መሠረት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ወጣት ዘወትር በማንኛውም ቦታና ሁኔታ አምላኩ ከእርሱ ጋር እንዳለ ስለሚያስብ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ብቻ ሳይሆን እንደ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በማሰብ ከኃጢአት ይሸሻል፡፡ ወጣቱ ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በማሰብ ፈጣሪውን ከእርሱ ጋር እንዲሆን አድርጎታልና ትጉህና ውጤታማ ሠራተኛ ሆነ፡፡ ዋዛ ፈዛዛ ሳቅ ስላቅ ከበዛበት፣ ፌዝና ተረብ ከነገሠበት ነገር ራሱን በማራቅ ከዋዛ ፈዛዛ ይልቅ በሥራ መትጋትና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ለታላቅነት እንደሚያበቃ በመረዳት ትኩረቱን ሥራው ላይ ያደርግ ነበር፡፡ በዚህም በደረሰበት ሥፍራ ሁሉ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርገው ነበር፡፡ ፍጻሜው የሚያምር ስኬት ላይ ለመድረስ መሠረቱ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ ዮሴፍ በተደላደለው መንገዱ ከጲጥፋራ ሚስት እግዚአብሔርንም እንዲያሳዝን ለመገፋፋት በዝሙት እንደተፈተነ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በዘፍጥረት መጽሐፍ ጽፎልናል፡፡ (ዘፍ. ፴፱፥፰-፱)
እግዚአብሔርን በጉብዝናው በማሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖር ስለነበረ ዮሴፍ እንቢ ለኃጢአት አለ፤ ‹‹እነሆ ጌታዬ (አለቃዬ) በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፡፡ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?›› እንዲል፤ (ዘፍ. ፴፱፥፰-፱)
ዛሬ የሰውን ሚስት የሚያባልጉ በሐሰትና በሚያሳስት ንግግር ወደ ዝሙት የሚወስዱ ይህንንም እኩይ ግብራቸውን እንደ ጀብድና ጀግንነት የሚቆጥሩ ወጣቶች መብዛታቸውን ስንመለከት የቅዱስ ዮሴፍ ታላቅነትና እግዚአብሔርን መፍራት እንደሚጎድላቸው እንረዳለን፡፡ ዮሴፍ ሕግ ባልተሰጠበትና ሰዎች በሕገ ልቡና በሚመሩበት በዚያ ዘመን የዝሙትን አስከፊነት መጽሐፍ ሳይጠቀስለት በትውፊት ከአባቶቹ ተምሮ ከዝሙት ሸሸ፡፡ ለራሱም፣ ለአለቃውም፣ ለፈጣሪውም የታመነ መሆኑን በተግባር አስመሠከረ፡፡ የዛሬ ወጣቶች ለምንሠራበት ተቋም፣ ለአለቃችን፣ ለጓደኛችን ታማኞች ነን? የአደራ ጥብቅነት ከሰማይ ርቀት ጋር ተነጻጽሮ በሚነገርበት ማኅበረሰብ መካከል አድገን ታማኞች መሆን አለመቻላችን ምክንያቱ ምን ይሆን? ዮሴፍ ዓለም በኃጢአት ስትፈትነው በወጥመዷ ላለመያዝ እግዚአብሔርን አስቧልና በሐሰት ወንጅለውና ወደ ወህኒ እንዲጣል አድርገው ለመከራ በዳረጉት ጊዜ እግዚአብሔርም እርሱን አሰበው፡፡ በወጣትነት ዘመን እግዚአብሔርን ማሰብ የጉልምስናና የሽምግልና ብሎም ከሞት በኋላ ለሚኖረውም ሕይወት ዋስትና በመሆኑ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ›› ብሎ አስተማረ፡፡ (መክ.፲፪፥፩)
በዓለም ላይ ያሉ ማናቸውንም ነገሮች ያለማቋረጥ ማሰብ አንዱ የሥነ ልቡና ሕመም መነሻ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ስለ ባለጠግነት ብቻ የሚያስብ ሰው ሐሳቡ ሳይሳካለት ቀርቶ በድኅነት ቢኖር ወይም ደግሞ ማግኘቱ ተሳክቶለት ዳግም ቢቸገር በሁለቱም ይጎዳል፡፡ የጤናን ነገር ሁሌ በማሰብ የሚኖር ሰው ሕመም በጎበኘው ጊዜ ይፍገመገማል፡፡ ደስታን ብቻ የሚያስብ ሰው ኃዘን በገጠመው ጊዜ ቆሞ መራመድ ያዳግተዋል፡፡ ማግኘትን ብቻ የሚያስብም ማጣትን አይቋቋምም፡፡ እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ ሲሔዱም ሲቀመጡም፣ሲበሉም ሲጠጡም፣ ሲሠሩም ሲያርፉም ማሰብ ግን ሕይወትም፣ ጤናም፣ የደስታም ምንጭ ነው፡፡
እግዚአብሔርን ማሰብ – መልካም ነገርን መናገር
ማሰብ ከመናገር ጋር የአንድ ሳንቲም ገጽታ ነው፤ ሰው የሚናገረው ያሰበውን ነውና፡፡ ማሰብና መናገር ያላቸውን አንድነት ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት ከተናገረው ኃይለ ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር›› በማለት የተናገረውን ቃል እናስተውል፡፡ ሰው በልቡናው ያስባል እንጂ አይናገርም፤ ሆኖም ግን በአንደበት የሚነገረው በልቡና የታሰበ ነውና በልቡም እውነትን የሚናገር ብሎ ተናገረ፡፡ (መዝ. ፲፬፥፩-፪)
በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን እንድናስብ የሚረዳን አንደበታችን ከክፉ ከልክለን ሽንገላንም ከእኛ አርቀን ሰዎችን የሚያጽናና የሚያረጋጋ መልካም ነገርንም ብቻ ስንናገር ነው፡፡ እግዚአብሔርን የማሰብ አንዱ መገለጫ መልካም ነገር መናገር ነው፡፡ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር መልካም ነው›› ብሎ እንደተናገረ ስለ እግዚአብሔር ቸርነት፣ ታላቅነትና መጋቢነት የሚናገር መልካም ነገር ተናገረ፡፡ (ናሆ. ፩፥፯)
እግዚአብሔር ስለሚወደውና ስለሚፈቅደው ነገር ብቻ መናገር እግዚአብሔርን ማሰብ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ሁሉ ስድብ፣ ትችት፣ ነቀፋ፣ ሐሜት፣ ሽንገላ፣ ተረብና የመሳሰሉት ሆነዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶዋል …. እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው የለም›› ብሎ እንደተናገረው የእኛም ነገር እንዲሁ ሆኗል፡፡ (መዝ. ፲፫፥፬-፮)
እግዚአብሔርን የሚያስብ ወጣት የሚናገረውን ያውቃል፡፡ አንደበቱም የተገራና በመልካም ነገር የተቀመመ ነው፡፡ ሰውን የሚያስደነግጥ፣ የከፋውን የሚያባብስ፣ በወገኖች መካከል ልዩነትን የሚያሰፋና ጠብ የሚጭር ነገር ከአንደበቱ አይወጣም፡፡ እየጮኸ፣ ጎረቤት እያወከ፣ ሰዎችን እያሳቀቀ፣ የሰዎችን ክብር እየነካ፣ በሌላው የአካል መጉደል እያሾፈ አይናገርም፡፡ ‹‹በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ›› እንደሚባለውም በአንደበቱ ምክንያት የማይገባውን እየተናገረ በራሱና በማኅበረሰቡም ሆነ በሀገሩ ላይ ጥፋትና መጠፋፋትን አያመጣም፡፡ የምንናገረውን ለማወቅ ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን እናስብ፡፡ እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን ስለተውነውም ሰዎች በድለውንም ይሁን ሳይበድሉን የስድብ ናዳ እናወርድባቸዋለን፡፡ በአንድ ሰው ስሕተት አባቱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ በመጣበት ነገድ፣ የተወለደበት መንደር ሳይቀረን በስድብ እናጥረገርጋቸዋለን፡፡ እግዚአብሔርን ማሰብ ስላቆምን የምንናገረው እያንዳንዱ ነገር ሰዎች ላይ ምን ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በሀገርም ላይ ምን ዓይነት ጥፋት ይዞ እንደሚመጣ ማስተዋል ተስኖናል፡፡ ጥቂት የማንባል ወጣቶች እግዚአብሔርን ማሰብ እንደሞት ስለምንቆጥረው የሞት ምክንያት የሆኑ አያሌ ነገሮች ከአጠገባችን ቆመዋል፡፡ ሽማግሎዎችን እንሳደባለን፤ አካል በጎደላቸው እንሳለቃለን፤ ችሎታ የጎደለውን እናሸማቅቃለን፤ ከደረስንበት ያልደረሰውን እናቃልላለን፡፡
እግዚአብሔርን ማሰብ- ከመከራ ሁሉ መዳኛ መንገድ ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› ብሎ የተናገረበትን ምክንያት ሲገልጥ የመጀመሪያ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ‹‹የጭንቀት ቀን ሳይመጣ›› የሚል ነው፡፡ በወጣትነት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚገጥሙንን የጭንቀት ፈተናዎች የምንወጣው በተለያዩ አደንዛዥ ዕፅ ሱሶች ውስጥ በመደበቅ፣ አልኮል መጠጦችን በማብዛት፣ መፍትሔ ብለን የምንወስዳቸው ሌሎች ችግር አምጪ አማራጮች ውስጥ በመግባትና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን በመከወን መሆን የለበትም፡፡ የጭንቀት መድኃኒቱ እግዚአብሔርን ማሰብና እንደ ፈቃዱም መመላለስ ነው፡፡ የወጣትነት ዕድሜ ካለፈ በኋላም ለሚገጥመን የሽምግልና ጭንቀት መድኃኒቱ የወጣትነት ዕድሜን አካሄድ ማስተካከል እንደሆነ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችም ሳይቀሩ ይመክራሉ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው›› ብሎ እንዳስተማረውም በኋለኛው ዘመን የሚኖረንን መዳረሻ የሠመረና ትርጉም ያለው የሚያደርገው በወጣትነት ዘመናችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖረን የምናደርገው መልካም አኗኗር ነው፡፡ በወጣትነት ያልዘሩትን በሽምግልና አያጭዱትም፡፡ በጉብዝና ያላረሙትን በዕርግና አያስተካክሉትም፡፡ (መዝ. ፻፲፰፥፱)
ጠቢቡ ሰሎሞን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን የማሰብ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ሌላኛው ምክንያት ‹‹ደስ አያሰኙኝም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፤ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፤……….አፈርም ወደነበረበት ምድር ሳይመለስ÷ ነፍስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ›› የሚል ነው፡፡ በፀሐይ በጨረቃና በከዋክብት የተመሰለ ማግኘት፣ ማሸነፍ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ሮጦ ማምለጥ፣ ወድቆ መነሣት የሚቻልበት የወጣትነት ጊዜ በእርጅና በድካም በደዌና ከፍ ሲልም በሞት ይደመደማል፡፡ በብርሃን ጀምረን በብርሃን፤ በድል ጀምረን በድል እንድንፈጽም ታናሽ የሆነ ጅማሬያችን እጅግ የበዛ እንዲሆን በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔርን በመንገዳችንና በተግባራችን ሁሉ እናስብ፤ ከእርሱ ጋር እንኑር፤ ስለ እርሱም እንናገር!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር