በግዮን ሆቴል ሊካሔድ የነበረው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ እንዳይካሔድ ተከለከለ
የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በየሦስት ዓመቱ የሚካሔደው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠ መመሪያ መሠረት እንዳይካሔድ ተደርጓል፡፡
የጉባኤውን መከልከል አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ እና የማኅበሩ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት በጋራ እንደገለጹት “ማኅበሩ በየሦስት ዓመቱ ይህንን ጉባኤ ያካሒዳል፤ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ዓላማውም የአብነት መምህራንን የቀለብ፣ የአልባሳት፣ የፍልሰት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም መምህራኑ በቂ ደመወዝ ስለማይከፈላቸው ድጋፍ ለማድረግና የአቅም ማጐልበቻ ውይይትና ሥልጠና ለማድረግ የታቀደ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ደብዳቤው ደርሶን የጉባኤውን መታገድ ምክንያት ለጊዜው ባንረዳም በቅዱስነታቸው መመሪያ መሠረት ጉባኤው መካሔድ እንደሌለበት ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ደብዳቤ እንደደረሳቸውና መቋረጥ እንዳለበት በቃል ነግረውናል” በማለት ገልጸው የዘንድሮው ጉባኤ ካለፉት ጉባኤያት የሚለየው በምንድን ነው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ:-
“የዘንድሮው ጉባኤ ባለፉት ጉባኤያት ከተነሡት አጀንዳዎች ልዩነት የለውም፡፡ ቀጣይና የሞኒተሪንግ አካል ነው፡፡ ትልልቅ ግንባታዎች የአብነት ት/ቤቶች ይሠራሉ፡፡ በእነዚህ ሥራዎች ላይ ጥያቄ አልቀረበም፡፡ በግዮን ሆቴልም ሆነ በሌሎቹ ማእከላዊ ቦታዎች ምክክር ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ አሁን የተከለከለውን ጉባኤ እንደገና ለማካሔድ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋርና ከብፁዓን አባቶች ጋር የጀመርነውን ውይይት እንቀጥላለን፡፡ ተመካክረን የምንሠራበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፤ ለዚህም ተስፋ አለን” በማለት ገለጻቸውን አጠቃለዋል፡፡