በግብፅ አብያተ ክርስቲያናትና ክርስቲያኖች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው
ነሐሴ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ደጋፊዎች የሆኑት የሙስሊም ወንድማማቾች በግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በተለይም በዲልጋ፤ ሚና፤ እና ሶሃግ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ የሚና ቅድስት ማርያምና የአብርሃም አብያተ ክርስቲያናት የሙስሊም ወንድማማቾችና ደጋፊዎች በእሳት አያይዘዋቸዋል፡፡ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችንም ሶሃግ በሚገኘው ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ወርውረዋል፡፡
ከካይሮ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የአልቃይዳ መለያ የሆነው ጥቁር ባንዲራ እየተሰቀለባቸው ሲሆን በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡
በላይኛው ግብፅም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉና ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን ክርስቲያኖችም መገደላቸውን ከግብፅ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ለመውጣት መገደዳቸውንም እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ሊቢያዊው ታማር ረሻድ የተባለው ተቃዋሚ “ለፓትርያርክ ታዎድሮስ መልካም ዜና ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ በግብፅ ምድር ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት የማይኖሩበት ጊዜው ደርሷል” በማለት ለቴሌቪዥን ጣቢያው ሲናገር ተደምጧል፡፡
በላይኛው ግብፅ ከሚገኙት ሚና፤ አስዩትና ሶሃግ በተጨማሪ የክርስቲያኖች መኖሪያና የሥራ ቦታዎች በእሳት ተያይዘዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱም አገልግሎታቸውን ማቋረጣቸውን ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡