በግብጽ አብያተ ክርስቲያናት በደረሰ የቦምብ ጥቃት ከዐርባ አራት በላይ ክርስቲያኖች ዐረፉ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

egypt10

በግብጽ አገር የቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት

በግብጽ አገር በአሌክሳንደርያ እና ታንታ ከተሞች በቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በደረሰ ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ከዐርባ አራት በላይ ክርስቲያኖች ሲያርፉ፣  ከአንድ መቶ በላይ የሚኾኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፡፡

egypt11

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጣዊ ክፍል እና ጥቃቱ በሕንጻዎቹ ላይ ያደረሰው ጉዳት በከፊል

ጥቃቱ የደረሰው በርካታ የግብጽ ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው በዓለ ሆሣዕናን ሲያከብሩ በነበሩበት በዕለተ ሰንበት ረፋድ ላይ ሲኾን፣ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በምእመናን በምእመናን ላይ ለደረሰው አሰቃቂ ጥቃትም ‹አይ ኤስ አይ ኤስ› ተብሎ የሚጠራው የጥፋት ቡድን ‹‹ሓላፊነቱን እወስዳለሁ›› ማለቱን፤ የሟቾች ቍጥርም ከተጠቀሰው አኃዝ በላይ እየጨመረ መምጣቱን ልዩ ልዩ የብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡

bishop-angaelos

ብፁዕ አቡነ አንጌሎስ – በእንግሊዝ አገር የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ

በእንግሊዝ አገር የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አንጌሎስ የደረሰውን ጥቃት በማስመልከት በሰጡት ቃለ ምዕዳን፡- ‹‹… በዛሬው ዕለት በዓለ ሆሣዕናን እና የክርስቶስን ወደ ኢየሩሳሌም መግባት እንዳከበርን ዅሉ፣ በዚህች ዕለት ያለፉ ወገኖቻችንም ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም መግባታቸውን እናጠይቃለን፡፡ የመድኃኒታችንን ቅዱስ ሳምንት (ሰሙነ ሕማማት) ስናከብርም የቤተሰቦቻቸውን ሐዘን እና በዚህ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን  ወገኖቻችንን ሕመም እንጋራለን፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ታላቁን በዓለ ትንሣኤ በምናከብርበት ወቀትም ምድራዊ ሕይወታችን ብዙ ጊዜ በመከራ የተመላ የሕይወት ጉዞ እንደ ኾነና ይህ መከራም በመጨረሻው ዘመን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንደሚያበቃን እናስተውላለን›› የሚል መልእክት አስተላፈልዋል፡፡

egypt12

‹‹ስለ እርሱ ዅልጊዜ ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎች ኾነናል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለይ ግብጻውያን በተደጋጋሚ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ በዚህ ዓመት በግብጽ ከደረሱ አሰቃቂ ጥቃቶች መካከል ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በካይሮ ከተማ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ከሃያ አምስት በላይ ግብጻውያን ክርስቲያኖችን መቅሠፉና ከአምሳ በላይ የሚኾኑትን ማቍሰሉ የሚታወስ ነው፡፡ በትናንትናው ዕለት የደረሰው ከፍተኛ ጥቃትም መላው የግብጽ ሕዝብን አስጨንቋል፡፡ የግብጽ መንግሥትም ለሦስት ወራት የሚቆይ የአስኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡

ምንጮች፡

  • Alahram /Daily News Egypt
  • Aljazeera
  • BBC
  • Christian Today
  • CNN
  • Orthodoxy Cognate Page
  • Reuters