በግቢ ጉባኤያት ለሚሰጥ የአብነት ትምህርት አገልግሎት ትኩረት እንስጥ

ኅዳር 28/2004 ዓ.ም.


የአብነት ትምህርት የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎትና የአገልግሎት  ሥርዓት መሠረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የአብነት ትምህርት የኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ መሠረትና አንድ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን መስፋፋቱን ተከትሎ ግን የአብነት ትምህርት ቤቶች ሚና ቤተ ክርስቲያን ለምትፈልገው አገልግሎት በሚያበረክተው ድርሻ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ሆኗል፡፡ ከዚያም አልፎ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን የመተዳደሪያ ሀብት ንብረት ማጣቷ በአብነት ትምህርት ቤቶች ጥንካሬ ከዚያም አልፎ በህልውናቸው ላይ ፈተኝ ሁኔታዎች ጋርጧል፡፡

ከእነዚህ ተጽዕኖዎች በላይ ግን አሳሳቢ የሆነው ከአብነት ትምህርት የሚወጡ ደቀመዛሙርት ዘመናዊውን ትምህርት የሚቀስሙበት አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ዘመናዊውን ትምህርት የሚከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለአብነት ትምህርቱ ባዕድ ሲሆኑ መታየታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ዓለማት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ውስጥ እየታዩ መምጣታቸው በአገልግሎት አሰጣጡ እና አቀባበሉ አለመግባባት፣ በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አንድነት ላይ ፈተና የማስከተል አዝማሚያ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በዘመኑ ልትጠቀምበት የሚገባውን የአሠራር፣ የአደረጃጀት፣ የአመራርና የአስተዳደር ዘይቤ ከዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት እንዳትወስድ አድርጓታል፡፡

እነዚህ መራራቆች በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አገልግሎቱን በሚቀበሉ ምእመናን መካከል ያለው ግንኙነት ላይ ችግሮች ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ በአገልግሎት አሰጣጡ የሚያስፈልገውን ሥነልቦናዊ አንድነት ያሳጣል፡፡ ከዚያ ውጭ አንዱ የትምሀርት ምንጭ ለሌላው ያለው አተያይ የተዛባ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ዘመናዊ የሚባለው ዓለም ያመጣውን ዕሴት ሁሉ በጭፍን የምትቃወም፣ የምትጸየፍም ያስመስላል፡፡ በአንጻሩ ዘመናዊ የሚባለው ዓለም የቤተ ክርስቲያን የሆነውን ሁሉ ኋላቀር አድርጎ የማሰቡ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ስለዚህ ይህንን የአመለካከት መራራቅ አጥፍቶ ቀጣይነት ያለው መፍትሔ ለማምጣት እንዲሁም በዘመናዊው ትምህርት ደቀመዛሙርትና በአብነት ትምህርት ደቀመዛሙርት መካከል በአገልግሎት አሰጣጥና አቀባበል ያለውን የመንፈስ አንድነት ለማምጣት ርእይ ይዞ፣ የሚጠይቀ ውን ስልታዊ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባት ተገቢ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ርእይ እውን ለማድረግ የሚቻለው በሁለቱም ዓይነት ትምህርት ምንጭ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ማለትም በአብነት ትምህርት ቤቶችና በዘመናዊው ትምህርት ተቋማት /ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች/ ላይ ቢሠራ እንደሆነ ያምናል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ተቋማት ማኅበሩ ያለውን የአገልግሎት ርእይ እውን ለማድረግ የመረጣቸው ስልታዊ ተቋማት ናቸው፡፡

በመሆኑም የአብነት ትምህርት የሚሰጥባቸው ጉባኤያት በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይፈቱ ለማድረግ ምእመናንን በማስተባበር ለትምህርት ቤቶቹ እድገት፣ ለመምህራኑ እና ለደቀመዛሙርቱ ኑሮ ከሚያደርገው ቁሳዊ ድጋፍ በተጨማሪ በጉባኤያቱ ከሚሰጠው መንፈሳዊ የአገልግሎት ትምህርት ጎን ለጎን የዘመናዊው ትምህርት ዕሴቶች ከሆኑት የአስተዳደር፣ የአመራር እና የሙያ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተጋ ነው፡፡

ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ በሚደረግባቸው ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ላሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ደግሞ ባቅራቢያቸው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰብስቦ የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አገልግሎቶች አንዱ ደግሞ የአብነት ትምህርት ነው፡፡ ተማሪዎች ዘመናዊ ትምህርት በሚከታተሉባቸው የትምህርት ተቋማት ውስጥ ሆነው  ከአብነት ትምህርት ጉባኤያት ጋር እንዲተዋወቁ፤ ከዚያም ባለፈ በጉባኤያቱ ተምረው አስመስክረው እንዲወጡ፤ የዲቁናና የቅስና መዓርገ ክህነት እንዲቀበሉ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ጣዕምና መዓዛ ስበት ቀላል ባለመሆኑ በትምህርት ቆይታቸው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ገበታም ውጭ በሥራ ላይ እያሉ የመከታተል፣ የማስፋት፣ የማሳደግ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል፡፡

የዚህ ተግባር ዋነኛ ግቦችም አስቀድመን የጠቀስነውን የአብነት ትምህርቱን ክብርና አስፈላጊነት ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ፣ ሀገሪቱ ወደፊት ከፍተኛ ሓላፊነት የምትሰጣቸው፣ የሀገራ ችን ዕድገት ፖሊሲ አውጪና አስፈጻሚ ልሂቃን እንዲያውቁት፣ እንዲወዱት፣ እንዲያከብሩት፣ እንዲያገለግሉበትና እንዲገለገሉበ ትም ማድረግ ነው፡፡ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እነዚህን ጉባኤያት ባወቋቸው ቁጥር እንደሚወዷቸው ይታመናል፡፡ ከወደዷቸው ደግሞ ይንከባከቧቸዋል፤ ያበለጽጓቸዋል፡፡ ስለዚህ የአብነት ትምህርቱን ህልውና ከማስጠበቅም አንጻር ታላቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት በሀገሪቱ የተለያዩ ሓላፊነትን፣ የሙያ ስምሪትንም ይዘው ከሚሠሩ ልሂቃን ጋር በአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ ተግባብተው የማየት ርእይ እውን ይሆናል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ይህ ርእይ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ወገን ርእይ መሆኑንም ያምናል፡፡ ከዚህ እምነት በመነሣትም የሁሉም ወገን ርእይ እውን እንዲሆን ደረጃ በደረጃ በሚፈጸሙ ተግባራት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ይሻል፡፡ የሁሉም አካላት ድርሻ የሚመነጨው ደግሞ ካለን አቅም ነው፡፡ ለዚህች ሀገር ዕድገት በጎ ሐሳብ ያላቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአብነት ትምህርት የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዕውቀት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ መንፈሳዊ ቅርሶች አንዱ አካል፣ ለማኅበረሰቦች የአኗኗር ባህልና ዕሴት አስተዋጽኦ የነበረውና ያለው የትምህርት ሥርዓት በመሆኑና የሀገራችን የትምህርት ታሪክ መሠረት በመ ሆኑ በሚመለከቷቸው ሓላፊነቶች በኩል ሊያደርጓቸው የሚገቡ አስተዋጽኦዎችን ማበርከት ይገባቸዋል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ድርሻ ግን መተኪያ የሌለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምእመናንና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከፍተኛ ባለደርሻ ናቸው፡፡ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አካላት በተሰጣቸው የሓላፊነት ደረጃ ልክ የወደፊቱን የቤተ ክርስቲያናችንን የአገልግሎት አካሔድ የተሻለ ለማደረግና ከፈተና ለመጠበቅ መጣር ይገባቸዋል፡፡ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች የአብነት ትምህርትን ቀስመው እንዲወጡ ከማነሣሣት ጀምሮ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ልባዊ ድጋፍም መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምእመናን ደግሞ የአብነት ተማሪዎችንና ትምህርት ቤቶችን መምህራንና ደቀመዛሙርቱን ለመደገፍ እንዲቻል ማኅበረ ቅዱሳን የሚያደርገውን ጥረት በገንዘባቸው፣ በጉልበትና በዕውቀታቸው  ለመደገፍ ያለመሰልቸት መንቀሳቀስ ይመበቅባቸዋል፡፡ በኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችም የአብነት ትምህርት መርኀ ግብሮችን በተጓዳኝ መከታተል እንዲችሉ ማበረታታት ይገባቸዋል፡፡ ወደኮሌጆች ከመግባታቸውም በፊት ተማሪዎች በየትውልድ አካባ ቢያቸው አብነት ትምህርትን ለመከታተል ዝንባሌ እንዲያድር ባቸው ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ የማኅበራችን ማዕከላትም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ የአብነት ትምህርት ለመከታተል ለተዘጋጁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ተምረው ዘመናዊውን ትምህርት በብቃት የተከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በአገልጋይነትም ሲሳተፉ ለማየት የያዝነውን ርእይ እውን እንዲሆን ሊተጉ ይገባል፡፡ ለዚህም ተማሪዎቹን ማነሣሣት፣ መምህራንና የትምህርት ቦታውን ማዘጋጀት፣ ከሚከታተሉት ዘመናዊ ትምህርት ጋር የተጣጣመ መርኀ ግብር መንደፍ፣ የተማሩትን ትምህርት ደረጃ እንዲያውቁ በአጥቢያቸው ባሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች እንዲሳተፉ ማድረግ የየጊዜውን ሂደት መገምገም እና የመሳሰሉት ተግባራት ሁሉ ይጠበቁብናል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ለተያዘው ርእይ እውን መሆን ድርሻ አለኝ የሚሉ አካላት ሁሉ ባላቸው አቅምና ችሎታ ሚና እንዲጫወቱ ማኅበራችን ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ወገን የቤተ ክርስቲያን  አገልጋዮቿ በሁሉም ነገር አቅማቸው የጎለበተ ሆነው በአንድ ሐሳብ በአንድ ልብ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ተስፋ እንዲሆኑ መጣር ይገባል፡፡

 

ምንጭ፡- ሐመር 19ኛ ዓመት ቁ.6 ጥቅምት 2004 ዓ.ም