በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለስብከተ ወንጌል የሚሰማሩ ሰባክያነ ወንጌል ተመረቁ
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማእከል ሥር የሚገኘው የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል ከአዳአ ወረዳ ቤተ ክህነት፤ ከበጎ አድራጊ ምእመናንና ማኀበራት ጋር በመተባበር በሁለተኛ ዙር ገጠር ተኮር የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለ፰ ወራት በሂዲ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወካህን መልከ ጼዲቅ አብያተ ክርስቲያናት ያሰለጠናቸውን ፴፬ ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ጥር ፭ ቀን ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም የአድአ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን፤የየአጥቢያዎቹ አስተዳዳሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል አባላት በተገኙበት አስመረቀ፡፡
ሰልጣኞቹ ከ፲ አጥቢያዎች የተመለመሉ ሲሆን፣፱ የትምህርት አይነቶችን ሲከታተሉ መቆየታቸውን፣አብዛኛዎቹ ሰልጣኞችም ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸው አቶ ሀብታሙ ዘውዱ የወረዳ ማእከሉ ሰብሳቢ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ካህናቱና ዲያቆናቱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስልጠናውን መውሰዳቸውም ለወደፊቱ ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተጨማሪ የቤተ የመቅደስ አገልግሎትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሆነና አብያተ ክርስቲያናቱም ለሥልጠና የሚሆኑ ቦታዎችን በማመቻቸት የነበራቸው ተሳትፎ ታላቅ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
“የሥልጠናው ዋና ዓላማ ምእመናን በሚያውቁት ቋንቋ በማስተማር ከነጣቂ ተኲላዎች ለመጠበቅ ነው፡፡ የሥልጠናው ሙሉ ወጪም ብር 123,348.90 (አንድ መቶ ሀያ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንትብር ከዘጠና ሳንቲም) በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ግቢ ጉባኤ ተመራቂዎች የተሸፈነ ነው” ብለዋል፡፡ የቀድሞ ተመራቂዎቹ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢው ይህንን መልካም ተሞክሮ ሌሎችም ማኀበራት በመውሰድ ሊማሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክትም “ሰልጣኞች ከምረቃ በኋላ ትምህርት በቃን ሳትሉ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግር ሥር ቁጭ ብላችሁ መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይገባችኋል፡፡ ዋናው ዓላማችሁንም ባለመዘንጋት ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች እየተዘዋወራችሁ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ይጠበቅባችኋል” በማለት በሪፖርታቸው አስገንዝበዋል፡፡
የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል አባላት ከግልና ከማኀበራዊ ጉዳያቸው ቅድሚያ ለሥልጠናው ልዩ ትኩረት መስጠታቸው፣ የአዳአ ወረዳ ቤተ ክህነት ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላትና ለአጥቢያዎች መመሪያ በመስጠት ስልጠናው የተሳካ እንዲሆን ታላቅ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን መልአከ ፀሐይ ቀሲስ እንዳለ ሐረገወይን ባስተላለፉት መልእክትም የወረዳ ማእከሉ ለስበከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን ለተመራቂዎችም “በቋንቋ ምክንያት የሚጠፋውን ትውልድ ከሞት ወደ ሕይወት የመመለስ አደራ አለባችሁ” ብለዋል፡፡
የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል ከአድአ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከበጎ አድራጊ ምእመናንና ማኅበራት ጋር በመተባበር በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተተኪ ሰባኪያነ ወንጌል ለማፍራት ፕሮጀክት ቀርጾ በመጀመሪያው ዙር በድሬ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከ፰ አጥቢያዎች የተመለመሉትን ፳፫ ሰልጣኞችን ለስምንት ወራት አሰልጥኖ የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በአባቶች ቡራኬ አስመርቋል፡፡
ምንጭ፤ሰምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 26ኛ ዓመት ቊ8ቅጽ 26ኛ ቊጥር 398 ከጥር 1-15 ቀን2011ዓ.ም