‹‹በደስታ በዓልን አድርጉ›› (መዝ.፻፲፯፥፳፯)
መስከረም ፲፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ቀናትን ሁሉ ባርኮ የሰጠን አምላካችን እግዚአብሔር ጊዜ የእርሱ ስጦታ በመሆኑ የከበረ ድንቅ ሥራውን ፈጽሞበታል፡፡ በእያንዳንዱ ዕለት ፍጥረታትን ከመፍጠሩ ባሻገር ለምስጋና፣ ለውዳሴ እና ለድኅነት ያከበራቸው በዓላትም አሉት፤ በእነዚህ ዕለታት ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረን የግዝት በዓላት ማለትም የወልድ/በዓለ ወልድ (፳፱)፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችበት በዓል (፳፩)፣ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓል (፲፪) እንዲሁም ሰንበታትን ጨምሮ ቅዱሳንን የምንዘክርባቸው እና የምናከብርባቸው በዓላት የድኅነታችን መሠረትና መፈጸሚያ በመሆናቸው የደስታችን ቀናት ናቸው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል ቅዱስ ግማደ መስቀሉ ወደ ግሸን ደርቤ ከርቤ የገባበትን ዕለት መስከረም ፳፩ ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ከንዋየ ቅድሳት ጋር በክብር በሠረገላ ተጭኖ ወደ ሀገራችን ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያም ታላቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ማብራቱን ቅዱሳት መጽሐፍ ይጠቅሳሉ፡፡ (መጽሐፈ ጤፉት)
ከዚህም በኋላ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› በማለት ደጋግሞ በራእይ እግዚአብሔር አምላክ በነገራቸው መሠረት ንጉሡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡
የከበረ ግማደ መስቀሉ የድኅነታችን ዓርማ፣ የሰላማችን መገኛ እንዲሁም የማንነታችን መገለጫ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተባረከች ናት፡፡ አምላካችን ክቡር ሥጋውን የቆረሰበትና ቅዱስ ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀል የሰው ልጆች ሁሉ ድኅነት ሲሆን ሙታንን የሚያስነሣ፣ ድውያንን የሚፈውስ፣ ዓይነ ሥውራንን የሚያበራ እንዲሁም ብዙ ድንቅ ተአምራትን የሚያድረግ በመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ነን፡፡
በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ግሸን ደርቤ ውስጥ በሚገኘው የእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጦ የሚገኘው ግማደ መስቀሉ የክርስቲያኖች መመኪያ ነውና የከበረ በዓልን በደስታ ልናደርግ ይገባል፤ ‹‹በደስታ በዓልን አድርጉ›› እንዲል፡፡ (መዝ.፻፲፯፥፳፯)
መስከረም ፳፩ ከሚከበሩት በዓላት ሌላው ፫፻፲፰ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለመስጠት የተሰባበሰቡት ቀን ነው፡፡ መናፍቅ አርዮስ “የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም” በሚል ክህደት በተነሣበት ወቅት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡
ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሄድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡ በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንቱ በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ የክፉ ሰዎች መጨረሻ አያምርምና አርዮስ በክፉ አሟሟት እንደሞተ በቅዱሳት መጽሐፍ ተመዝግቦ እናገኘዋለን፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር)
የሁሉ ፈጣሪና ገዢ፣ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ፈጣሪያችን አጋዝተ ዓለም ሥላሴ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በሦስትነቱ ሲቀደስ ሲሠለስ ሲኖር ክብሩ ብቻውን እንደቀረ አውቆ ፳፪ቱ ፍጥረታትን እኛ ሰዎችን ጨምሮ ፈጥሮናል፡፡ ስለዚህም የፈጣሪያችን የቅድስት ሥላሴ ሕልውናውን በማወቅ፣ ባሕርይውን በመረዳትና ለሕጉ በመገዛት ልንኖር ይገባል እንጂ ክህደት ልንፈጽም አይገባም፡፡ የተፈጠርንበትንም ምክንያት በተገቢው መንገድ በመረዳት ለአምላካችን መገዛት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸው ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የእግዚአብሔርን መንግሥት ወርሰዋል፡፡ ፈጣሪያቸውን የካዱ እንደ አርዮስ ያሉ መናፍቃን ግን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመሞታቸው ባሻገር ወደ ገሃነመ እሳት ተጥለዋል፡፡
ጠላታችን ዲያብሎስን በመስቀሉ እንዳሸነፈልን ሁሉ ጌታችን አርዮስንም በቅዱሳኑ ሊቃውንት አማካኝነት አጥፍቶታል፡፡ ይህ ለእኛ ታላቅ ደስታ ነው፤ ምክንያቱም የጥሉን ግድግዳ አፍርሶ፣ ጠላትን አሸንፎና መናፍቃንን አጥፍቶ ቤተ ክርስቲያንን ባያጸናል ኖሮ የድኅነት መንገድ አይኖረንም ነበር፡፡ ስለዚህ አምላካችን በማመስገንና ቅዱሳን ሊቃውንቱን በመዘከር ይህን የከበረ በዓል በደስታ ማክበር ተገቢ ነው፡፡
የክርስቲያኖች ደስታ ድኅነት ነው፤ የክርስቲያኖች ደስታ አምላክን ማመስገን ነው፤ የክርስቲያኖች ደስታ በሰላም፣ በፍቅር እንዲሁም በአንድነት መኖር ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ባለቤት ደግሞ አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ለእርሱ ያለንን ፍቅር፣ ክብርና ምስጋና በገሃድ የምንገልጸው ደግሞ ስሙ በሚጠራበት፣ ክብሩ በሚወደስበት እንዲሁም ድንቅ ተአምራቱ በሚዘከሩበት በከበሩ በዓላት ቀን ነው፡፡ አምላካችን ደስ የሚሰኝብን መልካም ስናደርግ፣ በዓላቱን ከእኩይ ተግባራት በመራቅ፣ ለሰዎች በጎ በማድረግ እንዲሁም በሥርዓት ሲሆን ነው፡፡
መልካም በዓል!