በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የደን ቃጠሎ በባሰ ሁኔታ ላይ ይገኛል!

መጋቢት 10/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


እሳት ወይስ መአት?


በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የደን ቃጠሎ በባሰ ሁኔታ ይገኛል፡፡ ቅዳሜ መጋቢት 8/2004 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 በኋላ ልዩ ስሙ አዱላላ ከሚባለው አቅጣጫ የተቀሰቀሰው ቃጠሎ በመነኮሳትና በአካባቢው ምእመናን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት  እያደረጉ እንደሚገኙና ከደብረ ዘይት የአየር ኀይል አባላት ትላንት ምሽት መጥተው እገዛ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን የገዳሙ ጸሐፊ አባ ወ/ሩፋኤል ቢገልጹም መፍትሔ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡

 

የቃጠሎው መንስኤ ለማወቅ ያልተቻለ ሲሆን “የቅዱሳን ከተማ” የተሰኘው የአባቶች የጸሎት ሥፍራ በከፍተኛ ሁኔታ በመቃጠል ላይ እንደሚገኝና በሥፍራው ውኃ የሌለ በመሆኑ ቃጠሎውን ለማጥፋት አፈሩን በመቆፈርና በመበተን እንጨቶችን በመቁረጥና በቅጠል በማጥፋት ርብርቡ የቀጠለ ቢሆንም ቃጠሎውን መግታት እንዳልተቻለ አባ ወልደ ሩፋኤል ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ወደ ጸበሉ ቦታ እንዳይደርስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ምእመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ገዳሙ በመሔድ ቃጠሎውን ለማጥፋት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ የገዳሙ ጸሐፊ አባ ወልደ ሩፋኤል ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ መጠኑን ለመግለጽ መቸገራቸውንና ለመንግሥት አካላትና ለምእመናን የድረሱልን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ተመሳሳይ ቃጠሎ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ በመሆኑ “እሳት ወይስ መአት?! በማለት በጭንቀትና በስጋት ምእመናን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

 

በ2000 ዓ.ም. በዚሁ ገዳም ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቅርቡም በጎንደር የሰለስቱ ምእት መጻሕፍተ መነኮሳት ጉባኤ ቤት፣ እንዲሁም የጥንታዊው የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ትምህርት ቤት ቃጠሎ የደረሰባቸው ሲሆን በምዕራብ ሐረርጌ የሚገኘው የአሰቦት ገዳም ደን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ይታወቃል፡፡

 

የዝቋላ የሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ውሎ

ቃጠሎው እጅግ አሳሳቢ  ሆኗል፡፡


ከጧት ጀምሮ ምእመናን ከደብረ ዘይት፣ ከአዲስ አበባ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ በማኅበረ ቅዱሳን የሚመራው የዩኒቨርሲቲዎች የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ቃጠሎውን ለማጥፋት ቦታው ድረስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከገዳሙ በደረሰን መረጃ መሠረት እስከ ቀኑ 12፡00 ሰዓት ድረስ ቃጠሎው በፀሐይና በንፋስ በመታገዝ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡ መነኮሳቱ ለኦሮሚያ ፖሊስ፣ ለፌደራል ፖሊስና ለአየር ኀይል እንዲሁም ለምእመናን የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ቦታው እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ውኃ ማግኘት ባለመቻሉ የደኑን ውድመት እያባባሰው ስለሚገኝ ውኃ የሚያመላልሱ ቦቴ መኪናዎች ያሏቸው ምእመናን ውኃ በማመላለስ እንዲደርሱላቸው በመማጸን ላይ ናቸው፡፡

 

ከተለያዩ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱት ምእመናን ከአስቸጋሪ ጉዞ በኋላ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ቦታው የደረሰ ሲሆን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ዜና እስካጠናቀርንበት 12፡00 ሰዓት ድረስ ቃጠሎው እንዳልጠፋና ከሌላ አቅጣጫ ሌላ አዲስ ቃጠሎ መቀስቀሱን በቦታው ከሚገኙ ምእመናን ለመረዳት ችለናል፡፡ ቃጠሎው በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ የደን ሀብት ያለበት ቦታ መያዙ እንደማይቀር ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

 

በቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናን እንደሚገኙ ከቦታው የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን በከፍተኛ ጥምና ረሃብ ላይ ለሚገኙ ምእመናን ውኃና ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጭምር ገልጸዋል፡፡