በዓታ ለማርያም
እንኳን አደረሰን
ቅድስት ድንግል ማርያም በ፶፻፬፻፹፭ ዓመተ ዓለም ከሐና እና ከኢያቄም በፈቃደ እግዚአብሔር ተወልዳ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ የኖረችው በወላጆቿ ቤት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ኢያቄምና ሐና የተሳሉትን ስእለታቸውን አስታውሰው ወስደው ለቤተ እግዚአብሔር ሰጧት፤ ካህኑ ዘካርያስም ስለምግቧ በመጨነቁ ሕዝቡን ሰብስቦ ሳለ መልአኩ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ዘካርያስ ለእርሱ የመጣ ሀብት መስሎት ታጥቆ እጅ ነስቶ ቢቆም ወደ ላይ ራቀበት፡፡ ከስምዖን ጀምሮ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎችም በተራ ቢሞክሩ በተመሳሳይ ወደ ላይ ራቀባቸው፡፡ ምን አልባት ለእንግዶች የመጣ ሀብት እንደሆነ ብለው ሐና እና ኢያቄም እንዲቀርቡ አደረጓቸው፤ ለእነርሱም ራቀባቸው፤ ዘካርያስም ሐናን ‹‹እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምና ልጅቷን ትተሸ ወደዚህ ነይ›› ባላት ጊዜ ቅድስት ማርያም ድክ ድክ እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ ፋኑኤል ወደ እርሷ ቀርቦ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ መግቧት ዐረገ፤ ሊቀ ካህናቱም ሕዝቡም የምግቧ ነገር ከተያዘልን በቤት እግዚአብሔር ትኑር ብለው አስገቧት፤ይህም ታኅሣሥ ፫ ቀን ነበር፡፡
ድንግል ማርያምም ሰማያዊ ኅብስትና መጠጥ እየተመገበች ፲፪ ዓመት በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡ ፲፭ ዓመት ሲሞላት ግን ለአቅመ ሔዋን በመድረሷ ከቤተ መቅደስ ትውጣልን በማለት አይሁድ በጠላትነት ተነሱባት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም ይህን ሰምቶ እመቤታችንን ጠየቃት «ኦ ወለተ እስራኤል እፎ ትፈቅዲ ትንበሪ፤ ልጄ እንደምን ሆነሽ ልትኖሪ ትወጂያለሽ?» አላት፡፡ እርሷም «ከእግዚአብሐር በታች ያለኸኝ አባት አንተ ነህ፤ በዚያውም ላይ እናት አባቴ አደራ ያሉህ አንተን ነው፤ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ፤» አለችው፡፡ ዘካርያስም ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን በትራቸውን ሰብስበህ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አግብተህ ስትጸልይ አድረህ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት አውጣው ብሎ ምልክትም እሳይህአለው ብሎ ነገረው፡፡ እርሱም እንዳለው አድርጎ በማግሥቱ በትሮቹን አውጥተው ቢያዩ የዮሴፍ በትር አብባና አፍርታ ተገኘች፡፡ ከበትሩ ጫፍ ላይ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ዕቀባ ለማርያም ፍኅርትከ፤ ዮሴፍ ሆይ እጮኛህ ማርያምን ጠብቃት፤» የሚል ጽሑፍ አገኙ፤ርግብም መጥታ በራሱ ላይ አርፋለች፤ ስለሆነም ዮሴፍ እንዲጠብቃት ተወሰነ፡፡