በዓለ ግዝረት
ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
በዘመነ ብሉይ ግዝረት የተጀመረው በአባታችን አብርሃም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሕዘበ እግዚአብሔር ከአሕዛብ የሚለዩበትና ክብር የሚያገኙበት ሕግ መጽሐፊያዊ ግዝረት ነበር፡፡ ያም እንደ ጥምቀት ይሆንላቸው ነበርና ነው፡፡ (ዘሌ.፲፪፥፫)
የከበረ ወንጌል እንደገለጸው በዘመነ ሐዲስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በስምንተኛው ቀን ግዝረትን ፈጽሟል፡፡ “ጌታ ሰው መሆኑ ሕገ ኦሪትን ሊሽር ባለመሆኑ ሥርዓተ ግዘረትን ፈጽሞልናል፡፡” (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፵፩)
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ፤ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውኃ ሆኖ ፈሰሰ። ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ፡፡” (ሉቃ.፪፥፳፩-፳፫)
የአምላካችን ድንቅ ሥራ ተነግሮ አያልቅምና በከበረች በጥር ፮ ቀን ሥርዓተ ግዝረትን የፈጸመልን ጌታ እኛም እርሱን አብነት አድርገን ወንድ ልጆችን በስምንት ቀናቸው እንድናስገርዝ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን ከጌታችን ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪያው የሆነውን የተቀደሰ ቀን ታከብረዋለች፡፡
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!
