በዓለ ዕረፍታ ለማርያም

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ጥር ፲፱፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

እንኳን ለእናታችን ለቅድስተ ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ!

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ይላል፤ “ትጥዓም ሞታ እሙ ወእመ ኵሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ፤ እናቱና የሁሉ እናት ሞትን ትቀምሰው ዘንድ ወልድ በማይሻር ቃሉ አዘዘ።” (ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም) ክርስቲያኖች ሞት ምን ጣዕም አለውና ነው? እስኪ ንገሩኝ! ጣፋጭ ነው ወይስ መራራ ወይስ ቆምጣጣ? ፈልፈለ ማኅሌት ቅዱስ ያሬድ “ሞትን ትቀምሰው ዘንድ አዘዘ” ሲለን የሚቀመስ ነገር ቢሆን አይደል? እስኪ ልጠይቃችሁ ሞት ምን ዓይነት ጣዕም ይኖረው ሽታውስ ምን ይሆን? አላስቀርብ ይል ይሆን? ወይስ ሽታው የሚያውድ ሆኖ ደስ እያላት ትቀርበው እንጃ?

ዛሬ የመቃብር ሽታ ተቀይሯል፤ መዓዛው ልዩ ሆኗል፤ እንዴት በወንጌል “የተለሰነ መቃብር” እያለ የመቃብርን አስከፊነት ከሰው ውስጣዊ ማንነት ጋር ይገልጽ የለም ብትለኝ አዎ እውነት ነው፤ (ማቴ.፳፫፥፳፯) ነገር ግን ያ ያስፈራ የነበረው፣ አበስብሶ አፍርሶ ይዞ ያስቀር የነበረው መቃብር ዛሬ ከመኖሪያ ቤታችን በላይ ምቹ ቦታችን ሆኗል። “ሽታው የሚጣፍጥ እንደ ዕፀ ሕይወት ያለ የሚጣፍጥ ሽታ ከመቃብሩ አፍ ላይ ወጣ” እንዲል፤ (ተአምረ ኢየሱስ ፺፰ኛ ተአምር) ሞትም ያስፈራ ሁሉንም ያስጨንቀ እንዳልነበር ዛሬ ኃይሉ ተነሣ፤ ደከመ፤ መውጊያው ተሰበረ፤ ጥርሱ ረገፈ።

የመቃብርን ሽታ እንረዳ ዘንድ ኑ፤ ወደ ጎልጎታ እንውጣ እና በዚያ የሆነውን እንይ! ምን ሰማችሁ? ምንስ ዓያችሁ? ክርስቶስ ተቀብሮበት የነበረው የመቃብር ሽታ መላእክትን ሳይቀር የማረከ ሽታ አስተዋልችሁን? ክርስቶስ ሞትን ገድሎት ሲነሳ ተመለከታችሁን? አያችሁ ዛሬ እኛ የምንፈራው የሞተውን ሞት ነው፤ አይገርምም? ልብ በሉ! ክርስቲያን ማለት እንደ የክርስቶስ ልጅ ማለት አይደል? ስለሆነም የመቃብር ሽታ የሚያስቸግረው ሳይሆን መቃብሩ ሽታ እንዲኖረው የሚያደርግ፣ ሞት የሚያስፈራው ሳይሆን በደስታ የሚቀበለው፣ ሞቱ በመቃብር ውስጥ ያለውን ቁጥር በአንድ የሚጨምር ሳይሆን በክርስቶስ ኃይል የሚነሣ፣ ተገድዶ በጭንቅ በገዓር የሚሞት ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ለመኖር እየናፈቀ ሞት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ መሆኑን አውቆ ተዘጋጅቶ የሚቀበል ነው። የሁላችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሞትን

የብዙዎችን ነፍሳት ትታደግ ዘንድ በዚህች ቀን የሞትን ጽዋ ተጎነጨች።
ሞት ሕይወትን የሚሰጠን ከክርስቶስ ጋር የምንኖርበት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ለዚህም ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ “ልሂድ፥ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና” ይለናል። (ፊል.፩፥፳፫) ልብ በሉ! ዛሬ ስንቶቻችን ይህን ነገር እናውቃለን? በእውነት ይህን ሞት ያልቀመሰ ከቅዱሳን ጋር ሰማያዊ ኅብረት መፍጠር አይችልም። እናም ሁላችን እንቀዳደምለት ዘንድ ዛሬ ቅድስት ድንግል ይህን የሞት ጽዋ ቀምሳ እንካችሁ አለችን።

የድንግል ማርያም ዜና ዕረፍት እንዴት ነበር? የሚለውን አንስተን ሐሳባችንን እናጠቃልል፦ ቅድስት ድንግል ማርያም በዮሐንስ ቤት ሳለች ወደ ልጇ መቃብር እየሔደች ጸሎት ታደርግ ነበር፤ በዚህም አይሁድ ተመቀኟትና ሊከለክሉአት ወደዱ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን መንፈስ ቅዱስ ዓይናቸውን እየጋረደላት መሔድን አላቋረጠችም። ከዕለታት አንድ ቀን በቤተ መቅደስ ስትጸልይ ሳለች እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያትን ከእያሉበት ሰበሰባቸው። በምስጋናም አገኟት፤ ወዲያውም ታመመች፤ ልጇ ወዳጇም መላአክትን አስከትሎ ወርዶ ነፍሷን ተቀበላት። (ተአምረ ማርያም፤ ፫,፲፩)

ሐዋርያትም የእመቤታችንን ሥጋ በጌቴሴማኒ ሊቀብሩ ሲጓዙ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “በፊት ልጇ ተነሣ ዓረገ እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ አሁን ደግሞ እርሷ ተነሣች፤ ዓረገች ሊሉን አይደል” በማለት “ኑዑ ናውያ በእሳት፤ ኑ በድንጋይ ወግረን በእሳት እናቃጥላት” ተባባሉ፡፡ ከአይሁድ ወገን የሚሆን ታውፋንያ የሚባል ጡንቻማ ሰው ተመርጦ ከሐዋርያት ሊቀማ የአልጋውን ሸንኮር ያዘ፤ ያኔም መልአኩ እጁን በሰይፍ ቀጣው፤ ሁለት እጁም ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። በፍጹም ልቡ ወደ እመቤታችን ቢለምን ድንግል ማርያም ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንበል ብላ እንዲጸልይለት ነገረችው፤ ያኔም እጅዎቹ እንደ ቀደመው ሆኑለት። (ተአምረ ማርያም ምዕ.፬)

ቅድስት ድንግል መጽሐፍ እንደተናገረ የሞት መድኃኒት ክርስቶስን ወልዳ መሞቷን ስናስብ እጅግ ይደንቀናል፤ ለዚህም ከቅዱስ ያሬድ ጋር እንዲህ እያልን እንዘምርላታለን፤ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለሁሉ የተገባ ነው፤ የማርያም ሞት ግን ለሁሉ ይደንቃል። (ድጓ ዘአስተርዮ ማርያም) በጉሥቁልናችን፣ ሕግ በመተላለፋችን፣ የባሕርያችን ያልሆነውን ሞት ወዳጃችን አስመስለነዋልና ለሁላችን የተገባ ነው። ቅዱስ ዳዊትም “መኑ ሰብእ በሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት፤ ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? (መዝ.፹፱፥፵፰) እንዳለ።

የቅድስት ድንግል ማርያም ሞት ግን ይደንቃል! የሞትን ኃይል ያጠፋ፣ ሞትን በሞቱ የገደለ፣ ክርስቶስን ወልዳ ሳለ መሞቷ ይደንቃል። እናም “ለምን ሞተች?” ብሎ መጠየቅ የተገባ ነው፤ ይኸውም በተአምረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው በሲኦል ያሉ ነፍሳትን አሳይቷት ስለነበር በልጇ ሞት ነፍሳት እንደዳኑ በእርሷ ሞትም ነፍሳትን እንደሚያድንላት ስለነገራት ስለ ኃጢአተኞች ነፍሷን በልጇ ትእዛዝ ሰጠች።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን!!!