በዓለ ኪዳነ ምሕረት

እንኳን አደረሳችሁ!

የካቲት ፲፬፳፻፲  .

ሰአሊተ ምሕረት፣ አቁራሪተ መዓት፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ማኅደረ መለኮት፣ ብፅዕት፣ ከፍጥረት ይልቅ የተመሰገነች፣ እመ ብዙሃን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለፍጥረት ሁለ ድኅነት ይሆን ዘንድ ከተወደደ ልጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን የተከበረች ናት፡፡

በየካቲት ፲፮ ቀን ስሟን ለሚጠራ ለድሆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን ነው። (ስንክሳር፣ የካቲት ፲፮) ይህም እንዲህ ነው። ጌታችን ወደዚህ ምድር የመጣበትን ተግባር ካከናወነ በኋላ በመጨረሻው በቀራንዮ አደባባይ ለአዳም ቤዛ ሊሆን በተሰቀለበት ጊዜ ከእግረ መስቀሉ ላልተለየው በድንግልና ጸንቶ ለኖረው ለቅዱስ ዮሐንስ ድንግል እናቱን በአደራነት ሰጥቶታል፤ ለእርሷም እርሱን ሰጥቷታል። (ዮሐ.፲፱፥፳፮)

ይህም ሆኖ ግን ምንም እንኳን አይሁድ ጠባቂዎችን ቢያቆሙም እመቤታችን ወደ ተወደደ ልጇ መቃብር እየሄደች ማልቀስን አላቋረጠችም ነበር። በዚህም ሁኔታ እያለች መላእክት በዐፀደ ሥጋ ወስደው ጻድቃን ወደ አሉበት ገነት አድርሰዋት በዚያ የጻድቃን ነፍሳት አመስግነዋታል፡፡ ትውልድ ዘየኀልፍ ያመሰግንሻል ያለው ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ነው። (ውዳሴ ማርያም ትርጉም)

ይህንም እንዳየች የኃጥአንንም መኖሪያ ያሳዩአት ዘንድ ወደ ኃጥአን ማደሪያም በወሰዷት ጊዜ የእነርሱን ሥቃይ አይታ እመቤታችን ርኅርኅተ ልብ ናትና ልጇ ከመከራ ያወጣቸው ዘንድ በጎልጎታ ስትጸልይ የካቲት ፲፮ ቀን ልጇ ወዳጇ የእናቱን ልመና ሰምቶ እልፍ አእላፋት መላእክትን አስከትሎ መጥቶ ሌላው ይቅርና ቀዝቃዛ ውኃ እንኳን በስማ የሰጠውን እንደሚምርላት ነግሯት ይህም የሰጣት ቃል ኪዳን እንዳይታበይ በራሱ ምሎላታል፡፡ (ሙሉ ሐሳቡን የካቲት ፲፮ ስንክሳር ላይ ይመልከቱ።)

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎቷ፣ አማላጅነቷና ተረዳኢነቷ አይለየን፤ አሜን!