በወርቅ ከተለበጠው በድንጋይ ወደ ታነፀው
ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መላክ
በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር
የመጀመሪያውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ከጥንት ሰዎች የተፈቀደው ለሰሎሞን ነው፡፡ ሰሎሞን የተወለደበት ዘመን በንጉሡ ዳዊትና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጥል ተወግዶ ፍቅር የተመሠረተበት የፍቅር ወቅት ነበር፡፡ በደለኛነቱ በነቢይ የተረጋገጠበት ንጉሥ ዳዊት በበደለኛነቱ ወቅት ከኦርዮን ሚስት በወለደው ልጁ ሞት ምክንያት የእርሱ ሞት ወደ ልጁ ተዛውሮለት እርሱ ከሞት እንዲድን ሆኗል፡፡ የእርሱን ሞት ልጁ ወስዶለት የልጁ ሕይወት ለእርሱ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ልጅ ሞት በኋላ ያለው ዘመን የሰላምና የእርቅ ዘመን በመሆኑ የተወለደው ልጅ ሰሎሞን ተብሎ ተጠራ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ የፍቅር ስም ነው፤1ኛ ነገ12÷24
የንጉሡ ዳዊት ንስሐ ለመጀመሪያው ጊዜ ቤተ መቅደስ በምድር ላይ ለመሥራት ምክንያት ነው፡፡ የምድር ሁሉ ንጉሥ ሆኖ ተሾሞ የነበረው አባታችን አዳም በደለኛ ሳለ በገባው ንስሐ ምክንያት የአምስት ቀን ተኩል (5500 ዘመን) ቀኖናውን ሲፈጽም የተወለደለት አንድ ልጁ ክርስቶስ የእርሱን ሞት ሞቶለት፣ የራሱን ሕይወት ለአዳም ሰጥቶት ባደረገው ካሳ በአዳምና በእግዚአብሔር መካከል ለተፈጠረው ሰላምና ፍቅር መገለጫ የሚሆን ቤተ መቅደስ በሰዎች መካከል ተሠርቷል፡፡ ዘመኑ ከጌታ ልደት በኋላ ሃምሳ አራት ዓመት ገደማ እመቤታችን ባረገች በአራት ዓመት ወንጌልን ለመስማት ከአውሮፓ ከተሞች የሚቀድማት የሌለው እና በመቄዶንያ አውራጃ የምትገኘዋ ግሪካዊቷ የፊልጶስ ከተማ ፊልጵስዩስ፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ወቅት ወንጌልን ሰምታ ካመነች በኋላ የመጀመሪያው የቤተ መቅደስ ሥራ በመካከሏ ተፈጽሞላታል፡፡
ክርስቶስ በምድር ላይ ሰውን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለማድረግ ሲተጋ ነበር ማደሪያ የሚሆነው ምድራዊ ድንኳን አልሠራም፡፡ ክርስቶስ የመጣው ሰውን ለመሥራት እንጂ በሰማይ ማደሪያ የሌለው ሆኖ ማደሪያ ፍለጋ የመጣ አይደለምና እንዲሁም ጊዜው ገና ስለነበር መጀመሪያ መሠራት ያለበት ሰው ነበር፡፡
ጊዜው ሲደርስ ከላይ በተጠቀሰው ዘመን ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ አስተምረው ባሳመኗት ከተማ መካከል በጥበበ እግዚአብሔር አዲስ ሕንፃ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት ተገነባ፡፡ እስከዚያ ቀን ድረስ ሐዋርያትና ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ለመሰብሰቢያነት ይጠቀሙበት የነበረው ካታኮምብ (ግበበ ምድር) ካልሆነ ለክርስቲያኖች ተብሎ የተገነባ ልዩ ሥፍራ አልነበረም፡፡ የአህዛብ መምህር ሆኖ የተመረጠው ቅዱስ ጳውሎስ እስኪነሣ ድረስ ከሐዋርያት አንዳቸውም ለዚህ አገልግሎት አልተመረጡም፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች የተሰጣቸው ጸጋ ልዩ ልዩ ነውና በአሕዛብ መካከል ቤተ እግዚአብሔር እንዲሠራ የተፈቀደው ለቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡
እርሱ ወንጌልን ሰብኮ ወደ ሌሎቹ ሀገራት ዘወር ሲል ሕዝቡ ተሰብስበው አንድ ጥያቄ ጠየቁ፤ ወደ ቤተ ጣዖት እንዳንሔድ ከልክላችሁናል፤ ሥርዓተ አምልኮ የምንፈጽምበት ቤት ልትሠሩልን ይገባል ብለው ጠየቋቸው፡፡ ጳውሎስና በርናባስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ተማክረው ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰኔ በሃያ ቀን ወርዶ ሐዋርያትን ባንድ ቦታ ሰብስቦ፣ ከተራራ ላይ የተቀመጡ ሦስት ድንጋዮችን ጠቅሶ ወደ እርሱ በማቅረብ ቅድስት፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት አድርጎ ሠርቶላቸዋል፡፡
ቤተ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተ እስራኤል ውጭ ተሠራች፤ ከከበሩ እና ተጠርበው አምረው ከቀረቡ ክቡራን ድንጋዮች ሳይሆን ተራራ ላይ ተቀምጠው ከሚኖሩ ተራ ድንጋዮች ተገነባች፡፡ በወርቅ ከተለበጠው በድንጋይ ወደ ታነፀው ተዛወረች፤ በዝግባና በጽድ የታነፀው አገልግሎት ከመስጠት ተከለከለ፤ በጢሮሳዊ የአልባስጥሮስ ግምጃ የተሸፈነው ተናቀ በነኪራም ብልሃት፣ በነባስልኤልና ኤልያብ ጥበብ የተጌጠው የጸሎት ቤት ክብሩን ለቀቀ፤ ሁሉም ነገር ከተጠበቀው ውጭ ሆነ፡፡
በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የእግዚአብሔር መልዕክት ምንድነው?
ቤተ መቅደሱ በድንጋይ ለምን ተሠራ? ከመሠረት እስከ ጣራና ጉልላት ሌላ ነገር አልተጨመረበትም፤ ድንጋዮቹም ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ዘመን በድንጋይ ላይ የሠራቸው አስደናቂ ነገሮች የተለዩ ናቸው፤ የቃና ዘገሊላውን ተአምር የተመለከትን እንደሆነ፤ የቢታንያ ድንጋዮችንም ያነሣን እንደሆነ በእነርሱ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያልተደረገ፣ ወደፊትም የማይደረግ ድንቅ ተአምር በነዚህ ድንጋዮች ውስጥ ሲደረግ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር ሊሠራ ከወደደ በድንጋይ ልብ ውስጥም ሥራ መሥራት እንደሚችል አሳየን፡፡ ቀድሞ በነቢያቱ ዘመን ዮናስን በባሕር ልብ ውስጥ አስገብቶ እንዲዘምር አደረገ፣ ኢያሱ ሥራውን እስኪጨርስ ፀሐይን አቆመ፣ በእኛም ዘመን የአቡነ ዘርዐ ቡሩክን የጸሎት መጻሕፍት እስከወደዱት ዘመን ድረስ በዐባይ ውኃ ጉያ ውስጥ ደብቆ አቆየ፡፡
ድንጋይ ሲፈልጡት ይፈለጣል፣ ሲረግጡት ይረገጣል እንጂ መች ቀድሶ ያውቃል? መች ወንጌል ሰብኮ ያውቃል? በቢታንያ የቆመው የድንጋይ ምሰሶ ግን ይሁዳ ንስሐ እንዲገባ ተግቶ የሰበከ ብቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡
የክርስቶስ ወደ ዓለም የመምጣት ምክንያት ይህ ነበር፡፡ እንደ ድንጋይ ኃጢአት ያፈዘዘው አዕምሯችንን ሕይወት እንዲኖረው ማድረግ! ድንጋይ ከውጪ እንጂ ከቤት ውስጥ ምን ሙያ አለው? እኛ ሁላችንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሙያ ታጥቶልን በውጭ እንድንጣል የተደረግን ሰዎች ነበርን፤ እንዲህ እንደ ድንጋይ ያለ ፈዛዛ ታሪክ በነበረን ወራት የተወለደው የማዕዘኑ ራስ ክርስቶስ በእኛ በድንጋዮች አድሮ ሥራ እንደሚሠራ ለማስረዳት ለልዩ ልዩ አገልግሎት ድንጋይን ሲጠቀም እንመለከተዋለን፡፡ የበረሃው ሰባኪ ቃለ ዓዋዲ ዮሐንስ እስራኤልን ሲገስጽ ‹‹እብለክሙ ከመ ይክል እግዚአብሔር እምዕላንቱ አዕባን አንሥኦ ውሉድ ለአብርሃም፤ እግዚአብሔር ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጅ ማሥነሳት እንደሚችል በእውነት እነግራችኋለሁ›› ማቴ3÷9 እያለ አብርሃም አባት አለን በማለት ብቻ ሊጸድቁ የሚያስቡትን ይዘልፋቸው ነበር፡፡ ሲጀመር ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን እንደ ሰማይ ከዋክብት ለሆኑት ልጆቹ ብቻ መች ሆነና! እንደ ባሕር አሸዋ በምድር ላይ ለተነጠፉት ልጆቹም ነው እንጂ፡፡
በእውነት ድንጋዮችን ልጅ አድርጎ ለአብርሃም የሚያስነሣበት ዘመን እንደደረሰ እንዲታወቅ በእነዚህ ድንጋዮች ቤቱን ሠራ፡፡ እኒህ ድንጋዮች እኮ የአሕዛብ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በከበሩ ድንጋዮች የተሠራ፣ በዋንዛ፣ በጽድ፣ በዝግባ የተዋበ፣ በወርቅ የተለበጠ ነበር 1ኛነገ. 6÷7፡፡ ለዚህ ግን እነዚህ ሁሉ ጌጣ ጌጦች አላስፈለጉትም፤ ድንጋዮች በቂ ነበሩና፡፡ ለክርስትና የጥንቶቹ ሊቃነ ካህናት ሌዋውያንና ፈሪሳውያን አያስፈልጉትም፤ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አሕዛብ ቤተ መቅደሱን ለመሙላት አላስቸገረም፡፡
ከድንጋይስ ምን አለበት የከበሩ ድንጋዮችን ቢመርጥ ኖሮ ሊባል ይቻል ይሆናል፤ ተራራው ላይ ሥራ አጥተው የተቀመጡትን ድንጋዮች ሥራ መስጠትኮ ነው የክርስቶስ ዓላማ፡፡ በማለዳም፣ በሦስት ሰዓትም፣ በቀትርም፣ እስከ ማታ ለወይኑ ቦታ ሠራተኞችን ሊስማማ በወጣ ጊዜ የተዋዋላቸው ሰዎች ሥራ ፈቶች አልነበሩምን? ማቴ20÷1 አሁንስ ለቤቱ የመረጣቸው ድንጋዮች በሰው ዘንድ ያልታሰቡ ቢሆኑ ምን ይገርማል፤ ለክርስቶስ ማደሪያነት ከቤተ አይሁድ ቀድሞ የሚገኝ አለ ተብሎ በሰው ዘንድ ታስቦ ያውቅ ነበር? አሕዛብን እግዚአብሔር ከውሻነት አውጥቶ ልጆች ያደርጋቸዋል ብሎ ማን አስቦ ኖሯል? እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ፤ ማቴ15÷26፡፡
ዳሩ ግን ሰው እንዳሰበው አልሆነም፤ በቃሉ የጠራቸውን ሦስቱን ድንጋዮች እንዲበቁ አደረጋቸው፤ እርሱ ይበቃል ያለው ይበቃል፤ የከለከለው ደግሞ ወርቅም ቢሆንም ተልጦ ይወድቃል፡፡ ሲፈቀድለት ጣዖት አጣኙ የሞዓብ ልጅ የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ተሾመ፤ ባይፈቀድለት የወርቁን ማዕጠንት በእጁ ይዞ የቃል ኪዳኑን ታቦት ሲያጥን የኖረው የአሮን ልጅ ተከለከለ፤ የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፡፡
የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ለምን በአሕዛብ ከተማ ተሠራ? አሕዛብ አማልክቶቻቸው ብዙ፣ አጋንንቶቻቸው ብዙ ናቸው፤ ቅዱስ ኤፍሬም እንደተናገረው ኃጢአት ብትበዛባቸው፤ ጸጋ እግዚአብሔር በዝታላቸው ብዙ ነገሮችን ከእስራኤል ቀድመው አግኝተዋል፡፡ ከአዳም ቀድሞ ገነት የገባው ፈያታዊ ዘይማን ከአሕዛብ ወገን ነበር፤ እስራኤል ሞትን ለፈረዱበት ጌታ ምንም እንኳን ማዳን ባይቻለውም ብቻውን የተከራከረለት ጲላጦስም ከአሕዛብ ወገን ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የቡራኬ ሥራም የጀመረው በአሕዛብ ሀገር በግብፅ ገዳማት በገዳመ አስቄጥስ ነው፡፡ ለአሕዛብ ምን ያልተደረገ ምን አለ? ይህን ታሪካዊ ቤተ መቅደስም በቤተ አይሁድ መካከል የሠራው አይደለም፤ በአሕዛብ መካከል እንጂ፡፡
ቤተ ክርስቲያን በምኩራብ ማኅፀን ውስጥ ተፀንሶ የቆየ ፅንስ እንጂ አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የፀነሰችው ምኩራበ አይሁድ ወልዳ መሳም ሳትችል ቀረች፤ ምክንያቱም እንደ ተወለደ በእስራኤል እንቢተኝነት ምክንያት ወደ አሕዛብ ስለገባ ነው፤ ሕንፃው በቅድስቲቷ ምድር ኢየሩሳሌም ሳይሆን ቀረ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በረከቱን ከእስራኤል እንዳራቀ፣ ክብራቸውን ወደ አሕዛብ እንደተነጠቀ ለማሳየት ነው ፡፡
አብርሃም በራዕይ የተመለከታቸው በምድራዊ አሸዋ የተመሰሉ ልጆቹ የሰማዩን ተስፋ፣ የቃል ኪዳኑን ምድር እንዲወርሱ የተወለዱለት በዚህ ጊዜ ነው፤ ዘፍ 22÷17፡፡ እንደ ባሕር አሸዋ የመንፈስ ቅዱስ ሙቀት የሌላቸው ቀዝቃዞች፣ በምድር እንጂ በሰማይ እንዳሉት ከዋክብት በላይ ለመኖር ያልታደሉ ብርሃን አልባ ድንጋዮች ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ከከበረ የአልማዝ ድንጋይ ይልቅ ያበራሉ፤ ድንጋይነታቸውን እንዳልናቀባቸው ለማስረዳትም በመካከላቸው የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ በድንጋይ ሠርቶ አሳየ፡፡ ለካ ድንጋይም አናጢዎች የናቁት ድንጋይም ለአገልግሎት ይፈለጋል ብለው እምነታቸው እንዲፈጸምላቸው ነው እንጂ ሌላ ምንድነው? ያልታሰቡትን ድንጋዮች ባንድ ቀን ለቤቱ እንዲበቁ አደረጋቸው::
በዚያውም ላይ እግዚአብሔር ሲፈቅድ የቀደሙት ኋለኞች፣ ኋለኞች ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ፤ ቀድመን ወንጌሉን ማወቃችን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛውን የሥልጣን ሥፍራ መያዛችን፣ በቤተ መቅደሱ ማደጋችን ብቻውን ያጸድቀናል የሚመስላቸው ብዙ ወገኖቻችን ናቸው:: በወንጌል ውስጥ ብዙ ኋለኞች ፊተኞች የሆኑ ሲሆን ብዙ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ሆነዋል፡፡
ቤተ መቅደሱ በእመቤታችን ስም ለምን ተሰየመ? የመጀመሪያው የመላዕክት የምስጋና መሥዋዕት በምድር ላይ የቀረበበት ቤተ መቅደስ ማኅፀነ ማርያም ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ “ድንግል አጽነነት ርዕሳ መንገለ ከርሣ ከመ ትስማ ቃለ እመላዕክት፤ ድንግል ከመላዕክት ቅዳሴን ልትሰማ ራሷን ወደ ሆዷ ዘንበል ታደርግ ነበር” በማለት የእመቤታችንን ማኅደረ ቅዳሴነት ይናገራል፤ ጌታችን የሚፀነስበት ወራት በደረሰ ጊዜስ እመቤታችን ከቤተ መቅደስ እንድትወጣ መደረጉ ለምን ይመስላችኋል፤ ቤተ መቅደስ በቤተ መቅደስ ውስጥ መኖር ስለሌለበት እኮ ነው፡፡ በዚያውም ላይ ያኛው ቤተ መቅደስ የሌቦች ዋሻ የወንበዶች መዳረሻ ሆኗል፤ ብቸኛዋ የእግዚአብሔር ከተማ ድንግል ከዚያኛው ጋር ምን ሕብረት አላትና በዚያ ሳለች ትፅነሰው?
ከአይሁድ ቤተ መቅደስ አውጥቶ ቤተ መቅደስ አደረጋት፤ በቤተ መቅደስ ትሰማው የነበረውን የመላእክት ዜማ አሁንም በሆዷ ውስጥ ትሰማው ነበር የምድራውያኑን ካህናት ቅዳሴ በሰማዩ ካህናት ቅዳሴ ለውጣዋለች:: ይህን ለመግለጽ ነው እንግዲህ ቤተ መቅደሱን ከሦስት ድንጋዮች ሠርቶ ሲጨርስ በሰኔ በሃያ አንደኛው ቀን ከሰማያት ወርዶ ቤቱን በእናቱ ስም ሰይሞ ቆርቦ እሷንም እነሱንም አቁርቧቸዋል::
አሕዛብ በሥላሴ ለማመናቸው ምክንያት የሆነች እርሷ ናት እንጅ ሌላ ማን አለ፤ ቅዱስ ኤፍሬም እንደ ተናገረው “ለሥላሴ ስግደትን የምታስተምርላቸው” ድንግል ማርያም ናት በኦሪትና በነቢያት ከተገለጠው ይልቅ የእግዚአብሔር ምሥጢር በዝቶ የተገለጠው ጌታ ከእመቤታችን ከተወለደ በኋላ ነውና፤ በዚያውስ ላይ አሕዛብን ማን ፈልጓቸው ያውቅ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታን በእቅፏ ይዛላቸው በከተሞቻቸው መካከል የተገኘች እርሷ እኮ ናት፡፡ ድንጋዮቹ አሕዛብ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲሆኑ እመቤታችን ምክንያታቸው ናት፤ ስለዚህ ቤቱ በእርሷ ስም ተሰየመ፡፡ አሁን ሁላችንም እንደ ሐዋርያው ቃል የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆናችን ምንም ጥርጥር የለንም 1ኛ ቆሮ3÷16፡፡ እግዚአብሔር “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም እርሱ ሥጋ ነውና” ዘፍ6÷3 ብሎ የማለውን መሀላ እንዲረሳና በሰው ላይ እንዲያድር ሰውም ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወደ መሆን እንዲያድግ ከእመቤታችን በስተቀር ሌላ ምን ምክንያት አለው፡፡
አምላካችን በድንጋይ ልብ ውስጥም ይመሰገናል ማለትም በአሕዛብም ዘንድ ቅዳሴው አይቋረጥበትም፤ ይህን ስጦታዋን በሰዎች መካከል ሲገልጽላት እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን በስሟ ሰይመላት፤ ከዚያም በኋላ የተነሡ መምህራን ይሄን መነሻ በማድረግ በዐራቱም መዐዝን ወንጌልን ሰብከው ብዙ የመታሰቢያ ቤቶችን በስሟ ከመሥራታቸውም በተጨማሪ ስሟን ለምዕመናን ስም እንዲሆን ፈቅደውላቸው እንዲጠሩበት አድርገዋል፡፡ በነቢይ ስለ እርሷ የተባለውም በዚህ ተፈጽሞላታል “ወይዘክሩ ስመኪ በኩሉ ትውልደ ትውልድ፤ ስምሽን ለልጅ ልጅ ያሳስቡልሻል” መዝ 44÷17፡፡