“በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ” (የዘወትር ጸሎት)
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ግንቦት ፲፭፤ ፳፻፲፭ ዓ.ም
በጉባኤ ኒቅያ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት“ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ…፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ…” እንዳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በአርባኛው ቀን በዚህ ዓለም የነበረውን የማዳኑን ሥራ ጨርሶ ወደ ላይ ማረጉንና በቀደመ ክብሩ በአብ ቀኝ መቀመጡን በማሰብ በዘወትር ጸሎታችንም እንዘክረዋለን፡፡
ዕርገቱ የማዳን ሥራውን የመፈጸሙ ምልክት ነው፡፡
አምላካችን “በዚህ አለ፤ በዚያ የለም” የሚባል አይደለም፡፡ የቦታ ውስንነት ኖሮበት “ወጣ፤ ወረደ” የሚባል አይደለም ። ‘ወረደ፣ ተወለደ’ ሲባል ሰው መሆኑን የትሕትና ሥራ መፈጸሙን ከመናገር ውጪ “ከዙፋኑ ተለየ” ማለት እንዳልሆነ ሁሉ “ዐረገ፤ ወጣ” ሲባልም ከሰማያዊው ዙፋኑ ተለይቶ ነበር ማለት አይደለም:: የማዳን ሥራውን መፈጸሙን ያመለክታል እንጂ:: ነገር ግን ዕርገቱ በሥጋ የተደረገውን ዕርገቱን ያመለክታል።
ዕርገቱ የአሸናፊነቱ ምልክት ነው፡፡
ይህም ዕርገት ቅዱስ ሥጋውን መቃበር ይዞ እንዳላስቀረው ሁሉ የምድር ስበትም ሆነ ቁጥጥር የማይዘው ለመሆኑ አስረጅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አምላካዊ ሥልጣኑን ያሳያል። “ዐረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፣ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው፤ ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም ወጣህ፤ ለሰው ልጆችም ጸጋህን ሰጠሃቸው”(እንዳለ ዳዊት ጌታችን በድል ማረጉን ይገልጣል፡፡(መዝ.፷፯፥፲፰)
ዕርገቱ የነፍሳችን ዕርገት ምልክት ነው፡፡
የእርሱ ዕርገትም ለነፍሣችን ዕርገት (ለዕርገተ መንግሥተ ሰማያት) አርአያ ሆኖናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታችንን በአየር እንቀበለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፡፡” (፩ኛተሰ.፬፥፲፯) ብሏል፡፡
ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው “ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ ለድንግል ዘፈትሐ ማሕፀና፤ ለደቂቀ እስራኤል ዘአውረደ መና፤ ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እም እደ ረበናት፤ ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፤በኅቱም ድንግልንና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደ፣ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረደ፣ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ፣ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ” ብሏል፡፡ ‘ዐረገ’ መባሉ የሌለበት ቦታ ኑሮ ካለበት ቦታ ወደ ሌለበት ቦታ ሔደ ማለት አይደለም፡፡ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ በባሕርይ አባቱ ቀኝ መቀመጡን፣ የማዳን ሥራውን መፈጸሙን፣ በሥጋ በክብር ማረጉንና እኛንም ልጆቹን እንደደመነፍሳዊ ፍጥረታት ፈርሰን፣ በስብሰን፣ አፈር ትቢያ ሆነን እንደማንቀር ዕርገተ ነፍስ እንዳለን ለመግለጽ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፤ “ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ።” (ቆላ.፫፥፩-፬)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ዐረገ ሲል በክብር ማረጉን፣ ልዕልናውን መግለጹ ነው፡፡ ደመና ክብሩ ልዕልናው ነውና። በደመና ዐረገ መባሉ ከእመቤታችን በነሣው ሥጋ ማረጉን ለመግለጽ ነው፡፡ ደመና ተብላ የተገለጠችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ናትና። “አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማይ ዝናም፤የዝናም ውኃ የታየብሽ የእውነት ደመና አንቺ ነሽ” እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም ከማርያም በነሣው ሥጋ ዐረገ ማለት ነው። ለመለኮትስ መውረድም መውጣትም የለበትምና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ደመናሰ ዘይቤ ይእቲኬ ማርያም እንተ ጾረቶ ዲበ ዘባና፤ ደመናስ የሚላት አምላክን በጀርባዋ የተሸከመችው ማርያም ናት” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ በደመና ዓምድ ዐረገ ሲል ከድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማይ ዐረገ ማለት ነው።
ዕርገቱ ዳግም የመምጣቱ ምልክት ነው፡፡
በልደቱና በትንሣኤው የተገኙትና ለሰው ልጆች መልካሙን ዜና ያበሠሩት ቅዱሳን መላእክት በዕርገቱም ተገኝተው ለዐሥራ አንዱ ሐዋርያት የዳግም ምጽአቱን ነገር አሳስበዋቸዋል፡፡ ቅዱስ ሉቃሰ ይህንን ሲገልጽ “እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” ብሏል። (ሐዋ.፩፥፲-፲፩) ቅዱስ ዮሐንስም እንደተናገረው እርሱ ዳግም ሲመጣ ሐዋርያቱ ብቻ ያይደለ የወጉት ጭምር ያዩታል በማለት ያስረዳል፡፡ (ራእ.፩፥፯)
የጌታችን ዕርገት በመርቀቅ /በርቀት/ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሐዋርያት እያዩት በመራቅ /በርኅቀት/ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በውንጌሉ “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው” በማለት ገልጾታል፡፡ (ሐዋ.፩፥፱) ይህም የሚያመለክተው በሚታይና በሚዳሰስ ሥጋ እንዳረገ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በቅዳሴው “በዚያች ሥጋ በመለኮት ኃይል ወደ ሰማይ ወደ ቀድሞ አኗኗሩ ዐረገ” ያለው ይህንን ለማመልከት ነው፡፡
ዕርገቱ አጽናኝ ና የእውነት የሆነውን መንፈስ ይልክላቸው ዘንድ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕርገቱ የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ “እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡” (ዮሐ.፲፮፡፯) ብሏል፡፡ እርሱ በአካል ስለሚለያቸው የኀዘን ሰሜት እንዳይሰማቸው የሚያጽናና መንፈስ ቅዱሱን እንደሚልክላቸው ከሞቱ አስቀድሞ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ብሎ ነግሯቸዋል። (ዮሐ.፲፬፥፮) ደቀ መዛሙርቱ ፈሪዎች ነበሩና ደፋር የሚያደርግ ፤ ረዳት”፣ “አጽናኝ”፣ ‘የሚያስተምር’፣ ‘የሚመሰክር’፣ ጥበብን የሚያናግር እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያን የእውነት መንፈስ ጥበብን የሚሰጥ መንፈስ ይልክላቸው ዘንድ ዐረገ፡፡ “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል” እንዳለ ያን የእውነት መንፈስ ልኮላቸው ሲቀበሉ በእነርሱ ላይ ያደረው መንፈስ ስለ ጌታችን ማዳን ስለ ባሕርይ አምላክነቱ በዓለም ሁሉ መሠከረ፡፡ እርሱ የእውነት መንፈስ ነውና በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራቸው ዘንድ፤ መጩ ዘመን ክፉ ነውና የሚመጣውን ይነግራቸው ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ሊልክላቸው በክብር ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ!
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት አይለየን!