በእንተ ጾም
በዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ
መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ጾም ‹‹ጾመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም መተው፣ መጠበቅ፣ መከልከል ማለት ነው፡፡ ጾም ከምግብ መከልከል ብቻ ሳይኾን ከክፉ ተግባር ዅሉ መቆጠብ ጭምር ነው፡፡ ሠለስቱ ምዕትም፡- ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾምስ በታወቀው ሰዓት፣ በታወቀው ዕለት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው›› በማለት የጾምን ትርጕም ያስረዳሉ /ፍትሐ ነገሥት፣ አንቀጽ ፲፭/፡፡
ጾም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን የታወቀ፣ በነቢያት የነበረ፣ በክርስቶስ የጸና፣ በሐዋርያት የተሰበከ እና የተረጋገጠ መንፈሳዊ ሕግ፤ ፈጣሪን መለመኛ መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይኾን ልዑል እግዚአብሔር የመሠረተው፣ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒችን ኢየሱስ ክርስቶስም እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጽድቅ የባሕርዩ የኾነ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያ ቤዛ ሊኾነን፣ እናንተም ብትጾሙ ብትጸልዩ አጋንንትን ድል ትነሳላችሁ ሲለን፣ ጾምን ለመባረክ ለመቀደስ፤ በመብል ምክንያት ስተን ስለ ነበር ስለ እኛ ኀጢአት እና በደል ሲል ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል፡፡
ጌታችን ሲጾም ዐርባውን መዓልት እና ሌሊት ሙሉ ምንም እኽል ውኃ አልቀመሰም፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም እንደዚሁ ጽላተ ሕጉን ከእግዚአብሔር ሲቀበል እኽል ውኃ አልቀመሰም ነበር፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ‹‹በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል፤ ከእኔ የበለጠም ያደርጋል›› ብሏልና፡፡ አባቶቻችን ጻድቃንም ከዐሥረኛው ማዕረግ (ከዊነ እሳት) ላይ ሲደርሱ በእርሱ መንፈስ (በመንፈስ ቅዱስ) ኃይል ታግዘው ከእኽል ውኃ ተከልክለው ይጾማሉ፡፡ ይህም በሥጋዊ ዓይን ሲመዘን ፈጽሞ የሚከብድ ነው፡፡ ሃይማኖት ከሳይንስና ከአእምሮ በላይ ነውና፡፡ በዚህም ሃይማኖት የሚቀበሉት እንጅ የሚጠራጠሩት የሚፈላሰፉት እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡
የጾም ሥርዓት
መጽሐፍ ‹‹ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርህማል፤›› /ዘዳ.፴፪፥፯/ እንዳለ ጾም እንዴት እንደሚጾም አባቶችን መጠየቅ እና የአባቶችን ፈለግ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ‹‹ቤተ ክርስቲያን እናቱ ያልኾነች ሰው እግዚአብሔር አባቱ አይኾነውም›› በማለት እንደ ተናገረው ያለ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን፤ ያለ እግዚአብሔር ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣ መጸለይ፣ ሥጋውን ደሙን መቀበል መገስገስ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ለክርስቲያን›› እንዲሉ አበው፡፡ በጾም ወቅት ደግሞ ይህንን ተግባር ይበልጥ ማሳደግ ይገባል፡፡
በጾም ወቅት የሥጋ አለቃ ነፍስ ናት፡፡ ነፍስ ፈላጭ፣ ቆራጭ፣ አዛዥ ናት፡፡ ሰው መልካም ሥራ ከሠራ በነፍስ በሥጋው ይቀደሳል፤ ገነት (መንግሥተ ሰማያትን) ይወርሳል፡፡ ክፉ ከሠራ ደግሞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያጣል፤ ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይወርዳል፡፡ ሰው ኀጢአተኛ ነው ሲባል ፈቃደ ሥጋው ሠልጥኖበታል ማለት ነው፡፡ ጻድቅ ነው ሲባል ደግሞ ፈቃደ ሥጋውን አሸንፏል (ለፈቃደ ነፍሱ እንዲገዛ አድርጓል) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሲቀደስም፣ ሲረክስም የሚኖረው በፈቃደ ሥጋ እና ፈቃደ ነፍስ መካከል ባለው የአሸናፊነትና ተሸናፊነት ትግል ነው፡፡
ጾም ራስን ዝቅ የማድረግ፣ የጸሎት እና የንስሐ ጊዜ እንደኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ /ዕዝ. ፰፥፳፩፤ ነህ. ፩፥፬፤ ዳን.፱፥፫/፡፡ ስለዚህም ራሳችንን ዝቅ በማድረግ (በትሕትና) መጾም ይገባናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በምዕራፍ ፶፰ ቍጥር ፭ ላይ ‹‹እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን?›› ይላል፡፡ እንግጫ ማለት ባሕር ውስጥ የሚበቅል ሣር ነው፡፡ በቀዳም ሥዑር ካህናት ‹‹ጌታ ተመረመረ፤ ዲያብሎስ ታሰረ፤›› እያሉ ለደስታ መግለጫ የሚሰጡት እና ራስ ላይ የሚታሰር ለምለም ሣር ነው፡፡ እንግጫ (ግጫ – በአንዳንድ አካባቢዎች) ሲያድግ ራሱን ዝቅ ያደርጋል፤ እያደገ ሲሔድ ራሱን ይደፋል (ዝቅ ያደርጋል)፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ ራሳችሁን እንደ እንግጫ (ግጫ) ዝቅ አድርጉ ማለቱ በጾም ወቅት ‹‹እንደዚህ ነው የምጾመው፤ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ነው የምጾመው›› እያልን ውዳሴ ከንቱን መሻት የለብንም ሲል ነው፡፡ ሰው እያወቀ ሲሔድ ራሱን ይደብቃል እንጅ ራሱን ከፍ ከፍ አያደርግም፡፡ የጾም ወቅት ትሕትናን ገንዘብ የምናደርግበትና ይበልጥ የምናሳድግበት ወቅት ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፈተናን ችሎ በትዕግሥት የሚያሳልፍ፣ እየሰማ የሚተው መኾን አለበት፡፡ ነቢዩ ዕዝራም በመጽሐፈ ዕዝራ ፰፥፳፩ ላይ ‹‹በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛ እና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ›› በማለት ራስን ዝቅ በማድረግ ለአምላክ ፈቃድ መገዛት እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡
የጾም ሰዓት
ስለ ጾም ሲነገር የጾም ሰዓትም አብሮ ይነሣል፡፡ በዘፈቀደ ሳይኾን በሰዓት የተወሰነ ጾም መጾም እንደሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ‹‹የእስራኤልም ልጆች ዅሉ ሕዝቡም ዅሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፡፡ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፡፡ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መሳ.፳፥፳፮/፡፡ የጾም ሰዓትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ተዘረዝሯል፡፡ ሠለስቱ ምዕት ‹‹ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ›› እንደዚሁም ‹‹በጾም ምክንያት ጠብ ክርክር ቢኾን መጾም ይገባል፤ ከመብላት መጾም ይሻላልና፤›› በማለት ከተወሰነው ሰዓት በላይ አብልጦ መጾም እንደሚቻልና ከመብል ይልቅ ለጾም ማድላት እንደሚገባ ነግረውናል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቍጥር ፭፻፹፬/፡፡
ሰው ይረባኛል ይጠቅመኛል ብሎ አብዝቶ ከመጾሙ የተነሣ መላእክትን፣ አባ እንጦንስና አባ መቃርስን እንደሚመስል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ አምላካችን ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል›› የሚል ቃል ኪዳን የሰጣቸው አባቶቻችን መምህራን የምንጾማቸውን አጽዋማት እና የምንጾምበትን የሰዓት ጊዜ ወስነውልናል፡፡ በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ አድሮ ሥርዓቱን የሠራልን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ምክንያቱም ካለ እርሱ ፈቃድ እጽፍ፣ እተረጕም ቢሉ አይቻልምና፡፡ ጌታችን በወንጌሉ ‹‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ዅሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፤ ትእዛዜን የሚያከብር እንጅ፤›› እንዳለ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመርተው አባቶች የደነገጉትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማክበር እና መጠበቅ አለብን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በየጥቂቱ ማደግ ይገባል›› እንዳለው ዅሉንም ነገር በአቅም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጾምን ስንጾምም አቅምን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ለመጾም ስንወስን ጽናታችንና ልምዳችንን ግምት ውስጥ በማስገባት መኾን ይኖርበታል፡፡ ካለበለዚያ ጥብዓት ጎድሎን፣ ትዕግሥት አንሶን እግዚአብሔርን ልናማርር እንችላለን፡፡ ጾመን የማናውቅ ሰዎች በስሜት ተነሣሥተን በአንድ ጊዜ ቀኑን ሙሉ መጾም አለብን ማለት የለብንም፡፡ ክርስትና የስሜት ጉዞ አይደለምና፡፡ እስከ ሰባት ሰዓት ጹሞ የማያውቅ ክርስቲያን እስከ ዐሥራ ሦስት ሊጾም አይችልም፡፡ በስሜት የሚደረግ ማንኛውም ነገር ፍጻሜ አይኖረውምና ስንጾም አቅማችንን ማወቅ ተገቢ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ይጠቅማል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እጅግም ድሀ አታድርገኝ፤ እጅግም ሀብት አትስጠኝ›› ይላል፡፡ እኛም ስንጾምም ስንለምንም በአቅማችን መኾን አለበት፡፡ ስለጾምና የሰዓት ገደብ ሲነገር ማስተዋል የሚገባን ቁም ነገር ከእኽል ውኃ ከመከልከል አኳያ ጾም በቍጥርና በጊዜ የተወሰነ ይኹን እንጂ ከክፉ ተግባር ከመራቅ አንጻር ክርስቲያን እስኪሞት ድረስ ጾመኛ ነው፡፡ ምንጊዜም ቢኾን ከክፉ ነገር፣ ከኀጢአት ዅሉ መጾም (መከልከል) ይጠበቅበታልና፡፡ ዅላችንም ይህን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ ላይ ግን አንድ ሰው በመጾሙ ብቻ አምላክን ያስደስተዋል ማለት አይደለም፡፡ መጾም ያለበትም ለሥራው ኀጢአት ማካካሻ አይደለም፡፡ የኀጢአት ስርየት የሚገኘው ንስሐ በመግባት እንጅ በመጾም ብቻ አይደለምና፡፡ ሌሎችንም የትሩፋት ምግባራት መሥራት ስንችል ነው ኀጢአታችን የሚሰርይልን፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ፣ ንስሐ በመግባት፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት ከጾምን ኀጢአታችን ይሰረይልናል ማለት ነው ‹‹በጾም ወበጸሎት ይሰረይ ኵሉ ኃጢአት፤ በጾም በጸሎት ኀጢአት ዅሉ ይደመሰሳል፤›› እንዲሉ ሊቃውንት፡፡
ጾም እና ፈተና
‹‹ቤተ ክርስቲያን እየሔድኹ፣ እየጾምኹ፣ እየጸለይኹ፣ እፈተናለሁ፤ ለምንድን ነው?›› የምንል ብዙዎች ነን፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስሔድ ፈተና እየበዛብኝ ነው በማለት ከቤቱ የምንርቅም ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ብዙ ጊዜ ከመልካም ነገር በስተጀርባ ፈተና አለ፡፡ ከጌታችን የምንማረው ሕይወትም ይኸን ነው፡፡ የማይሾሙት ንጉሥ፣ የማያበድሩት ባለጠጋ፣ ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉን የሚገዛ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ጾመ፤ ተራበ፤ በሰይጣን ተፈተነ፡፡ በእኛ ላይም ብዙ ፈተና ቢመጣብን ለምን ያስደንቃል? ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፤ ለስድብም ኾነብኝ›› ይላል /መዝ.፷፱፥፲/፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የሚበረታ ሰው ይሰደዳል፤ ይሸነገላል፤ ፈተና ይበዛበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው›› በማለት ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳዘዙን ለሚያሳድዱን መጾም መጸለይ ይኖርብናል /ዲድስቅልያ ፩፥፭/፡፡ ክርስትና ሲገፉ መግፋት አይደለምና፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ በርናባስ ‹‹ከቤተ ክርስቲያንን የተጠጋ እንኳን ሰው ዛፉ ይለመልማል›› ይሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አባታችን፣ ቤተ ክርስቲያን እናታችን ብሎ የሚኖር ሰው ፈተና በየጊዜው ቢገጥመውም መጨረሻው ያማረ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ተከትሎ የወደቀ የለምና፡፡
የጾም ጥቅም
በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው ጾም የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፤
- የሥጋን ምኞት ያጠፋል፤
- የነፍስ ቍስልን ያደርቃል፤
- ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ያስገዛል /ፍት.ነገ.፲፭፥፭፻፷፬/፤
- መላእክትን መስሎ ለመኖር ያስችላል፤
- ልዩ ልዩ መከራን ያቃልላል፤
- አጋንንትን ያስወጣል /ኢያ.፯፥፮-፱/፤
- ሰማያዊ ክብር እና ጸጋን ያስገኛል /ኛነገ.፲፱፥፰/፤
- በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር የሚያስችል ምግባርን ያሠራል /ሉቃ.፮፥፳፩/፤
- ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እና ምሕረትን ለማግኘት ይረዳል፤
- አጋንንትና ጠላትን ድል ለማድረግ ያግዛል /ማቴ.፬፥፲፩፤ መጽሐፈ አስቴር ምዕ.፯/፤
- ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ይረዳል /፩ኛነገ.፲፱፥፩/፤
- ከእግዚአብሔር ቍጣ ለመዳን ያስችላል /ዮናስ ፫፥፩/፤
- የተደበቀ ምሥጢርን ይገልጣል /ዳን.፲፥፲፬/፤
- ጸጥታን እና ርጋታን ያስተምራል፤
- ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋል፤
- ሕይወትን ያድሳል፤
- መንፈሳዊ ኃይልን ያሰጣል /፩ኛሳሙ.፯፥፭/፤ጥበብን ይገልጣል /ዕዝራ ፯፥፮፤ ዳን.፱፥፪/፤
- ክህደት ጥርጥርን በማጥፋት እምነትን ለማጠንከር ይረዳል፤
- ዕድሜን ያረዝማል፤
- ትዕግሥትን ያስተምራል፤
- በመላእክት ጠባቂነት ለመኖር ያስችላል /ዘፀ.፲፬፥፲፱. ሐዋ.፲፥፫/፡፡
ጾም ከሚያስገኘው መንሳዊ ጸጋና በረከት ባሻገር በርካታ ሥጋውያን ጥቅሞችም እንዳሉት በጾም ዙሪያ የተደረጉ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በጥናቶቹ መሠረትም ጾም፡-
- የደምና የስኳር መጠንን ይቆጣጠራል፤
- የአንጎል እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲኾን ያደርጋል፤
- የስብ ክምችትን ይቀንሳል፤
- የምግብ መፍጨት ስርዓታችንን ያስተካክላል፤
- የካንሰር ሕዋሳት ዕድገትን ይከላከላል፤
- የጠራ የሰውነት ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፤
- በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል፡፡
በአጠቃላይ ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ አይደለም፤ የመሠረተውም ራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን አዳምና ሔዋንን ‹‹ዕፀ በለስን አትብሉ›› ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ የጾም ሕግን ሠርቶልናል፡፡ በዚህም ጾም የመጀመሪያ ትእዛዝ ናት እንላለን፡፡ አዳም በመብል ምክንያት ሕገ እግዚአብሔርን በመጣሱ ነው ከክብሩ የወረደው፡፡ እኛም ብንጾም እንጠቀማለን፤ ባንጾም ደግሞ በረከትን እናጣለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሥጋዬ ቅቤ በማጣት ከሳ፤›› /መዝ.፻፱፥፳፬/፤ ነቢዩ ዳንኤልም ‹‹ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ ሥጋ እና ጠጅም በአፌ አልገባም፤›› /ዳን.፲፥፫/ ሲሉ እንደ ተናገሩት፣ በጾም ወቅት ከጥሉላት ምግቦች መከልከል አለብን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም፤›› ሲል ማስተማሩም ከመብል ተከልክለን መጾማችን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንገድ መኾኑን ያመላክታል /ሮሜ.፲፬፥፯፤ ፩ኛቆሮ.፰፥፰/፡፡ አበው ‹‹ጾም ገድፎ የወፈረ በዓል ሽሮ የከበረ የለም›› እንደሚሉት በጾም ወቅት በልተን ከምናገኘው ጥቅም ይልቅ ጾመን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንቀበለው በረከት ይበልጣል፡፡
ጾም ቍስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ዅሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ ለጽሙዳን ክብራቸው፣ ለደናግል የንጽሕና ጌጣቸው፣ የጸሎት እናት፣ የዕንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ዅሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት /ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕራፍ ፮/፡፡ እንደዚሁም ጾም ዕድሜን ያረዝማል፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ ረጅም ዕድሜ የኖሩ አባቶቻችን ሕይወትም ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ቄርሎስ ዘአንኮራይት ፻፰፤ ቅዱስ እንጦንስ ፻፭፤ ቅዱስ መቃርስ ዘእስክንድርያ ፻ ዓመት በምድር ላይ ቆይተዋል፡፡ ምእመናንም ጾምን ስንጾም አምላካችን ዕድሜአችንን ለንስሐ ያረዝምልናል፡፡ በጾም ወቅት መጸለይ፣ መመጽወት፣ መስገድ በጾም የምናገኘውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ‹‹ስለ ኀጢአቱ እንደሚጾም፣ እንደሚጸልይ ሰው ኹኑ›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡
አንድ ክርስቲያን ጾም አልጾምም የማለት ሃይማኖታዊ ሥልጣን የለውም፡፡ ምክንያቱም ጾም ለዅሉም ክርስቲያን ሕግ ኾኖ የተሰጠ የአምላክ ትእዛዝ ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ‹‹ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤›› በማለት መጾም፣ መጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታ መኾኑን ነግሮናል /ኢዩ.፪፥፲፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም›› ሲል ምክንያት እየፈጠርን ከመንፈሳዊ ሕይወትና ከአገልግሎት ወደ ኋላ ማለት እንደሌለብን አስተምሮናል /፪ኛቆሮ.፮፥፫/፡፡ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ‹‹በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ለማለት ይከብዳል›› ይላሉ፡፡ እንደሚታወቀው በዐቢይ ጾም ከበሮ እና ጸናጽል ዅሉ ይጾማሉ፡፡ ይኸውም የጾሙን ትልቅነት ያረጋግጥልናል፡፡ የዜማ መሣሪያዎች ዐቢይ ጾምን ከጾሙ ለባዊነት ያለን የሰው ልጆችስ (ክርስቲያኖች) ለጾሙ ምን ያህል ዋጋ እንሰጥ ይኾን? ዅላችንም ጾሙን በደስታና በፍቅር ጾመን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡