በእንተ ስምዐ ለማርያም

(ተሜ አንድ ዕለት)

አቤል ቤዛ

ዓለም ከተፈጠረበት ረቂቅ ብልሃት ይልቅ

ሰውን ወርዶ ላዳነበት ለምሥጢሩ ስንደነቅ

ከሰማያት ከፍ ብላ ከተገኘች ውቧ ሰማይ

መጽሐፉም ይነግረናል ወደ አንዲቷ ምሥራቅ እንድናይ

ኢሳይያስ በትንቢቱ ያነሳትን አንዲቷን ዘር

መዳኛ ትንሽ ደመና በመሆኗ ለእኛ ስትቀር

እንደተዘጋች ነበረች ለዘለዓለም ህትምት ብሎ

ሕዝቅኤል ተነበየላት በቤተ መቅደስ መስሎ

እርሷስ አማናዊቷ መቅደስ ናት የምትወደድ

እንጀራን ያስገኘችልን መሶብ ወላዲተ ወልድ

የፍጥረትን ችግር የማትወድ ርኀብ ስደት መከራ

ርኅርኅተ ሕሊና ለፍጥረት ሁሉ ‘ምትራራ

የአዳምን እንባ ያበሰች የሔዋን የልቧ ደስታ

የናሆም መድኃኒቱ ናት፤ አዛኝት ከፍጥረቷ

ለኔም ሸክሜን አቅላይ የልቤ ድጋፍ መጽናኛ

በሰው ፊት ሞገስ የምትሆን ከኃጢአት ሥቃይ መዳኛ

ስሟ ከአፌ ሲወጣ የፍጥረት ልቡ ይራራል

በእመ አምላክ ስም ተለምኖ ማን እምቢ ማለት ይችላል፡፡

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ዛሬ በፍልሰታዋ በአዛኝት የጾም ወራት

ልመናዬ አይደለም ፍርፋሪ ኩርማን ዱቄት

በደብረ ታቦሩ በዓል በተገለጸበት ምሥጢር

የዕለት ጉርሴን አልጠይቅም ቆሜ በደጅዎ በር

ልለምን . . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ክፉ ሥራን ይተው ሰውነት የሁሉ ጌጥ

ያለዎትን ያካፍሉ አይረሳዎት እርሱ ሲሰጥ

ደግነት ልብስዎ ይሁን ለአዳም ልጅ በሙሉ

ውኃና እሳት ቢሆንም የፍጥረት አመሉ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

የአንገትዎን ማህተብ የልጅነት አደራ

የክርስትናዎትን ቃልኪዳን አይሁንብዎ ኪሳራ

መስቀሉን በትከሻ ሕጉን ከልብዎ ያኑሩ

መታመኛ መከታ ቃሉን አብለው አይሻሩ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

በደብረ ታቦር እንደበራው የመለኮት ድንቅ ብርሃን

እስቲ ይትጉ በትሩፋት ፍጻሜው ድል እንዲሆን

ቅዱሳኑን አድርገው የአሣር ቀን መሸሸጊያ

ይታትሩ ለበጎ ሥራ ለመንግሥቱ ቤት መተያያ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ችላ አይበሉ ሠናይ ሥራን በአብሮነት ሲኖሩ

ድሆችን አይርሱ የሰማዩን ቀድመው ይሥሩ

ማንም አልታየም ተቸግሮ ለድሃ በመስጠቱ

ብድር ነው የሚመለስ ተቀማጭ ለሰማይ ቤቱ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

የአዲሱን ዓለም እስራት ምዕራባዊ እሳቤ

ግለኝነት ጭካኔ  የራስ አምልኮ ውቃቤ

ያምልጡ ከተሰሎንቄ ከብልጭልጭ ከንቱ ዓለም

ዳሩ ሞት ነው መሐሉ ነጻነት ቢመስልዎትም

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ከክርስቶስ አምላክነት ከድንግል እናቱ ምልጃ

ከቅዱሳኑ በረከት ከአምላክ ቃል መፋረጃ

ከቀናችው መንገድ ሊያስወጣዎት ከሚመጣ

ያድኑ ራስዎን በእውነት ከመናፍቃን ቅሰጣ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ዘር አንድ ነው የለውም ሁለት ሦስት

አዳም ነው መነሻው ለህልቆ መሳፍርት ፍጥረት

መጨካከን መገዳደል ተከፋፍሎ በነገድ

ለቃየንም አልሆነውም  የሄደበት የሞት መንገድ

. . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

የእጅዎን ዛሬ አልሻም ገጸ በረከት አምሃ

ምስጋናዬን አላስቀርም ባያጠጡኝ ንጹሕ ውኃ

እዝነ ልቡናዎ ከደረሰ የዛሬ ጩኸት ልመና

እግዚአብሔር ይስጥልኝ ያግኙ የሰማዩን መና

የደብረ ታቦሩ ጌታ ይግለጥልዎት ምሥጢሩን

ወርቅ ለብሰው ይዋሉ የነዳይ ምርቃቱን

ከመንግሥቱ ያድርስዎ በምሕረት ካጌጠው

ይስጥዎት ጥብዓቱን በቅዱሳን ላይ ካደረው

አብዬ ይንገሡልኝ ከቅዱስ ቊርባኑ ዙፋን

እምዬም ይሰብስቡ የንስሐ ፍሬዎትን

በሉ ደህና ክረሙ የ አዲስ ዓመት ሰው ይበለን

እንደቀኑ አዲስነት ቅዱስ ሕይወት ያድለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!