በእሾህ መካከል የበቀለች ጽጌሬዳ
ሰኔ ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
የውበት ልኬት በእርሷ እንደሆነ እስኪሰማኝ ድረስ ማረከችኝ፡፡ የምድር ጌጥ በመሆኗም ብዙዎች ተደነቁባት፤ ውበቷን በቃላት መግለጽ እስኪያቅታቸው ድረስ ተገረሙባት፡፡ ተፈጥሮዋና ውስጠቷ ዕፁብ የሆነው ጽጌሬዳ በማይነገረው ድንቅ ፍጥረቷ የተማረኩ ብዙኃኑ ሊቀርቧት፣ሊነኳት ወይም ሊያበላሿት አልያም ሊቀጥፏት ይከጅላሉ፡፡ የቀለሟ ድምቀትና መዓዛዋ ከሩቅ እየጠራቸው ሊወስዷት ፈለጉ፡፡አላገኛት ሲሉም በዙሪያዋ እንደሚበቅሉ እሾሆች ከበቧት፤ እርሷን ግን ማግኘት አልቻሉም፤ በጸና ግንብ፣ በማይደፈር ቅጽር ታጥራለችና፡፡
ፈክታ ስትታይ እንዳማረችው እንቡጥ አበባ መሆን ምንኛ ያስደንቃል? ለሚመለከታት ጊዜዋን ጠብቃ፣ አፍርታና አብባ ውበትን የምትለግስ፣ የምትማርክና ጥዑም መዓዛን የምታውድ ስትሆን በዘመኗ መሪር ሥቃይን ያሳለፈች እንደሆነች ማን ባወቀላት! በዕንቡጥነት ጊዜዋ እንዳታብብ፣ በመፍካቷ ወራት ጣፋጭ ፍሬ እንዳታፈራ እና በመልካም እርግና እንዳታልፍ እክል የሆኑባት እሾሆች መከራ የሚያጸኑባት ለምን ይሆን? ውበቷን ማድነቅ ሽተው? ወይስ ተመቅኝተው? ወይስ ቀጥፈው ሊጥሏት? የውስጣቸውን ሐሳብ ማን ያውቃል? እኔ ግን የውበቷን ምሥጢር ለማወቅ ተመኘሁ፤ ጥንካሬዋን አደነኩ፤ በትዕግሥቷም ተገረምኩ፤ ጣፋጭ ማንነቷን ቀምሼና አጣጥሜ ለማወቅም ወሰንኩ፤ በእሾህ መካከል የበቀለችው ጽጌሬዳ እውነተኛዋን ክርስቲያን መስላኛለችና፡፡
ፍቅር አገብሮት፣ ሞት ሕልፈት የሌለበት አምላክ በመስቀሉ ሲሰቀል፣ ራቁቱን በቀራንዮ አደባባይ አይታ ያለቀሰች፣ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር የተቀበለልንን መከራ ተረድታ ያዘነች፣ በመስቀሉ ላይ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠንን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያወቀችና ያመነች እውነተኛዋ ክርስቲያን በእሾህ መካከል እንደበቀለችው ጽጌሬዳ በመከራና ፈተና ውስጥ የምትኖር እንደሆነች አስተዋልኩ፡፡ ያንን ሁሉ ችላም በትሕትና ሁሉን የሚችል፣ ምሉእ በኩለኤ የሆነ፣ ለዘለዓለም እየተመሰገነ የሚኖር አምላኳን ዘወትር የምታመሰግን ናት፤ አንገቷን ዘንበል ቀለስ፣ ራሷን ጎንበስ አድርጋ ለእርሱ እየሰገደች ትኖራለች፡፡
ጌታ ባሕርዩውን ዝቅ አድርጎ፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ እንደ ሕፃናት ድሆ፣ እንደ ሰው በእግር ተመላልሶ፣ እንደ ልጅ ለክብርት እናቱ ታዝዞ፣ ጊዜው ሲደርስም መከራና ሥቃይ ተቀብሎ ሕይወቱን የሰጠን ለእርሷ ሲል መሆኑን አውቃም በውስጧ ታነባለች፤ ትተክዛለች፤ ገጿ ግን ሁል ጊዜ እንዳበበ ስለሆነ የውስጧን የሚያውቅ የለም፡፡
በፍቅሩ ምክንያት መከራ መስቀሉን የተሸከመችው ክርስቲያኗ በምቀኞቿ ተከብባ እንዳለችው በእሾህ መካከል የበቀለችውን ጽጌሬዳ አወሳችኝ፡፡ የፍቅሩን ጥልቀት፣ የቸርነቱንና የምሕረቱን ብዛት አውቃ፣ በእንባ እየታጠበች፣ ስለ እውነት ስትል ሥቃይዋን ደብቃ፣ ዘወትር አብባና ተውባ እንደምትታየው ጽጌሬዳና እጅግ እንደትመስጠው አበባ ውብ እንደሆነች አወኩኝ፤ ድብቁ ውበቷ የመነጨውም ውብና መልካም አድርጎ ከተሠራው ማንነቷ ላይ ነውና፡፡
በእሾህ መካከል የበቀለችው ጽጌሬዳ በመከራ ውስጥ እንኳን ሆና ፍጹም ፍቅር ለሌሎች ትለግሳለች፤ ከክበቧ ሲቀርቡ ተቀብላ ሳታዳላ ሁሉንም በትሕትና ታስተናግዳቸዋለች፤ የትኛውንም ዓይነት ክፉም ይሁን ጥሩ ሐሳብና ምኞት ቢኖራቸውም ሳትፈራ አቅርባ ሰላሟን፣ በጎነቷንና መልካምነቷን ታካፍላቸዋለች፤ ይህን ሁሉ ከጌታዋ ተምራለችና፡፡ በመልካም መስኖ፣ በለመለመ መስክ ላይ ተክሎ፣ ምግቧንና መጠጧን አዘጋጅቶ እየመገበ የሚያኖራትን መልካሙ ጌታዋን እያከበረችም ስታገለግለው ትኖራለች፡፡
በእሾህ መካከል የበቀለችው ጽጌሬዳ በዕንቡጥነት ወራቷ በውበቷ ሳትመጻደቅና ሳትታለል፣ ከትምክህት ርቃ፣ የዚህን ዓለም ነገር ንቃ፣ ትታ፣ ተግታና ለጌታዋ ተገዝታ የኖረች እንደሆነች እርሱ ብቻ ያውቅላታል፡፡ ከራሷ ጥቅም ይልቅ ስለ እርሱ ፍቅር ስትል በዙሪያዋ ከበው በከንቱ ውዳሴ የሚያሞካሿትን ትታ፣ “ምቶትና ድሎት ወዳለበት እንውሰድሽ” እያሉ ከተተከለችበት እሾህ ላይ ነቅለው ሊወስዷት የሚጥሩትን ሁሉ አሳፍራና ድል ነሥታ በመከራ ውስጥ መኖርን እንደ መረጠች ታሳያቸዋለች፤ እንደ እርሷም ይሆኑ ዘንድ በውበቷ፣ በጥዑም መዓዛዋ፣ በትሕትናዋ፣ በትዕግሥቷና በመልካምነቷ ትጋብዛቸዋለች፡፡
በዙሪያዋ ከበዋት ያሉት እሾሆች እንዳትኖር ወይም እንዳትሞት አድርገው ቢያሠቃይዋትም ከጌታዋ መለየትን ያህል ቁስልና ሕመም ለእርሷ እንደሌለ አበክራ ትነግራቸዋለች፡፡ እሾሆቹን እርሷና ጌታዋ ብቻም ስለሚያውቋቸውም ማንም በመከራዋ ጊዜ አይደርስላትም፡፡ እንዲያውም በውበቷ የተነሣ በምቾት ላይ እንደሆነች በማሰብ በቅናትና በምቀኝነት ተነሣሥተው ዕድሜዋን ለማሳጠር ሲጥሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሌላ ዓይነት እሾሆች ይሆኑባትና ሥቃይዋ ይበዛል፡፡ እነዚህን በመሰሉ እሾሆች ተከብቦ መኖር ምንኛ ሥቃይ ነው?
በብቸኝነትና በሰቀቀን የተሞላው ኑሮዋ ላወቀላት እጅጉን ያሳዝናል፤ በእሾህ መካከል የበቀለችው ጽጌሬዳ ግን “መከራ በዛብኝ፤ ሥቃዬን መቋቋም አልቻልኩም፤ ሰለቸኝ፤ ደከመኝ ወይም መረረኝ” ሳትል ፈጣሪዋ የቸራትን ውበት መለገሥ አታቋርጥም፤ ይህም የውስጧ ውበት የትሕትናዋ፣ የትዕግሥቷ፣ የበጎነቷና የመልካምነቷ ኅብር በገጿ ፍንትው ብሎ ስለሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ድንቅ የፈጣሪ ሥራ ከልብ ከመደነቅና ከማክበር ይልቅ ብዙዎቹ እንደ ከበቧት እሾሆች በክፋታቸው፣ በተንኮላቸውና በመርዛቸው ሲያሠቃዩአት መኖርንና ጨርሰው ማጥፋትን የሚሹ ናቸው፤ በእሾህ መካከል የበቀለችው ጽጌሬዳ ግን በትዕግሥት ሁሉን ታልፋለች፡፡
የዕንቡጥነት ወራቷ ሲያልፍ እንደምታብብና እንደምታፈራ ከዚያም ደግሞ በእርግናዋ ወራት ፈጣሪዋ መልካም ዕረፍትን እንደሚሰጣት በማመን በተስፋ ትኖራለች፡፡ ምንም እንኳን እርግናዋ ሲደርስ፣ ውበቷ ሲጠወልግ፣ ሲረግፍና ሁሉም ሲርቃት ብታዝንም በመጨረሻ ወደ ፈጠራት እንደምትጓዝና ወደ ፍጹም ደስታ እንደምትገባ በማሰብ ፍጹም ሐሴትን ታደርጋለች፡፡
በእሾህ መካከል የበቀልሽው ጽጌሬዳ ሆይ፥ አቤቱ ውበትሽ ድንቅ ነው! አንቺንም የፈጠረ ጌታ ግሩም ነው!
ምንጭ፡- መጽሐፈ ድጓ ዘጽጌ፣ መጽሐፈ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ መጽሐፈ ማኅሌተ ጽጌ