‹‹በንስሓ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ›› (ሕዝ.፲፰፥፴፪)
መጽሐፍ ቅዱስ የቆሬን የዳታንና የአቤሮንን ዐመፅ እንዲሁም ይህንን ዐመፅ ተከትሎ ከእግዚአብሔር ፊት የወጣውን ቁጣና መቅሠፍት እንዲህ ሲል ያስታውሰናል፡፡
ቆሬና የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን እግዚአብሔር ባከበራቸው ካህናት በሙሴና በአሮን ላይ በማጕረምረም ለእነርሱ ባልተገባ የክህነት አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በዐመፅ ተነሡ፡፡ በእስራኤላውያንም መካከል ዝናቸው የተሰማና በምክር የተመረጡ ሁለት መቶ ኀምሳ የማኅበር አለቆችን ለዐመፃቸው ተባባሪዎች አደረጓቸው፡፡
እግዚአብሔር ለቅድስና አገልግሎትና ሕዝብን ለመምራት የመረጣቸውን ሙሴንና አሮንንም ‹‹እናንተ ይበቃችኋል፤ ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና እግዚአብሔርን ማገልገል ይችላሉ›› አሏቸው፡፡ (ዘኁ.፲፮፥፫)
ዐመፀኞቹ ቆሬ ዳታንና አቤሮን ካህናቱን ሙሴንና አሮንን ከቤተ መቅደሱ በጉልበት በማስወጣት እነርሱ የቅዱሳኑን ቦታ ተክተው ማገልገል እንደሚገባቸው ተናገሩ፡፡ ከዚያም ጥናቸውን ወስደው እሳት አደረጉበት ዕጣንም ጨመሩበት፤ ከእግዚአብሔር ባለሟሎች ከሙሴና ከአሮን ጐንም እኩል በእግዚአብሔር ፊት ይቆሙ ዘንድ ማዕጠንቶቻቸውን ይዘው ተሰበሰቡ፡፡ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጣ፡፡ ሙሴንና አሮንንም ‹‹ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ እናንተ ከዚህ ማኅበር ፈቀቅ በሉ›› አላቸው፡፡ በዚህ ቀን በቆሬ ምክንያት ከሞቱት በተጨማሪ በመቅሠፍቱ የሞቱት ፲፪ ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፡፡ ዘኁ.፲፮፥፳፩)
እንግዲህ ‹‹ብዙ ኃጢአት ባለችበት በዚያ የእግዚአብሔር ምሕረት ትበዛለች›› ተብሎ እንደተጻፈ ከኀጢአታችን ይልቅ የእርሱ ቸርነት እየበዛ እንጂ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በሚፈጽሙት በደል ምክንያት ቁጣ ከእግዚአብሔር ፊት ይወጣል ያን ጊዜም ዐመጸኞች የዐመፃቸውን ዋጋ በገፍ ይቀበላሉ፡፡ (ሮሜ.፭፥፲፬-፲፮)
የቃየል በምድር ላይ ተቅበዝባዥነት፣ የሰዶማውያን አሳዛኝ የሕይወት ፍጻሜ፣ የንጉሥ አክዓብ የሚስቱ የንግሥት ኤልዛቤል፣ የአፍኒንና የፊንሐስ ክፉ አሟሟት በኃጢአታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት በወጣ ቁጣ የሆነ የተደረገ ነው፡፡
ከሰው ልጅ እስከ እንስሳት በሞተ በኵር፣ በቅማል፣ በጓጉንቸርና፣ በተናካሽ ዝንብ እንዲሁም በአንበጣ መንጋ በሻህኝ (በቁስል) በበረዶ፣ በጨለማ፣ ውኃን ወደ ደም በመለወጥና እነዚህንና በመሳሰሉ በዐሥር መቅሠፍቶች እግዚአብሔር ግብፃውያንን የቀጣቸው ልቡ ከዐለት ይልቅ የደነደነው ፈርዖን ‹‹ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ›› በማለት የታዘዘውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማም ብሎ በእግዚአብሔርና በሕዝቦቹ ላይ በማመፁ ነበር፡፡ (ዘጸ.፰፥፩)
የሰው ልጅ በዘመኑ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የተገረፈበትን ወይም የተቀጣበትን የቀደመውን ኃጢአት እያስታወሰ ባለፈው መማር ሲገባው ከቀደመው ይልቅ አብዝቶ ኃጢአት በመሥራት ፈጣሪው እግዚአብሔርን በእጅጉ እያሳዘነ ይገኛል፡፡ ከዚህም የተነሣ ቁጣ ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ መላዋን ዓለም በገጸ መዓቱ እየገረፋት ነው፡፡
እውነት ነው! ዛሬም እንደ ጥንቱ እንደ ቃኤል ወንድም ወንድሙን ይገድላል፤ ለሞትም አሳልፎ ይሰጣል፡፡ የሰዶምን ሥራ ከቀደመው ይልቅ አብዝተው የሚሠሩ ሰዶማውያን ዓለምን ሞልተዋታል፤ የአፍኒንና ፊንሐስን የኃጢአት ፈለግ ተከትለው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያረክሱ አገልጋዮችም እንዲሁ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ እንደ ንጉሥ አክዓብና ሚስቱ ንግሥት ኤልዛቤል በሥልጣናቸው የድኃውን ርስት ሀብትና ንብረቱን የሚቀሙ አማሳኝ ባለሥልጣናት የሚፈጽሙት ግፍ በምድራችን ላይ ተትረፍርፈዋል፡፡
ነቢዩ ዳዊት ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ፤ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም›› በማለት አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉም እንደየዐቅሙ እንደየችሎታው ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ ሥልጣን ያለው በሥልጣኑ ጉልበት ያለውም በጉልበቱ በሌለው በደካማው ላይ አብዝቶ ኃጢአት ይሠራል፤ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፍ አብዝቶ ይበድላል፡፡ (መዝ.፶፪፥፫)
አሮንና እኅቱ ማርያም ወድንማቸው ሙሴ እርሱ ዕብራዊ /እስራኤላዊ/ ሲሆን ከዕብራውያን ወገን ያልሆነችውን ኢትዮጵያዊቷን እንዴት ያገባል? በማለት በሙሴ ላይ በማጕረምረማቸው (ወንድማቸውን በማማታቸው) እግዚአብሔር በዚህ ዘረኝነታቸው ምክንያት ‹‹የእግዚአብሔርም ቁጣ በእነርሱ ላይ ወረደ›› ተብሎ እንደተጻፈው እግዚአብሔር አሮንና እኅቱ ማርያምን ቀጥቷቸዋል፡፡ አሮንም ሙሴን ‹‹ስንፍና በማድረግ በድለናልና እባክህ ኃጢአት አታድርግብን›› በማለት እንደተማጸነ እኅቱ ማርያም በላይዋ ላይ በወጣባት ለምጽ ምክንያት ‹‹ከእናቱ ማኅፀን ሞቶ እንደተወለደ ከተበላ ግማሽ ሥጋዋ ጋር ለሞት አትተዋት›› እያለ እግዚአብሔር ኃጢአቷን ይቅር ይላት ዘንድ ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲለምንላቸው ሲማፀነው እንመለከታለን፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፱-፲፬)
እኛም በዘመናችን ይህንኑ አሮንና እኅቱ ማርያም የተቀጡበትን የዘረኝነት ኃጢአት አዘውትረን እየፈጸምነው እንገኛለን፡፡ የእኛ ደግሞ ከእነርሱ የከፋ ነው፤ ለዘመናት አብረን የኖርን ከአንድ ኢትዮጵያዊነት ወንዝ የተቀዳንና አንድ ደም ያለን ሕዝቦች ሆነን ሳለን እንዲህ እንድንባላ እርስ በርሳችን እንድንናከስ እያደረገን ያለው ዘረኝነት አሮንና እኅቱ ማርያም ከፈጸሙት ይልቅ እጅግ የከፋ ዘረኝነት ነው፤ በቅርብ ጊዜ ደግሞ ከቀያችሁ ያላገባችኋትን ሚስታችሁን ፍቱና እኛን የቀያችሁን ልጆች አግቡ፤ በማለት በይፋ የታወጀውን ዘረኝነት ሰምተናል፤ አይተናልም፡፡ በዚህም ምክንያት የዘራነውን እናጭድ ዘንድ ‹‹ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጥቶአልና ሕዝቡን ያጠፋቸው ዘንድ ጀምሮአል›› ተብሎ እንደተጻፈ በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት የወጣውን ቁጣ የሰው ልጆችን ሁሉ ያጠፋቸው ዘንድ ጀምሮአል፡፡ (ዘኁ.፲፮፥፵፰)
ዓለም ኃጢአተኝቱን ላለማመን ይህንን የመጣብንን መቅሠፍት (ኮሮና ቫይረስ) ‹‹እንዲህ የምትባል ሀገር ናት ያመረተችው፤ ከእንትና ቤተ ሙከራ አፈትልኮ የወጣ ቫይረስ ነው፤›› በማለት የተለያዩ የሽፍጥ ምክንያቶችን ትደረድራለች፡፡ ይሁን እንጂ ማንም ምንም ቢል እውነታው ግን ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ የሰው ልጅ የኃጢአት ደመወዙን ከእግዚአብሔር እጅ እየተቀበለ ነው፡፡ (ሮሜ.፮፥፳፫)
ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ራሱ እግዚአብሔር ገጸ መዓቱን መልሶ ምድርን በዓይነ ምሕረቱ እንዲመለከታት ‹‹በንስሓተመለሱና በሕይወት ኑሩ›› እንደተባለ በሕይወት እንኖር ዘንድ አሁኑን እያንዳንዱ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይኖርበታል፡፡ (ሕዝ.፲፰፥፪)
ያ ካልሆነ ደግሞ ‹‹እሺ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፌ ትበላችኋለች›› ተብሎ በነቢዩ እንደተነገረን በእምቢተኝነት አልመለስም ካልን እስክናልቅ ድረስ የጀመረን ይህ ሰይፍ (መቅሠፍት) እየበላን እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን በፊታችን እሳትና ውኃ ተቀምጦልናል የማንጎዳው እጃችንን ወደ የትኛው ብንጨምረው ነው? ስንል መልሱ ለሁላችንም ግልጽ ነው በሕይወት ለመኖር የሚጎዳንን እየተውን የሚጠቅመንን የእግዚአብሔርን ሕግ መከተል ይኖርብናል፡፡ (ኢሳ.፩፥፲፱)
በመጽሐፍ ‹‹ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፤ ማስተዋልም ይጋርድሃል›› ተብሎ እንደተነገረን ወደ እግዚአብሔር መመለሳችን እንዳለ ሆኖ በሥጋዊ አኗኗራችን ደግሞ ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄ ማድረግ ከሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክረ ሐሳቦችም ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው እንላለን፡፡ (ምሳ.፪፥፲፩)
‹‹…ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔር ቃል ባትሰማ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል… እግዚአብሔር ልትድን በማትችልበት በክፉ በሽታ ከእግር ጫማህ እስከ አናትህ ይመታሃል!›› (ዘዳ.፳፰፥፲፫-፮)