በባዕድ ምድር እስከመቼ?

ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

የስምዐ ጽድቅ ዝግጅት ክፍል በዝርወት ለሚኖሩት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የእናት ቤተ ክርስቲያናቸውን አስተምህሮ፣ ምክርና ተግሳጽ ይሰሙ ዘንድ ዓምድ በከፈተላቸው ጊዜ፤ መጀመሪያ ወዲያውም ዓምዱን ማስተዋወቂያ  ቢሆን ብዬ የጻፍኩት ጽሑፍ ዐራት እትሞች ዘልቆ ተፈጸመ፡፡ ጽሑፉን አስመልክቶ ከተለያዩ ጓደኞቼ ካገኘሁአቸው አስተያየቶች በመነሣት እንደ አብርሃም ሁሉ የያዕቆብን የስደት ሕይወት በመመርመር ለዛሬዎቹ ስዱዳን አርኣያ በሚኾን መልኩ በአጭሩ ለማቅረብ መረጥኩ፡፡ ጽሑፉ ይኸውና፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን ኑሮአቸውን በስደት ያደረጉ ወንድሞችና እኅቶች ዕለት ከዕለት ከሚያጋጥማቸው ችግር በመነሣት ጽሑፎችን አዘጋጅተው ወደ ዝግጅት ክፍሉ በመላክ ቢማማሩ መልካም ነው፡፡

ሕይወተ ያዕቆብ
ከአያቱ አብርሃምና አባቱ ይስሐቅ ቀጥሎ ሦስተኛው የሕዝበ እስራኤል አባት /3rd Patriarch/ ተብሎ የሚታወቀው ያዕቆብ ወላጆቹ ይስሐቅና ርብቃ በጋብቻ በተጣመሩ ሃያኛው ዓመት ላይ ተወለደ፡፡ እሱ ሲወለድ አባቱ የ60 ዓመት ጎልማሳ ነበር፡፡ /ዘፍ. 25ሚ20፤ 25ሚ26/፡፡ ይስሐቅና ርብቃ በሃያ ዓመት የጋብቻ ሕይወታቸው ወልደው ለመሳም አልታደሉም ነበር፡፡ በዚህ የተነሣም የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ፍሬ ይሰጣቸው ዘንድ አምላክን ይማጸኑ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን ሰምቶ በርብቃ ማኅፀን ያዕቆብና መንትያው ኤሳው ተፀነሱ፡፡ ነገር ግን በልመናና በጩኸት የተፀነሱት ያዕቆብና ኤሳው ገና በማኅፀን ውስጥ ሳሉ እየተገፋፉ እናታቸውን ይሠቃዩ ጀመር፡፡ በዚህ የተሠቃየችው ርብቃ እንደ ገና ፅንሱን ወደ ሰጣት አምላክ ምሕረትን በመለመን ጮኸች፡፡ በዚህ ጊዜ በማኅፀኗ የተቀረጹ ልጆቿ እስከሚወለዱና ከተወለዱም በኋላ ዕድሜ ልካቸውን የሚጣሉና አንዱ በሌላው ላይ እየተነሣ እንደሚጥለው በራእይ ተረዳች፡፡ ይህንን ምስጢር በልቡናዋ ያዘችው እንጂ ለባሏ አልነገረችውም ነበር፡፡ ሕፃናቱ ሲወለዱ እንደተነገረው ትንቢት አንዱ ከሌላው የማይመሳሰል ሆነው ተወለዱ፡፡ በኲሩ ዔሳው እንደ ጽጌረዳ አበባ ሰውነቱ ሁሉ ቀይና ጸጉራም ሆኖ፣ በኋላ የተወለደው ያዕቆብም የወንድሙ የዔሳውን እግር ይዞ ወደዚህ ዓለም መጡ፡፡ የኋለኛው በዚህ ግብሩ ያዕቆብ ተብሏል፡፡

 

ያዕቆብ ብሂል አኀዜ ሰኰና አዕቃፄ ሰኰና ማለት ነው፤ ሲያድጉም ዔሳው የበረሃ ሰው አርበኛ አዳኝ ሲሆን ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበር፤ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር፡፡ ዔሳው አድኖ በሚያመጣለት ምግብ የተነሣ የአባቱን ከፍ ያለ ፍቅር ሲያገኝ ያዕቆብ ደግሞ ከቤት ውሎ እናቱን ስለሚያጫውትና ስለሚታዘዛት የእናቱን ከፍ ያለ ፍቅር አገኘ፡፡ አባታቸው ይስሐቅ በእርጅና ምክንያት ጉልበቱ ደክሞ ዓይኑ ደግድጎ ከቤት በዋለ ጊዜ አንድ ቀን የሚወደውን ልጁን ዔሳውን እኔ እንደ ምወደው አድርገህ የምበላው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ ሳልሞት ሰውነቴ /ነፍሴ/ እንድትመርቅህ /እንድትባርክህ/ ወደ ዱር ሄደህ አድነህ አምጣልኝ አለው፡፡ ይህንን የሰማች ርብቃም የምትወደውን ልጇን ያዕቆብን እንደ ዔሳው አስመስላ አልብሳ አባቱ ይስሐቅ የጠየቀውን ምግብ እንደሚወደው አድርጋ አዘጋጅታለት ይዞ ወደ አባቱ እንዲገባና የአባቱን በረከት እንዲቀበል የምትችለውን ሁሉ በማድረግ አዘጋጀችው ዔሳውን መስሎ ወደ አባቱ በመግባትም የአባቱን በረከት ለመቀበል በቃ፡፡ በረከት በመቀበል እንደቀደመው የተረዳው ወንድሙ ዔሳውም “በጽድቅ ተሰምየ ያዕቆብ እስመ ፪ ጊዜ አዕቀጸኒ  ቀዳሚ ብኲርናየ ነሥዓኒ ወናሁ ዮምኒ ወዳግመ በረከትየ፤ ያዕቆብ በእውነት ስያሜውን አገኘ፡፡ አንደኛ ብኲርናዬን ሁለተኛ በረከቴን ወስዶብኛልና ሁለት ጊዜ አሰነካክሎኛ” በማለት ምሬቱን ገልጿል፡፡ /ዘፍ.27፥6/ ያም ሆነ ይህ ሁሉም በፈቃደ እግዚአብሔር የተከናወነ ሆነ፡፡

ምክንያተ ስደቱ
ለያዕቆብ ስደት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ትዳር ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ አባቱ ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ መርቆ “ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስት አታግባ፡፡ ተነሥተህ በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል ወደሚኖር ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሒድ፡፡ ከናትህ ወንድም ከላባ ልጆች ሚስት አግባ ብሎ አዘዘው፡፡ ፈጣሪዬ ካንተ ጋራ በረድኤት ይኑር፡፡ ያክብርህ ያግንህ ያብዛህ፡፡ ብዙ የብዙ ወገን ያድርግልህ አለው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ምድር ከነዓንን ትወርሳት ዘንድ የአባቴ የአብርሃምን በረከት ይስጥህ፡፡ ካንተ በኋላ ላሉ ለልጆችህም ይስጣቸው” አለው፡፡ /ዘፍ.28፥1-5/

ከያዕቆብ ሕይወት ምን እንማራለን?
ሀ. የእግዚአብሔርን ውለታ እያሰቡ ፍቅርን በሥራ መግለጽ
ያዕቆብ በስደት ሕይወቱ እግዚአብሔር በተለያዩ ጊዜያት እየተገለ ጠለት መክሮታል፤ አበረታቶታል፤ ሲያጠፋም ገሥጾታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስት አታግባ፤ ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሒድ፤ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ ያፍራህ ያብዛህ ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃምን በረከት ለአንተ ይስጥህ ለዘርህም እንዲሁ እንደ አን” ብሎ ምክር ያዘለ ትእዛዝ በሰጠው መሠረት ከቤርሳቤህ ተነሥቶ የርብቃ ወንድም ላባ ወደ ሚገኝበት በሁለቱ ወንዞች መካከል ወደምትገኝ ወደ ሶርያ ጉዞ ጀመረ፡፡ ሲጓዝ ውሎ ሎዛ ተብላ ትጠራ ከነበረች ቦታ ሲደርስ መሸበት፤ ደከመውም፡፡

 

በዚያውም ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፡፡ በሕልሙም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ በመሰላሉም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡበትና ሲወርዱበት ተመለከተ፡፡ በመሰላሉ ላይ የቆመው እግዚአብሔርም “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤ ይከብራሉ፡፡ ያዕቆብን ያከበረ ያክብርህ እየተባባሉም ይመራረቃሉ፡፡ ካንተም በኋላ በልጅህ ይመራረቃሉ፡፡ በምትሔድበት መንገድ ሁሉ በረድኤት ጠብቄ ወደዚህ አገር እመልስሀለ” አለው፡፡ /ዘፍ.28፥13-ፍጻ/ 

ይህ አምላካዊ ቃል ኪዳን ከወላጅ ከዘመድ ተለይቶ የስደት ጉዞ ላይ ለነበረው ያዕቆብ ታላቅ ቃል ኪዳንና የምሥራች ነበር፡፡ በመሆኑም ያዕቆብ ይህንን ቃል ኪዳን ለሰጠው አምላክ ውለታውን እያሰበ ፍቅሩን ለመግለጽ ፈጣን ነበር፡፡ ያ ታላቅ ሕልም ያየበት ሌሊት ሲነጋ ተነሥቶ የእግዚአብሔር ስም ማስጠሪያ ይሆን ዘንድ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤ በላዩም ዘይት አፈሰሰበት፡፡ ስሙንም ቤቴል ብሎ ጠራው፤ ቤተ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ በዚህም ብቻ አላበቃም፡፡ ስእለትም ተሳለ፡፡ “እግዚአብሔር በረድኤት ከኔ ጋራ ካለ በምሔድበትም ሀገር ሁሉ በረድኤት ከጠበቀኝ የዕለት ጉርስ ያመት ልብስ ከሰጠኝ ወደ አባቴም ቤት በደኅና ከመለሰኝ እግዚአብሔር ፈጣሪዬ ይሆንልኛል አለ፡፡ ፈጣሪውስ የግድ ፈጣሪው ነው እወደዋለሁ አመልከዋለሁ ሲል ነው፡፡ አንድም ይህን የሰጠኝ እግዚአብሔር አምላኬ ነው ማለት እሱን ብቻ አመልካለሁ ሌላ አላመልክም ማለት ነው፡፡ ይህችም የተከልኋት ደንጊያ የእግዚአብሔር ማደሪያ ትኾንልኛለች አለ፡፡ የሰጠኸኝን አሥራቱንም ሁሉ ላንተ ካሥር አንድ እሰጣለ“ አለ፡፡/ዘፍ.28፥20-ፍጻ/

በስደት በምንኖርበት ጊዜ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ የቸርነት ሥራውን ይሠራልናል፡፡ በበረከቱ ይጎበኘናል፡፡ በዚህ ጊዜ አባታችን ያዕቆብ እንዳደረገው ያንን ላደረገ እግዚአብሔር ውለታውን መክፈል ባይቻልም ፍቅራችንን በሥራ ለመግለጽ የተጋን መሆን አለብን፡፡ በያለንበት ክፍለ ሀገር ስሙ የሚቀደስበት መንግሥቱ የሚሰበክበት አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ማድረግ፤ በተቋቋመበት ቦታ የምንኖር ከሆነም እንዲጠናከሩ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር አብዝቶ ከሚሰጠን በረከትም አሥራት ማውጣት ይኖርብናል፡፡          

ለ. በስደት ሕይወት ትዕግሥት ማድረግ
አባቱ የመከረውን ምክርና የሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሔዶ የሕይወት ጓደኛውን ራሔልን ቢያገኝም እንዳሰበው አገር አቋርጦ የመጣላትን የትዳር አጋሩን ይዞ ወደ አገሩ በቶሎ መመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም አባቷ ላባ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሠረት ለሰባት ዓመታት የበግ ጠባቂው ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ከተሰደደ በኋላ አይቶ የወደዳትን ራሔልን በእጁ ያስገባ ዘንድ ሰባቱን ዓመት አገልጋይ ሆኖ የቆየው ያዕቆብ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ጨርሶ ልሂድ ብሎ ሲነሣ የራሔል አባት አልፈቀደለትም፡፡ ራሔልን ይዞ ለመሔድ ከፈለገ ሌላ ሰባት ዓመታትን እያገለገለ መቆየት እንዳለበት ነገረው፡፡ ያዕቆብ በተገባለት ቃል መሠረት ሰባት ዓመት ሲጠናቀቅ መሔድ ባለመቻሉ ቢያዝንም የመጣበት ዓላማ ግድ ይለዋልና ሌላ ሰባት ዓመታት ጨመረ፡፡ የእናቱ ፍቅር የወንድሙን የዔሳውን ብኲርናና ምርቃት መውሰድ እስኪያስችለው በፍቅርና በክብካቤ ያደገው ያዕቆብ ለ14 ዓመታት በግ ጠባቂ እረኛ ሆኖ በቀን ፀሐይና በሌሊት ቊር ሲሠቃይ ቢቆይም ተስፋ በመቁረጥ ተማሮ ወደ እናቱ አልሔደም፡፡ እርጅና ተጫጭኖት ሞት አፋፍ ላይ ሳለ ትቶት የመጣው አባቱ አሳስቦትና ናፍቆት ልሒድ አላለም ዓላማውን ማሳካት ነበረበትና በትዕግሥት ቆየ፡፡

ዛሬ በልዩ ልዩ ምክንያት በስደት የምንኖር ወገኖች ተወልደን ያደግንበ ትን ሀገርና ባሕል ትተን ስንመጣ ይነስም ይብዛ ይዘነው የመጣነው ዓላማ አለን፡፡ ይሁን እንጂ በስደት ሕይወት በሚያጋጥሙን ችግሮች የተነሣ ከዓላማችን የምናፈነግጥ ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገቡት በዋናነት በሁለት ምክንያት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሲመጡ በአዕምሮአቸው ሥለውት የመጡት ነገርና ሲደርሱ የሚያጋጥማቸው የተለያየ መሆን ነው፡፡ ሲመጡ ውጭ አገር ገንዘብ በቀላሉ የሚታፈስ እንደሆነ አስበው ይመጡና ካሰቡት ቦታ ደርሰው ሲያዩት እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ይደናገጡና ከሀገራቸው የወጡበትን ቀን ይረግማሉ፡፡ ተስፋም ቆርጠው ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት ይሳናቸዋል፡፡

ነገር ግን ከአባታችን ከያዕቆብ የስደት ሕይወት የምንማረው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ አባቱ ተነሥተህ ወደ ወገኔ ሒድና ሚስት የምትሆንህን ይዘህ ና ሲለው ምናልባት በወጣትነት አእምሮው እንደ ደረሰ በዓይኑ ዐይቶ የፈቀዳትንና የወደዳትን ይዞ እንደሚመለስ አስቦ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሶርያ ሲደርስ ያጋጠመው ሌላ ነገር ነው፤ የ14 ዓመታት የእረኝነት ሕይወት፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ደንግጦ ወይም ተበሳጭቶ ወደ አገሬ ልመለስ አላለም፡፡ በዚያው ሲቆይም ዕለት ዕለት ሲበሳጭና ተስፋ ሲቆርጥ እንደነበረ መጽሐፍ አያስነብበንም፡፡ ስለዚህ በስደት ሕይወት ስንኖር ባልጠበቅነው ሁኔታ በሚያጋጥመን ችግር የተነሣ ሳንሳቀቅ ከሀገራችን ስንወጣ ይዘነው የወጣነውን ዓላማ አጽንተን ለስኬታማነቱ እየታገልን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ያንን ያደረግን እንደሆነ ያዕቆብ ራሔልን ከነአገልጋዮቿ ይዞ አገሩ እንደገባ እኛም በዕውቀት በልጥገን በገንዘብ ከብረን አገራችን እንገባለን፡፡

ሌላው ምክንያት የወጡበትን ዓላማ በአግባቡ ለመረዳት አለመቻል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ ውጭ የሚወጡት በተረዳ ነገር ሰፍረው ቆጥረው በዕቅድ ያወጡትን ዓላማ ሳይዙ ነው፡፡ ያ ባለመሆኑም በስደት ሕይወታ ቸው በሚያጋጥማቸው ችግር በቀላሉ መደናገጥና መማረር ብሎም ተስፋ መቁረጥ ያጋጥማቸዋል፡፡ በስደት ሕይወት ይቅርና በየትኛውም ሕይወቱ ቢሆን ሰው የሚመራበት የሕይወት ዓላማ ያስፈልገዋል፡፡ ዓላማ የሌለውና ዓለማውን በአግባቡ ያለተረዳ ሰው በየመንገዱ በሚፈጠሩ ችግሮች /መሰና ክሎች/ በቀላሉ ለመውደቅ የተመቻቸ ይሆናል፡፡ ዓላማ ያለውና በአግባቡ ዓላማውን የተረዳ ሰው ግን በጥንካሬ የሚጓዝ፣ በቀላሉ የማይወድቅና ቢወድቅም ፈጥኖ የሚነሣ ሰው ነው፡፡ አባታችን ያዕቆብ ከሀገሩ የወጣበትን ዓላማ ያልተረዳ ቢሆን ኖሮ በፍጹም አስቦትና ሆኖት የማያውቀውን ሕይወት ለ14 ዓመታት ይቅርና ለ4 ቀናትም ቢሆን ታግሦ ሊቆይ አይችልም ነበር፡፡  

    
ሐ. ያሰቡትን ካገኙ በኋላ ወደ ተወለዱበት ሀገር መመለስ
ያዕቆብ ከ21 ዓመታት አገልግ ሎት በኋላ ራሔልን ሲያገኝ ራሔልንና በስደት ያጠራቀመውን ሀብት ይዞ ወደ ተወለደበት ሀገር ሊመለስ ወሰነ፡፡ ዓላማውን ካሳካ በኋላ በባዕድ ምድር ተጨማሪ ዓመታትን በባዕድነት መቆ የት አልፈለገም፡፡ ፈጣሪው እግዚአ ብሔርም ተመለስ አለው፡፡ /ዘፍ.31፥3/ እሱም ተመለሰ፡፡

ሰዎች በስደት ሕይወት ሲኖሩ ከሀገር ይዘውት የሚመጡት ግልጽና የጸና ዓላማ ሊኖር እንደሚገባ ሁሉ ዓላማቸውን ከግብ ካደረሱ በኋላ ሊኖር ስለሚገባው ሕይወት ማሰብ አግባብ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ ረጅም ጊዜ በስደት የኖሩ ሰዎች ዓላማቸውን ካሳኩ በኋላም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የማያስቡ ይኖራሉ፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚያደርጓቸው በቂ ምክንያቶች የሚኖሯቸውም አይጠፉም፡፡

ዓላማን ከግብ ካደረሱ በኋላ ወደ ሀገር መመለሱ ለተመላሹ ከሚሰጠው የአእምሮ ዕረፍትና የተረጋጋ ሕይወት ባሻገር ከተመላሹ በሚገኘው ዕውቀት፣ ልምድ፣ ሀብትና ጥረት ወገንና ሀገር እንዲጠቀም ያስችላል፡፡ ያዕቆብ ዓላማውን ካሳካ በኋላ በመመለሱ ሕዝበ /ሀገረ/ እስራኤልን በአዕማድነት የመሠረቱ ልጆች ለማፍራት ችሏል፡፡

በዚህም ዘመን ሰፊ ራእይ ሰንቀን ሩቅ አልመን ወደተለያዩ ሀገሮች የተሰደድን ኢትዮጵያውያን በከፈልነው መሥዋዕትነትና በእግዚአብሔር አጋዥነት ዓላማችን ከተሳካልን በኋላ ወደ ሀገራችን ልንመለስ ያስፈልጋል፡፡ “ሠናይ ለብእሲ ለእመ ይከውን መቅበርቱ ውስተ ርስቱ፤ የሰው ሞቱ፤ መቃብሩም በሀገሩ /ርስቱ/ ቢሆን መልካም ነው“ እንደተባለ መመለስ የማያስችለን መሠረታዊ ችግር ከሌለ በስተቀር የተሰደድንበት ዓላማ ከተሳካ በኋላ በባዕድ ምድር ውሎ ከማደር ይልቅ ባካበትነው ቁሳዊና አእምሮአዊ ሀብት ሀገርንና ወገንን በመጥቀም ለመጠቀም ቤተሰብን ይዞ፤ ሀብትንም ሸክፎ ርስት ሆና ወደ ተሰጠችን ምድረ ኢትዮጵያ ለመግባት ማመንታት የለብንም፡፡ ያዕቆብን ተመለስ ብሎ ያዘዘው እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ወደሀገራችን እንድንመለስ ፈቃዱ እንደሆነም እንረዳለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 16 ከግንቦት 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.