‹‹በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት›› (ገላ. ፭፥፲፫)
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ነጻነት ከማንወደውና ከማንፈልገው አካል፣ ሐሳብ፣ ተጽዕኖ፣ ጫና፣ አገዛዝ ሁሉ ነጻ መሆንንና አለመገዛትን ያመለክታል፡፡ የነጻነትን ታላቅነት የምንረዳው ባርነት ምን ያህል አስከፊ መሆኑን በባርነት ካሉ፣ ከነበሩ ወይም ደግሞ ራሳችን ባርነትን ከቀመስነው ብቻ ነው፡፡ ጨለማን ያላየ በብርሃን ለማመስገን እንደሚቸገር፣ ረሀብን ያልቀመሰ ረሃብ ምንድነው? ማለቱ እንደማይቀር ሁሉ ባርነትና የጭካኔ አገዛዝን ያልተመለከተም የነጻነትን ነገር ለመረዳት ይቸገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት ነጻነትን በቃል ደረጃ የተረዳነው ይምሰለን እንጂ ምንነቱን ለመረዳት የተቸገርን ለመሆናችን አያሌ ማሳያዎች አሉ፡፡ የዚህም አንዱ ማሳያ ዛሬ በዓለም ላይ ነጻነት ከዋልጌነት ጋር መመሳሰሉ ወይንም መተርጎሙ ነው፡፡ ነጻነት የፈለግነውን መናገር፣ መጻፍ፣ ወይንም መተግበር ሳይሆን ዐስቦና አገናዝቦ መናገርና መጻፍ እንዲሁም ማድረግ ነው፡፡ ነጻነት ሥልጣን፣ ገንዘብ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ወሳኝ ሰዎችን ሁሉ በእጄ በደጄ ብሎ የገዛ ሐሳብን ፍላጎትንና አላስፈላጊ ጫናዎችን የእግዚአብሔር በሆኑና አምላክ ነጻ አድርጎ በፈጣራቸው ሰዎች ላይ እንደፈቀዱ ማድረግ ሳይሆን በሰፈሩት ቁና መሰፈር እንዳለ በመገንዘብና ነግ በኔን ዐስቦ በራስ ላይ ሊደርስ የማንፈልገውን በሌሎች ላይ ከማድረግ መቆጠብ ነው፡፡
ነጻነት አለኝ ብሎ እንደ ልብ መናገር፣ ያሰቡትን ሁሉ መፈጸም አእምሮውን ያጣ ሰው መገለጫ እንጂ ጤነኝነት አይደለም፡፡ ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን ነጻነታችን ገደብ አለው፡፡ ለነጻነቱ ገደብ የሌለው ቸርነቱ ካልከለከለው በቀር ሁሉን ማድረግ የሚችል እርሱ ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ቀዳማዊው ሰው አዳም አምላካችን እግዚአብሔር ሲፈጥረው ነጻ አድርጎ የፈጠረው መሆኑ ባያጠያይቅም ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ‹‹በገነት ካለው ዛፍ ብላ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና›› ብሎ ገደብ አስቀምጦለታል፡፡ (ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯)
የነጻነትን ትርጒም በሚገባ ሳይረዱ ለልጆችም ሆነ ለራስ ‹ሙሉ ነጻነት› መስጠት የዋልጌነትን መንገድ ገርብቦ ሳይሆን አስፍቶ መክፈት ነው፤ መጨረሻውም ባርነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰው ነጻ ሆኖ የተፈጠረ፣ የመረጠውን ለማድረግም ነጻ ፈቃድና መብት የተቸረው ቢሆንም ያን ነጻነት ተጠቅሞ የሚያደርገው ሁሉ እንደማይጠቅመው ሲናገር ‹‹በሆነው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፤ ግን ሁሉ የሚጠቅመኝም አይደለም›› በማለት አስተምሮዋል፡፡ የመብላት መብት አለኝ ተብሎ ሁሉ ይበላልን? የመናገር ነጻነት አለኝ ብለን ያሰብነውን ሁሉ ብንናገር ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር እንችላለንን? (፩ኛቆሮ. ፮፥፲፪)
ዛሬ በዓለም ላይ የነጻነት ትርጒም በመዛባቱ ምክንያት ራስን መግዛትና ሕገ እግዚአብሔርን መጠበቅ እንኳን በመታሰሪያ ገመድ እንደመጠፈር እየተቆጠረ ነው፡፡ ‹ገንዘብ ሞልቶኛልና የፈለኩትን ለማድረግ ነጻነት አለኝ፤ እንደ ፈቀድኩ ልሁን ማለት› ወደ አዘቅት መውረድ ነው፡፡ መብቴ ነው እያሉ ገደብ አልፎ መጠጥ መጠጣቱ ቤተሰብን ወደመበተን፣ ጤናን ወደማሳጣት፣ ሰውንም ወደማሳዘንና ወደሌሎችም ማኅበራዊ ሥነ ልቡናዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች የሚዘፍቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ የከለከለን፣ አድርጉ ብሎ ያዘዘን ነገር ሁሉ ከኀዘን፣ ከመከራ፣ ከችግር፣ በማኅበራዊ አኗኗራችን ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች፣ ከስስትና ስግብግብነት፣ ኃላፊነትን ባለመወጣት ከሚመጡ ተጠያቂነቶች፣ ኃፍረት አስከትለው አንገትን ከሚያስደፉ ድርጊቶችና ከመሳሰሉት ሁሉ የሚጠብቀን አጥር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ስለ እግዚአብሔር ሕግ ሲናገር ‹‹ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ የሚያመለክትና የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ የሰማውን የሚዘነጋ ያይደለ ይህ በሥራው ብፁዕ ነው›› (ያዕ. ፩፥፳፭) ይላል፡፡
ሰው ሥልጣን ሲያገኝ ሥልጣኑ በሕግና በሥርዓት ካልተገደበ አጥፍቶ ይጠፋበታል፡፡ ለአንደበቱና ለብዕሩ ገደብ ካላኖረ ብዙዎችን ይጎዳበታል፤ ሀገርንም ይጠፋበታል፡፡ ሰው እንዳያዝንም እንዳያሳዝንም ገደብ ሊኖረው ይገባል፤ እውነተኛ ነጻነት ይህ ነውና፡፡ ለደረስንበት ታላቅ ደረጃና ለወጣንበት የስኬት ማማ በሥራችን ያሉ ሰዎች ገደብና ልክ ባያኖሩልን እንኳን ለራሳችን ገደብ ልናኖር ይገባናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ነጻነት ወጥታችሁ፥ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ›› ብሎ ካስተማረው ትምህርት በተቃራኒው ነጻነትን በክርስቶስ እንዳገኘ እየተናገረ ጆሮዎችን ጭው የሚያደርግ ክፋት የሚፈጽም ሰው እጅግ በዝቶዋል፡፡ አንድ ሰው ነጻ ወጥቶዋል የሚባለው በምን ዓይነት ሁኔታ ሲኖር ነው? መጽሐፍ እንደሚያስተምረን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ ከዘለዓለም ሞትና ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ አውጥቶናል፡፡ ነጻ ወጥተሃልን? የሚለው ጥያቄም የሚነሣው ክብር ይግባውና ነጻነትን ካደለን በኋላ ዓለም በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ያለው የሚለውን ስንመለከት ነው፡፡ መጽሐፍ በክርስቶስ ነጻ እንደወጣን እንደሚነግረን ሁሉ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ያስጠነቅቀናል፤ ‹‹እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ›› እንዲል፤ (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፲፮፣ገላ. ፭፥፩)
ነጻ ወጥተሃልን? ለሚለው ጥያቄም መልሳችን ‹አዎን› ከሆነ በባርነት እንዳልተያዝን እርግጠኞች ልንሆን ይገዛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነጻ እንደወጡ ከመናገር አልፈው ሌሎችንም ነጻ ወጥታችኋል እያሉ የሚሰብኩ ነገር ግን ደግሞ ራሳቸው ነጻነት ያላገኙ ሰዎች እንዳሉ ሲያስተምረን ‹‹የነጻነትን ሕግ ተምረው ራሳቸው ለኃጢአት የሚገዙ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ለታዘዘለት ይገዛልና›› በማለት ይናገራል፡፡ (፪ኛ ጴጥ. ፪፥፲፱)
ዓለም ነጻ ወጥቻለሁ እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ለዋጀው የሰው ልጅ መጥፊያ በሚሆን ባርነት አልተያዘምን? በዘረኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በሥልጣን ጥም፣ ለጥቅም ሲሉ ፈጣሪያችን ክርስቶስ ወደ መቃብር በወረደላቸው ሰዎች መካከል ጠብ በመዝራት፣ ሀገርን በሚጎዳ ብልሹ አሠራር፣ እግዚአብሔር እጅግ በሚያዝንበት ጉቦ ተኮርና የዘመድ አዝማድ አሠራር፣ በትምህርት ደረጃና በዕውቀት በመመካት ባርነት አልተያዝንምን? እኔና የኔ ብቻ ይኑር ሌላው ይጥፋ አላልንምን? በእግዚአብሔር ነጻ ወጥቻለሁ እያሉ ማመፅ፣ ጠብ መቀስቀስ፣ ሤረኝነት፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨት በእግዚአብሔር ላይ መዘበት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፉ ነገር ይራቅ›› ይላልና፡፡ (ገላ. ፮፥፯፣ ፪ኛ ጢሞ. ፪፥፲፱)
ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በሃይማኖት ጸንታችሁ እንደ ሆነ ራሳችሁን መርምሩ›› ብሎ እንደተናገረ÷ ነቢዩም ‹‹መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን›› ብሎ እንደሰበከ እስኪ ራሳችንን እንፈትሽ፤ ክርስቶስ ነጻነትን ባደለበት ዓላማ ነው የቆምነው ወይስ ሰውን በሚጎዳ ሰይጣናዊና ፍጹም ዓለማዊ ግብር? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ÷ እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋልና፤ ነገር ግን ለሥጋችሁ ፈቃድ ነጻነታችሁን ምክንያት አታድርጉላት›› በማለት ነጻ መውጣት ማለት ለዚህ ዓለም ምቹ ሰው መሆን አርነቱን ምክንያት እያደረጉ በሥጋ ፈቃድና መንገድ መጓዝ ማለት እንዳልሆነ ያስተምረናል፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፫፥፭፣ሰቆ. ኤር. ፫፥፵፣ ገላ. ፭፥፲፫)
ክርስቲያን ነኝ የሚልና ነጻነት አለኝ የሚል ሰውመንገዱ መከራ መስቀል ምርኩዙ እግዚአብሔር ዓላማው መንግሥተ ሰማያት ሊሆን እንደሚገባ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ሲያስተምር ‹‹ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡ ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ያጠፋታል÷ ሰውነቱን ስለ እኔና ስለ ወንጌል የሚያጠፋትም ያገኛታል›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ማር. ፰፥፴፬)
ራስን መካድ የራስን የሥጋ አስተሳሰብ ፈቃድና ምኞት መተው እንደመሆኑ አንድ ሰው በክርስቶስ ክርስቲያን ይባል ዘንድ መስቀሉንም መሸከም ያስፈልጋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሰዎች በዚህ ዓለም ስንኖር ስለ ክርስቶስና ስለ ወንጌል መከራን መቀበል ይጠበቅብናል፡፡ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለምን ድል ነሥቼዋለሁና፡፡›› እንዲሁም ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ ልንገባ ያስፈልገናል›› ተብሏልና፡፡ (ዮሐ. ፲፮፥፴፫፣ ሐዋ. ፲፬፥፳፪)
ጌታችን ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ እንደሚያጠፋት ሲናገርም ነፍሱን (ሰውነቱን) በዚህ ዓለም ሐሴትና ደስታ ሊያኖራት፣ በራሱ ፈቃድም ሊመራት የሚወድ በሚመጣው ዓለም እንደሚያጠፋት፣ ከመንግሥተ ሰማያትም ውጭ እንደሚያደርጋት ሲገልጽን ነው፡፡ ስለ እርሱና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እንደሚድን ስለ እርሱና ስለ ሕገ ወንጌል ብሎ ፈቃዱንና ምኞቱን የተወና ዓለምንም የናቀ ሁሉ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት በምትገለጠው በመንግሥተ ሰማያት እንደሚያገኛት ተናግሯል፡፡ (ራእ. ፯፥፲፬፣ ፲፬፥፩፣ መዝ. ፴፫፥፲፱፣ ሉቃ. ፲፮፥፲፱-፴) ራስን ሳይገዙ ክፉ የሆነ የሥጋ ፈቃድን በቃለ እግዚአብሔር ሳይገቱ፣ ለሠሩትም ክፉ ሥራ ንስሓ ሳይገቡ፣ ቸርነቱ ብዙ ነው እያሉም በኃጢአት ላይ ኃጢአት እየከመሩና በዋዛ ፈዛዛ እየተመላለሱ ነጻነት አግኝቻለሁ ማለት ከንቱ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ (ኤር. ፰፥፫-፭፣ ገላ. ፭፥፳-፳፫፣ ሲራ. ፲፭፥፭)
በክፋት መንገድ እየተጓዙ ነጻ ወጥቻለሁ ማለት ነጻነት ሳይሆን ጒስቁልና መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያንን አለቃ ሲገሥጸው ‹‹ሀብታም ነኝና፥ ባለጠጋ ሆኛለሁ፥ አንድ ስንኳ አያስፈልገኝም ትላለህ፡፡ ነገር ግን ጎስቋላና ምስኪን፥ ድሃም፥ ዕውርም፥ የተራቈትህም መሆንህን አታውቅም›› ብሎ በተናገረው ቃል እናስተውላለን፡፡ (ራእ. ፫፥፲፯) ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹምን ሕግ የሚመለከትና የሚጸናበት …›› በማለት በተናገረበት አንቀጽ ነጻነት ብሎ የጠራው ምንን ነው? ቢሉ ነጻ የምታወጣ ሕገ ወንጌልን ነው፡፡ ክርስቶስ ነጻ ያወጣን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ባልንጀራችሁን እንደራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ በሚል ሕገ ወንጌል እንድንኖር ነውና ሐዋርያው ወንጌልን ‹‹ነጻ የምታወጣ ፍጹም ሕግ›› ብሏታል፡፡ (ያዕ. ፩፥፳፭)
ሕገ ወንጌልንም የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በቤተ ክርስቲያንና በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ደግሞ በዘመናት የነበሩ አያሌ ነገሥታትና አሸባሪዎች የነጻነትን መንገድ የምታስተምራቸውን ቤተ ክርስቲያንን ነጻነት ሲያሳጧት ኖረዋል፡፡ በዘመነ ሐዋርያት በሄሮድስ ዘመነ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ መከራ እንደሆነና ክርስቲያኖችም በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ወደ ልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች እንደተሰደዱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተገልጿል፡፡ በቀድሞ ስሙ ሳውል ኋላም በክርስትና ስሙ ጳውሎስ የተባለው ሐዋርያም ክርስትናን ባለመረዳቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳድድ እንደወጣና በደማስቆ መንገድ ላይ ክርስቶስ ማንነቱን ያውቅ ዘንድ ተገልጦለት ለሐዋርያነት እንደመረጠው ተጽፎልናል፡፡ (ሐዋ. ፱፥፩) ይኸው ሐዋርያ ክርስትናን ተቀብሎ ተመልሶ ወንጌል ማስተማር ከጀመረ በኋላም ስለቤተ ክርስቲያንና ስለ ክርስቲያኖች ሲናገር ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስንም በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ›› በማለት ቤተ ክርስቲያን እስከ ምጽአተ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚጠብቃትን ነገር ተናግሯል፡፡ (ሐዋ. ፰፥፩፣፪ኛ ጢሞ. ፫፥፲፪)
ከዘመነ ሐዋርያት በኋላም እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ቤተ ክርስቲያን በኔሮን ቄሣር፣ በድምጥያኖስ፣ በዳክዮስ፣ በቨሌርያን፣ በአሌርያን፣ በትራጃን፣ በማርቆስ አብሪሊዮስ፣ ዲዮቅልጥያኖስና በሌሎችም ቄሣራውያን ነገሥታት ስትሰደድና ልጆችዋንም በእነርሱ ሰይፍ ስትነጠቅ፣ ቅርሶችዋን ስታጣ ኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ዳርቻዎች በአፍሪካም ሆነ በመካከለኛ ምሥራቅና በአውሮፓም በክፉዎች ነገሥታትና ቡድኖች የቀመሰችውንም የግፍ ጽዋ ዓለም ያውቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ራሷ የሆነ አካሉ የሆነችለት ክርስቶስ በዳግም ምጽአት እስኪመጣ ድረስ ትሰደዳለች፡፡ የስደቷም ምንጭ የአሳዳጆችዋ እርሷን አለመረዳትና የልቡና ክፋት ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ወንጌሉና በተግባርም እንደሚስተዋለው በዚህም ዘመን ቢሆን ቤተ ክርስቲያንን ከማሳደድና እንድትሰደድ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ያላረፉ ብዙ እጆች አሉ፡፡ እንደውም በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ከማሳደድ የከፋ አንድነቷን ፈትቶ የማዳከም ሤራ ሲጠነሰስ የተመለከትነው ሀቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰደድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከማሳደድ በላይ ነው፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፩፣ ዮሐ. ፲፮፥፩፣ ፊል. ፩፥፳፱)
ቤተ ክርስቲያን እንድትሰደድ ስሟን ማጠልሸትና ሳያውቋት የድንቁርናና የኋላቀርነት ምንጭ ማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ከማሳደድ በላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ‹የጨቋኞች መጠቀሚያ ሆና ኖራለች፤ ስትበዘብዝ ኖራለች ….ወዘተ› እያሉ በእርሷ ላይ አጥፊ ቅስቀሳ መንዛት ከማሳደድ ባሻገር ሳትሰደድ ማጥፋት ነው፡፡ በመሠረታዊ የዶግማ ትምህርቷ ተከራክሮ ማሸነፍ ሲያቅት ‹እንዲያ ነበረች እንዲህ ነች› እያሉ ልጆችዋንና ተቋማትዋን ለአጭዳ ማመቻቸት ከማሳደድ በላይ ነው፡፡ የሌላውን የእምነት መገለጫ አለባበሶችና ምልክቶች እያከበሩ የኦርቶዶክሳዊነት መገለጫ የሆኑ ምልክቶችን (እንደ አንገት ማዕተብ) ማንኳሰስና በ ‹ሴኩላሪዝም› ስም ኦርቶዶክሳውያኑ እንዳያደርጉት ማሸማቀቅ የማሳደዱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ድርጊቱ እየተፈጸመ ድርጊቱን መካድና ድርጊቱን ለፈጸሙ አካላትም በልዩ ልዩ መንገድ ሽፋን መስጠት ደግሞ ከማሳደድ በላይ ነው፡፡
በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች መንፈሳውያን በዓላት እንዳይከበሩ ተጽዕኖ መፍጠር፣ ቦታዎችን መንጠቅ፣ ካህናቱንና አገልጋዮቹን ማዋረድና ማሳደድ እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው በክርስቲያኖች ላይ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አፍራሽ ድርጊቶች ዋነኛ የስደት ዓይነቶች መሆናቸው በልዩ ልዩ አካላት ተገልጧል፡፡ ሥልጡኖች ነን እያሉና ስለነጻነትና መብት እየደሰኮሩ ሌላውን ነጻነት ማሳጣት የኋላቀርነት ኋላቀርነት እንጂ ሌላ ምን ስያሜ ይሰጠዋል!! ቤተ ክርስቲያንን ማሳደድ መሰደድን ያመጣል፡፡ ክርስቲያኖችን መግደል ሞትን ያመጣል፡፡ የክርስቲያኖችን ንብረት ማውደም ውድመትን ያስከትላል፡፡ በቡድን ተደራጅተህ ዛሬ ክርስቲያኖችን አዋክብ የምትዋከብበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስትናው ከተመለሰ በኋላ ክርስቲያኖች ላይ በልዩ ልዩ ስልትና መንገድ መከራ ስደት ኀዘንና ልቅሶን የሚያመጡ ቡድኖች መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ለተሰሎንቄ ምእመናን ሲገልጽ ‹‹ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን፡፡ ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቆጠሩ ዘንድ÷ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ÷ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን÷መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና›› ብሏቸዋል፡፡ (፪ኛ ተሰ. ፩፥፯)
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል አማለጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር