‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› (መዝ. ፳፪፥፬)
ዓለም በኃጢአት እና ክፋት ተሞልታ በሰይጣን አገዛዝ ሥር ከሆነች ውላ አድራለች፤ የሰይጣን ሥራ ከዳር እስከዳር ተስፋፍቶ በበዛበት ወቅት ሰዎች የርኩስ መንፈስ ቁራኛ በመሆን የመከራ አረንቋ እየተፈራረቀባቸው ይገኛሉ፡፡ ጦርነት፣ ቸነፈር፣ ረኃብ፣ በሽታና ሥቃይ እንግልትም እየደረሰባቸው ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዓይነት ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደሚበረታ ይጠቅሳል፡፡ ሰዎች አምላካቸው እግዚአብሔርን በኃጢአታቸው የተነሳ ሲያሳዝኑ እና ትእዛዛቱን ሲተላለፉ የተለያዩ ቅጣቶች በምድር እንደሚደርስባቸው ሲያስረዳም እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡›› (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩)
ሰዎች ከእግዚአብሔር ሕግ ውጪ ከሆኑና ትእዛዛቱን መተላለፍ ከጀመሩ በተሳሳተው መንገድ በመጓዝ ከፈጣሪያቸው ይርቃሉ፤ ለዚህም አላስፈላጊ ለሆነ ክፉ ድርጊት ይጋለጣሉ፤ ሆኖም የሕይወት መንገድ አንድ ብቻ ነውና በእርሱ ልንጓዝ ያስፈልገናል፡፡ ያም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤›› እንዲል (ዮሐ. ፲፬፥፮)
ዓለም በቸነፈር በተመታችበት በዚህ ወቅት ብዙ ሰዎች መድኃኒት የለሽ በሆነ በሽታ በመሸበራቸውና በመሠቃየታቸው በሞት ጥላ ውስጥ መሆናቸው እሙን ነው፤ አንዳንድ ሰዎች የፈጣሪያችንን ይቅርታ በመሻት፤ ከቁጣ ወደ ምሕረት እንዲመለስልን መማጸን ጀመረናል፡፡ ሆኖም ግን ንስሓ ሳንገባ ቂም በቀልን ከእኛ ሳናርቅ ፈጣሪያችንን ብንለምነው ጸሎታችን ከአምላክ ዘንድ ሊደርስ አይችልም፡፡ እንዲሁም ሌሎች በሠሩት ኃጢአት ተጸጽተው ንስሓ መግባት የተሳናቸው እና ወደ እርሱ መመለሻ መንገዱ የጠፋባቸው ሰዎች ነገ የሚመጣውን እንደአመጣጡ ለመቀበል በስጋት የሚኖሩ ሆነዋል፡፡
ነቢዩ ዳዊት ‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› እንዳለው በትራችንና ምርኩዛችን እግዚአብሔር መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ የእግዚብሔርን አምላክነት በማመንና በመቀበል፤ በሕጉም በመመራት ፈጣሪያችንን እያመለክን ልንኖር ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ግን በመቅሠፍት እንዲህ ይቀጣናል፤ ለጠላትም አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ በሰይጣን ባርነት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ደግሞ ለንስሓም ሆነ ለይቅርታና ምሕረት የበቃ አይሆንም፡፡ የኃጢአት ትንሽ ትልቅ እንደሌለው እና ሁሉም እንደየሥራው እንደሚፈረድበት ወይም እንደሚፈረድለት አምላካችን ተናግሯል፡፡
ክርስቲያን በክርስቶስ ክርስቲያን መባል ብቻ ሳይሆን ለዐሥርቱ ትእዛዛት መገዛት እና በክርስቲያናዊ ሕይወት መኖር ይገባዋል፤ ይህን ሁሌም እናስታውስ ዘንድ ይጠበቅብናል፡፡ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ እኛን ክፋትንና ተንኮልን በማሳሰብ አብዝተን ኃጢአት እንድንሠራ ከማድረግ ባሻገር ልባችን ደንድኖ እዝነ ልቡናችን ታውሮ እየጠፋን መሆኑን መለየት እስኪያቅተን ድረስ ያስታልና፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ሕግ እንድንጥስ ወይም በድፍረት እንድንተላለፍ ያደርጋል፡፡
ነገር ግን ሰው በእምነት እና በተስፋ በምድር ላይ የሚገጥመውን ችግርም ሆነ መከራ ለማለፍ ከትእዛዛቱ አንዱን እንኳን ሳያጎድል ለፈጣሪው መገዛት አለበት፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ትእዛዛቱን ለሙሴ በራሱ ጣት ጽፎ እንደሰጠው እና እንደተማርናቸው ልናስታውሳቸውና ልንተገብራቸው ይገባል፡፡ እነርሱ ለእኛ በትርትና ምርኩዝ ናቸውና፡፡
፩. ከኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ
፪. የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ
፫. የሰንበትን ቀን አክብር
፬. አባትህንና እናትህን አክብር
፭. አትግደል
፮. አታመንዝር
፯. አትስረቅ
፰. በሐሰት አትመስክር
፱. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ
፲. ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ
ከዐሠርቱ ቃላት ዘጠኙ ተጠብቀው አንደኛው እንኳን ከፈረሰ ዐሠርቱ ሕግጋት ሁሉ እንደፈረሱ ይታሰባል፡፡ ዘጠኙን ሕግ ብቻ መጠበቅ ምንም ዋጋ አይኖረውም። ለምሳሌ ዐሥር በር ያለው ቤት ቢኖር ዘጠኙ በሮች ቢዘጉና አንዱ ሳይዘጋ ቢያድር፤ ሌባ ክፍት በሆነው በአንደኛው በር ገብቶ ንብረቱን ሁሉ ከወሰደው የዘጠኙ በሮች መዘጋት ምንም ጥቅም አላስገኘም ማለት ነው፡፡ የአንደኛው መከፈት ለንብረቱ መጥፋት መንስኤ ይሆኗልና። ዐሥርቱ ቃላትም በትክክል ካልተጠበቁ ዋጋ የማያሰጡ መሆናቸውን ሐዋርያው ያዕቆብ እንዲህ ሲል ያስረዳል፤ ‹‹ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው እርሱ አትግደል ብሎአልና፤›› (ያዕ. ፪፥፲)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል እስራኤል ዘነፍስ ለተባልነው ለእኛ ስለትእዛዛቱ እንዲህ አስተምሮናል፡፡
ሰውን መግደል እንደማይገባ
‹‹ለቀደሙት ሰዎች ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ የተባለውን ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጨርቅ ለባሽ’ የሚለው በአደባባይ ይፈረድበታል፤ ‘ደንቆሮ’ የሚለውም ሁሉ በገሃነመ እሳት ፍርድ ይፈረድበታል። መባህን በመሠዊያው በምታኖርበት ጊዜ፥ በዚያም ሳለህ የተጣላህ ወንድምህ እንዳለ ብታስብ፥ መባህን ከዚያ በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድና አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚህ በኋላም ተመልሰህ መባህን አቅርብ። በመንገድ ከእርሱ ጋር ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራህ ለዳኛ እንዳይሰጥህ፤ ዳኛውም አሳልፎ ለሌላውም ይሰጥሀል፤ ወደ እስር ቤትም ትገባለህ፡፡ እውነት እልሀለሁ፤ የመጨረሻዋን ትንሽ ገንዘብ እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።›› (ማቴ. ፭፥፳፩-፳፮)
ጌታችን ያስተማረውን ይህ ትእዛዝ ስንመለከት ሌሎችን መግደል ብቻ ሳይሆን በእኛ መካከል ፍቅርን የሚያጠፋ እና ክብርን የሚያጎድፍ ቃል እየተጠቀሙ መስደብና መዝለፍ ኃጢአት እንደሆነ ነው፡፡ ሰዎች እርስ በርስ በመዋደድ እንጂ በጥላቻ መኖር እንደሌለባቸውም ያስረዳል፤ ምክንያቱም ለሌሎች ፍቅር ካለን አንሳደብም፤ ለስሜታቸው መጎዳትም እንጨነቃለን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ስድብ ጥልን ያመጣል፤ ያም ወደ ቂም በቀል ይመራል፡፡ ቂም ያለበት ሰው ክፋት በውስጡ ስለሚኖር ኃጢአትን አብዝቶ ይሠራል፤ በመሆኑም ከፈጣሪው ጋር ይጣላል፡፡ የሚያደርገውም ምግባር ሁሉ በፈጣሪው ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ለኃጢአቱ ስርየት ለማግኘትም ወደ ንስሓ አይመራም፡፡
ማመንዘር እንደማይገባ
‹‹ለቀደሙት ሰዎች ‘አታመንዝር’ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን አይቶ የተመኛት ሁሉ ፈጽሞ በልቡ አመነዘረባት፡፡ ቀኝ ዐይንህ ብታስትህ፥ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሁለት ዐይና ሆነህ ወደ ገሃነም እሳት ከምትገባ ይልቅ፥ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና፡፡ ቀኝ እጅህም ብታስትህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ አካልህ ሁሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካልህ አንዱ ቢጠፋ ይሻላልና። ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ፥ የፍቺዋን ደብዳቤ ይስጣት ተብሏል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እርሱ ራሱ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።›› (ማቴ. ፭፥፳፯-፴፪)
ዝሙት በፈጣሪያችን ዘንድ የተጠላ ምግባር ነው፤ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፤ ቅዱስ ለመሆን የሥጋ እና የነፍስ ንጽሕና ያስፈልጋል፤ የሥጋም ድንግልና ለተባረከው ትዳር ማለትም ለተክሊል በቅተው የሚጋቡ ባልና ሚስት የሚያገኙት ክብር እንደመሆኑ ከጋብቻ በፊት ግን ምንም ዓይነት የአካል ግንኙነት እንዲኖራቸው አይፈቀድላቸውም፡፡ (ዘሌ. ፲፱፥፪)
ይህ ብቻም እንዳልሆነ ቃሉ እንዳስረዳን ከሆነ ወንድ ያላገባትን ሴት በሐሳቡም ሊመኛት እንደማይፈቀድለት ነው፡፡ በልቡ ከተመኛት ከእርሷ ጋር ዝሙት መፈጸሙ አይቀሬ ይሆናልና፡፡ የዝሙት ሐሳብ በውስጡ ካለ ደግሞ ጠላት በድክመቱ ሊያስተው ይችላል፤ አመንዝራም ይሆንበታል፡፡ ‹‹ዐይን ተመልክቶ ልብ ይመኛል›› እንደሚባለው ዐይናችን ኃጢአት ከመሥራት ሊታቀብ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን አይቶ መመኘት ኃጢአት አይደለም ብሎ ከማሰብ ይልቅ አውጥተን መጣል እንደሚቀል ከቃሉ እንረዳለን፡፡ በኃጢአት ወደ ሲኦል ከመጣል ይልቅም ማንኛውም የአካል ክፍላችን ተቆርጦ ቢጣል ይሻላል፤ በኋለኛው ዘመን ሥጋችን በሠራው ኃጢአት የሚቀጣው ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ ነውና፡፡
በሐሰት መማል እንደሌለብን
‹‹ለቀደሙት ሰዎች፥ ‘መሐላችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ እንጂ በሐሰት አትማሉ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፡፡ በምድርም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር የእግሩ መረገጫው ናትና፤ በኢየሩሳሌምም ቢሆን፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና ፤ በራሳችሁም ቢሆን አትማሉ፤ ከጠጕራችሁ አንዲቷን ነጭ ማድረግ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና። ነገር ግን ቃላችሁ ‘አዎን፤ አዎን ወይም ‘አይደለም፤ አይደለም’ ይሁን፤ ከእነዚህም የወጣ ከክፉው ወገን ነው።›› (ማቴ. ፭፥፴፫-፴፯)
የእግዚአብሔር ስም የከበረ ነውና በስሙ በሐሰት መማል አይገባም፡፡ እውነትን ደብቆ ሐሰት በሆነ ነገር ስሙን መጥራት ኃጢአት ነው፡፡ እውነት ወደ ሐሰት ከቶ ሊለወጥ እንደማይችል መረዳት አለብን፤ ይህን እያወቅን ብንዋሽ የእግዚአብሔርን ክብር እየተደፋፈርን ስለሆነ የዘለዓለም ቅጣት ይጠብቀናል፡፡
መበቀል እንደማይገባ
‹‹ዳግመኛም ለቀደሙት ሰዎች፥ ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉን በክፉ አትቃወሙት’፤ ቀኝ ፊትህን ለሚመታህ ግራ ፊትህን መልስለት። ቀሚስህንም ሊቀማህ ለሚሻ መጎናጸፊያህን ተውለት። አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለት ምዕራፍ አብረኸው ሂድ። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚወደውን አትከልክለው። ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህንም ጥላ’ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶችችሁን ውደዱ ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ። በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን ያዘንማልና፡፡ የሚወዱአችሁንም ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ፥ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ ሰማያዊው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።›› (ማቴ. ፭፥፴፰-፵፰)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለልጆቹ ሲል ከድንግል ማርያም ተወልዶ በዚህ ምድር መከራ ሲቀበልልን በነበረበት ወቅት ጠላቶቹን በትሕትናና በትዕግሥት አሸንፎአል እንጂ ሁሉን ማድረግ ሲቻለው ስለገረፉት አልገረፋቸውም፤ ስለሰደቡት አልሰደባቸውም፤ ስለቀሉት አልሰቀላቸውም፤ ነገር ግን በዕለተ በምጽአት እንደሚፈርድባቸው መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡
በመሆኑም በክርስቶስ ክርስቲያን ለምንባል ‹‹እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ›› ብሎ እንዳስተማረን ክፋት ለሚያደርጉብን በጎ መሥራት እና የሚረግሙንን መመረቅ እንዳለብን አስረድቶናል፡፡ ሌሎች መጥፎ ነገር አድርገውብናል ብለን እኛም እንደእነርሱ መሆን እንደሌለብንም አስተምሮናል፡፡ እነዚህ ትእዛዞች ሁሉም ሰው ሊተገብራቸው የሚስፈልጉ በመሆናቸው ሊዘነጉ አይገባም፤ ቸሩ አባታችን እግዚአብሔር አዞናልና፡፡ ትእዛዛቱን ከፈጸምን እግዚአብሔር ይረዳናል፤ ሰላምና ፍቅር ጤናንም ይሰጠናልና እኛም ትእዛዛቱን ለመፈጸም አምላካችን፤ እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡