በመቅረዝ ላይ የተቀመጠች መብራት
ግንቦት ፳፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ከመቅረዜ ላይ አድርጌ ለኮስኳት፡፡ እርሷም ቦገግ ብላ አበራችልኝ፡፡ ከመብራቷ የሚወጣውን ብርሃን ስመለከት ውስጤ ሰላም ይሰማኛል፤ ተስፋም አገኛለሁ፤ በጨለማ ውስጥ መብራት ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ በጭንቅ፣ በመረበሽ እና በሁከት ተወጥሮ ለሚጨነቅ አእምሮዬ ወገግ ብላ እንደምታበራ ብርሃኔ ሆነችኝ፡፡ ፍንትው ብሎ የበራውን ብርሃኗን ስመለከት የመኖሬ ትርጕም ይገለጽልኛል፡፡ መቅረዙ ላይ ሆና ሳያት ነገን ማሰብና መመኘት እጀምራለሁና፤ ሌሊቱ እስኪነጋም እጓጓለሁ፡፡
በሰላምና በዕረፍት ያሳለፍኩትን ሌሊት የሚያረጋግጥልኝ ብርሃኗ፣ በጥዋት ወገግ ሲል ምንኛ ያስደስታል! ውስጥን አለምልሞ ፍቅር ያሳድራል፡፡ በቀናው መዓልት በቀኜ ተነሥቼ ስመለከታት “በመቅረዝ ላይ የተቀመጠች መብራት” ሆና ታየችኝ፡፡ መኖሬ በእርሷ በመሆኑ “ሕይወቴ” እላታለሁ፡፡
ስሟን በአንደበቴ ስጠራው ከጣፋጭነቷ የተነሣ በአፌ ውስጥ እንደ ማርና ወተት ሆነልኝ፡፡ በሥሯ ተጠልዬ ስኖርም እንደ ምርኩዝ ድጋፍ ሆናልኝ ወጀቡን አለፍኩኝ፡፡ “ክርስትናዬ” ለእኔ መከታዬም ጋሻዬም ናት፡፡ በመቅረዙ ላይ ሆና እንድታበራልኝ ስለምሻም በቤቷ እኖራለሁኝ፡፡
በመቅረዝ ላይ የተቀመጠችው መብራቴ ብርሃን ትሆነኝ ዘንድ የምትችለውን ያህል እንደምታበራልኝ አዘውትራ ስላሳየችኝ ምን ጊዜም ቢሆን ልጠራጠራት እንደማይገባ አሳውቃኛለች፡፡ በብቸኝነት፣ በባርነት፣ በእስርና በጭንቅ መኖሬን አይታ ባዶ የሆነውን ሕይወቴ በብርሃን የሞላችልኝ ብቸኛ ተስፋዬ እርሷ ናት፡፡
ተስፋ፣ ፍቅርና ሰላም የተሞላው ውስጧ ሕይወትን ሰጥቶኛል፡፡ ሰው ሆኜ ተፈጥሬ ያለ ፍቅር መኖር እንዴት ይቻለኛል? የፍቅር ባለቤት ጌታ የሞተው ለፍቅር አይደለምን? ሕይወትን እስከ መስጠት ያህል የፍቅር መግለጫ ከወዴት ይገኛል? ተስፋዬ የእርሱ ፍቅር፣ በመቅረዙ ላይ ተቀምጣ ዕድሜዬን ሁሉ ታበራልኛለች፡፡
በመስቀሉ ላይ ጠላትን ድል የነሣልኝ ጊዜም ሰላምን በእርሷ ሰጠኝ፡፡ በስሙ ሰይሞና በከበረ ሥጋና ደሙ አትሞ ያበረከተልኝ ውዷ ስጦታ ‘ክርስትናዬ’ “በመቅረዝ ላይ የተቀመጠች መብራት” ናት፡፡
በመቅረዝ ላይ የተቀመጠችው መብራቴ ስታበራልኝ የኖረችው ራሷ የሆነው ጌታ ብርሃኗ ስለሆነ ነው፡፡ ብርሃን ብቻ ካለበት ዓለም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ አንዱ ወልድ ወደ ዚህች መከራ ሥቃይ በበዛባት ምድር መጥቶ ወደ ብርሃን አወጣኝ፡፡ ‹‹ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ የመብራት ብርሃን፥ ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ያበራላቸዋልና፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ›› የተባለው ያ ብርሃን ጌታዬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ (ራእ.፳፪፥፭) በትንሣኤው ትንሣኤዬን፣ በሕይወቱ ሕይወትን ሲሰጠኝ ብርሃን ሆነልኝ፡፡
መቅረዝ ለመብራት ጠንካራ መስቀያ እንደሆነ ሁሉ በጸና እምነት የተመሠረተችው ሃይማኖቴ ለክርስትናዬ ጽኑ ምሰሶ ሆናታለች፡፡ በከበረ ተዋሕዶ ሃይማኖት ኖሬ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብዬ፣ በከፍታ ላይም ሆኜ እንዳበራባት ሃይማኖቴ ለክርስትናዬ መቅረዜ ናት፡፡ በመቅረዜም ያለችው ክርስትናዬ ዘወትር ታበራለች፡፡
ብርሃን በሌለበት ዓለም መኖር ሰው ለሆንኩት ለእኔ እንዴት ይቻለኛል? ብርሃን ከሌለ ጨለማ ይውጠኛልና እፈራለሁ፤ ሰላም አጣለሁና እጨነቃለሁ፤ ተስፋም ቆርጬ ከንቱ እንዳልሆን እሰጋለሁ፡፡ ውስጤ የባዳነት ስሜት የሚፈጠርብኝም ተስፋዬ የሆነችው፣ በመቅረዜ ላይ ተቀምጣ የምታበራው መብራቴን ያጣኋት ጊዜ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስዘናጋ ትርቅብኛለች፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ ድክመቴን አይታ እና ሽንፈቴን ተመልክታ ፍዝዝ ድንግዝ ትልብኛለች፡፡ በዚያች ቅጽበት እንኳን ግን ጭላንጭል መብራቷን እያየሁ ሕይወቴን በመቅረዙ ሆና እንድታበራልኝ በተስፋ እመለከታታለሁ፤ እጠብቃታለሁ፤ እታገሳለሁም፡፡
በመቅረዝ ላይ የተቀመጠችው መብራቴ ያስተማረችኝ ትዕግሥት ብቻ አይለደም፡፡ መከራን መቀበል፣ ችግርን መቻል እና ተስፋ አለመቁረጥንም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ብርሃኗን ገለጠችልኝ፤ መቅረዟ ጽኑ፣ መብራቷ ርቱዕ ነውና፡፡ ‹‹በዓለም ውስጥ ላለ ሁሉ ሰው የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን›› ጌታዬ አንተ በመቅረዜ ላይ ላለችው መብራት ለክርስትናዬ ብርሃን ሆንካት፡፡ (የሰኞ ውዳሴ ማርያም)
ለዓለም ሁሉ ብርሃን ሆነህ በመስቀልህ ቤዛነት ከጨለማ ያወጣኸኝ “በመቅረዝ ላይ በተቀመጠችው መብራት በክርስትና ነውና” መስቀልህን ተሸክሜ፣ በቀራንዮ አደባባይ ተጉዤ፣ ዕፀ መስቀልህን እየተመለከትኩና ተስፋ እያደረኩ በመጨረሻ በክርስትና ሕይወት ብርሃን እንደምቃለሁ፡፡
የኃጢአት ዓለም ‘ባርነት፣ ድቅድቅ እና ጨለማ’ መሆኑን ብርሃንህን ያገኘሁ ቀን አረጋገጥኩ፡፡ ‹‹የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ በጨለማም አይመላለስም›› (ዮሐ.፰፥፲፪) ብለህም ብርሃን የተሞላባትን የክርስትና ሕይወቴን ሰጥተኸኛልና ብርሃን የሆንከው ጌታዬ ክቡር ምስጉን ነህ!!!
ሎቱ ስብሐት!!!