‹‹በሕማም፣ በመከራና መሥዋዕት በመሆን ፍቅራችን ይፈተናል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ
ፍቅርን የሚያውቅ ሰው ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሰው በመጀመሪያ መሥዋዕት ለማድረግ መልመድ ያለበት ከእርሱ ውጪ በሆኑ ነገሮች ማለትም ገንዘቡን፣ ጊዜውን እና ሀብቱን በመለገስ ነው፤ መስጠት ከማግኘት አንድ ነውና፡፡ ለሰዎች ደስታ እንደራሱ የሚጨነቅ እርሱ ፍቅርን ያውቃል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ መሥዋዕትነት መክፈል ካልቻልን ግን ፍቅር አልገባንም ማለት ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔርን ማፍቀር ካልቻልን ደግሞ ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ማግኘት አንችልም፡፡
ፍቅር የሚፈተነው በሕማም በመከራና መሥዋዕት በመሆን ነው፤ መሥዋዕት መሆን የማይችል ሰው የማይወድ ወይም የማያፈቅር ሰው ነው፡፡ የሚወድ ሰው ከሆነ ግን ለመውደድ ማንኛውም ነገር መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡
የአባቶች ሁሉ አባት የተባለው አብርሃም ለእግዚአብሔር ካለው ፍቅር የተነሣ ወገኖቹንና የአባቱን ቤት ትቶ በመውጣት በአንድነት በድንኳን ውስጥ ኖሯል፤ ይሁን እንጂ አብርሃም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያሳየው አንድ ልጁን በመሠዊያው ላይ ባስተኛው ጊዜ ነበር፡፡ እርሱ በልጁ ዙሪያ እንጨቶች ሰብስቦ ካቀጣጠለ በኋላ መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ቢላዋ የያዘ እጁን ቃጥቶ ነበር፡፡
ነቢዩ ዳንኤል እግዚአብሔርን በወደደ ጊዜ ወደ ተራቡ አናብስት ይወረወር ዘንድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ሦስቱ ወጣቶች እንዲሁ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ያረጋገጡት በእቶኔ እሳት ውስጥ በመወርወር የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር የገለጠው እንዲህ በማለት ነው፤ ‹‹አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ፤….›› (ፊል. ፫፥፰-፱)
አባታችን ያዕቆብ ከራሔል ጋር በፍቅር በወደቀ ጊዜ ስለ እርሷ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍሏል፡፡ እርሱ ራሔልን ለማግኘት ለሃያ ዓመታት ያህል በቀን ሀሩንና በሌሊት ቁር መድከም ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሷ ከፍተኛ ፍቅር ስለ ነበረው እነዚህ ዓመታት ለእርሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበር ያለፈለት፡፡ እኛም ለሰው ዘር በሙሉ ሲል በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ ለቀረበው ለኢየሱስ ክርስቶስ የምናቀርበው መሥዋዕት በዚህ ምድር የሚገጥመን ችግር በወጣት፤ የሚደርስብንን መከራ እና ሥቃይ በትዕግስት በማለፍ ነው፡፡
‹‹ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና›› እንደተባለውም ጌታችን ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ ካዳነን በኋላ እኛም የምናቀርበው ለእርሱ መባ እና ምጽዋዕት ኃጢአታችንን ያስተሰርይልናል፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን ለመዘከርም ሆነ ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓል ለማክበር ስንሄድ እግዚአብሔር የምናቀርበው ስጦታ ነው፤ ሆኖም ግን በእምነት እና በበጎ ምግባር ያልተደገፈ ማንኛውም ስጦታ በእርሱ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሁሉን የሚያይ አምላካችን ልባችንን እና ኵላሊታችንን ይመረምራልና የውስጣችንን ክፋት ስለሚያውቅ የምናቀርበውን መሥዋዕት አይቀበለውም፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንን በድፍረት በመርገጣችንም በኋላኛው ዓለም ይቀጣናል፡፡ (ዕብ. ፲፥፫-፬)
አባቶቻችን ሰማዕታትን ካህናት ለእግዚአብሔር ካላቸው ፍቅር የተነሣ ደማቸውን፣ ሕይወታቸውን እና መደላደላቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፡፡ እነርሱ ለእግዚአብሔር የተለየ ፍቅር ስለነበራቸውና ሥቃይን ስለተለማመዱት ፈጽሞ ፈርተው አያውቅም ነበር፡፡
እኛም እንደ አባቶቻችን ለእምነታችንም ሆነ ለሃይማኖታችን ሰማዕት መሆን ባንችል እንኳን በዚህ በምድራዊ ሕይወታችን ማንኛውም ዓይነት ችግር እና መከራ ሲገጥመን ባለመማረር ሥቃዩንም ተቋቁመን ፈተናችንን ማለፍ ይጠበቅብናል፤ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች መዳን ምክንያትም ልንሆን እንችላለን፡፡ ያን ጊዜም በሰላም፣ በፍቀር እና በአንድነት እንኖራለን፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በሰላም እና በፍቅር አንድንኖር ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፤ ‹‹መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው- ክፍል አንድ፤›› በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ