በለንደን ያሉ ምእመናን ለቅዱሳት መካናት እርዳታ ሰጡ፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም ቀጠና ማዕከል

ለገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች መርጃ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያና የምሳ መርሐ ግብር ኅዳር 12 ቀን 2003 ዓ.ም በለንደን ከተማ ተካሂዷል። ይህ ሪፖርት እስከ ተጠናቀረበት ኅዳር 27 /2003 ዓ.ም በጥሬ ገንዘብ £5,000.00 ፣በዓይነት አንድ የአንገት የወርቅ ሐብል እና አንድ የወርቅ የእጅ አምባር ሊገኝ ተችሏል።

lendon.jpg
ፎቶ፦ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለውና ተሳታፊ ምዕመናን

በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል የዩናይትድ ኪንግደም ቀጠና ማዕከል እና ለንደን ከተማ በሚገኘው የስንቄ ሬስቶራንት ትብብር በተዘጋጀው መርሐ ግብር የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የተገኙ ሲሆን “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው’’ የሐዋ ሥራ ምዕ 20፥35 በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመነሳት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አያይዘው የገዳማትን ችግር መጠነ ሰፊነት በማውሳት በቤተክርስቲያናችን አስተዳደር ከ44ቱም አህጉረ ስብከት ከሚገባው ገቢ 5% ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት እርዳታ እየተደረገ መሆኑ ፤ በሌላም መልኩ በተለይም በአዲስ አበባ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላለፉት አስር ዓመታት በዓመት አንድ ጊዜ የወር በዓል ገቢያቸውን ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት መርጃ መዋሉ፤ የአብያተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮች 15% በቋሚነት እንዲያዋጡ መደረጉ እና ሌሎችም ዘዴዎች ለዚህ ተጠቃሽ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ከእርዳታው ስፋት እና ከአብያተ ክርስቲያናቱ ብዛት አንጻር ችግሩን እስከ መጨረሻው መፍታት እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን ረዳት ድርጅት ነው፤ ወጣት ስለሆነ ይሮጣል፤ዘርፈ ብዙ ሥራ አለው። ያስተምራል ፤ ይሰብካል ያሳምናል ፤ ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ይጠብቃል። በተለይም የተቸገሩ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ከመርዳት አኳያ በተለያዩ ምክንያቶች ሀገረ ስብከቶቹ ሊረዷቸው ያልቻሏቸውን ቦታዎች ፈጥኖ በመድረስና ቦታው ድረስ በመገኘት ይረዳል። በመሆኑም በሀገር ውስጥ በእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ማኅበሩ የሚሰራው ሥራ በሊቃነ ጳጳሳቱ ይታወቃል። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን እየሠራ ያለው ሥራ እጅግ ደስ የሚል፤ የሚያስመሰግንና የሞራል ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ እና ቅዱስ ሲኖዶስም በእጅጉ እንደሚደሰትበት ገልጸዋል። ስለሆነም ይህ ዕለት የተቀደሰ ነው፤ እኛ በዚህ ላለነው ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ ጥሩ ዕድል ነው፤ ገዳማቱ እና የአብነት ት/ቤቶቹ መረዳት አለባቸው። ስለዚህ ይህን ችግር ከምንጩ ለመቅረፍ ሁላችሁም በጥልቀት በማሰብ የእርዳታ እጃችሁን እንድትዘረጉ አሳስባለሁ ብለዋል።

ለዚህ ዝግጅት ከአሜሪካን ሀገር ተጋብዘው የመጡት መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” መዝ 67፥21 በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።

(ፎቶ፦ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን)

kesisyared.jpgበዚህ ትምህርታቸው ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ሀገር ፤ ሕዝቦቿም ሕዝበ እግዚአብሔር ለመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ለብዙ ሺህ ዓመታት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ፀንቶ የኖረው ሃይማኖታዊ ባህል ምስክር መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ  ብሉይና ሐዲስን አስተባብራ ይዛ መገኘቷ ከሌላው ዓለም ተለይታ እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህም በላይ ታቦተ ጽዮን ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል፣ ገዳማቱ ፣ አድባራቱና የአብነት ት/ቤቶቹ ምን ያህል የሃይማኖት፣የታሪክ እና የባህል ሀገር እንደሆነች እንደሚያስረግጡ በሰፊው አስረድተዋል። በመጨረሻም እነዚህን ሃይማኖታዊ ታሪክ የያዙ መካናት እና ቅርሶች መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ መሆኑን በማስገንዘብ ወቅታዊና አሳሳቢ ችግር ላይ ላሉት ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባን አሳስባዋል።

ከትምህርቱም ቀጥሎ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች አሁን የሚገኙበት ሁኔታ በሚል በመልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን ሰፋ ያለ ገለጻ ቀርቧል። ገለጻው ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ  መስኮች የነበራቸውን ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ደግሞ ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ያሉባቸውን ልዩ ልዩ ችግሮች የዳሰሰና በመረጃ በመደገፍ የተቀነባበረ ነበር። በዚህ ገለጻቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትተዳደርበት የነበረው የእርሻ መሬት “በመሬት ላራሹ” መቀማቷ፣ የምእመናን ኢኮኖሚያዊ አቅም እየተዳከመ መምጣት እና ኅብረተሰቡ ለአብነት ተማሪዎች ያለው አመለካከት እየተለወጠ መምጣት ገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች ላሉባቸው ችግሮች ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል። ይህ ዝግጅት ታዳሚውን ስለ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ያለውን ግንዛቤ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ በችግሮቹ ዙሪያ ምን እናድርግ የሚል አስተሳሰብን የጫረ ነበር።

በማስከተልም ዲ/ን ሚሊዮን አጀበ በማኅበረ ቅዱሳን የዩናየትድ ኪንግደም ቀጠና ማዕከል ሰብሳቢ በዚህ ዝግጅት በሚገኝ ገቢ ሊረዱ የተመረጡ የሁለት ፕሮጀክቶች ዝርዝር አቅርበው ለተሰብሳቢዎቹ ገላጻ አድርገዋል። በገለጻቸው ማኅበረ ቅዱሳን ከዓላማ እና ተግባሩ ጀምሮ እስከ አወቃቀሩ እና የአባላቱ ስብጥር እንዴት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ቅዱሳት መካናትን እና የአብነት ት/ቤቶችን ለማዳረስ እንደሚችል፣ እነርሱንም ለመደገፍ ያከናወናቸውንና እያከናወነ ያለውን አገልግሎት አጭር ዳሰሳ እና በዚህ ዝግጅት በሚገኝ ገቢ ሊረዱ የተመረጡት ሁለት ፕሮጀክቶች ዝርዝር ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ቀርበዋል። ፕሮጀክቶቹም   በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ከላላ ወረዳ ለሚገኘው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት እና በከፋ ሀገረ ስብከት ቦንጋ ከተማ ለሚገኘው ኪያኬላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የአብነት ት/ቤት የዘመናዊ የከብት ርባታ ፕሮጀክት ናቸው።

የገቢ ማሰባሰቡ ሥራ የተከናወነው በተለያየ መልክ ነበር። የመግቢያ ትኬት ሽያጭ፣ የገዳማት ፎቶዎች ጨረታ፣ የቶምቦላ ዕጣ እና የበጎ ፈቃደኞች የገንዘብ ስጦታዎች ነበሩ።

በመርሐ ግብሩ ብፁዕነታቸውን ጨምሮ፣ በለንደን የደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለው፣ ለዚህ ዝግጅት ከአሜሪካን ሀገር ተጋብዘው የመጡት መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን እና ከተለያዩ አድባራት የመጡ ምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተገኝተዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ዝግጅቱን በማስተባበር የሠሩትን የማኅበሩን አባላት፤ የስንቄ ሬስቶራንት ባለቤትን እና የዝግጅቱን ታዳሚዎች በማመስገን መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል።