ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – ካለፈው የቀጠለ
ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ
አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ባቀረበ ጊዜ፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንደሚያድናቸው በምሳሌው ተረድቶ ተደስቶ ነበር፡፡ ጌታችን ይህን ሲያስረዳን ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደርገ፡፡ አየም፤ ደስም አለው፤›› ብሎ ገለጠልን /ዮሐ.፰፥፶፮/፡፡ እንደ ልቤ የተባለው ንጉሥ ዳዊት በቃል ኪዳኗ ታቦት ፊት በደስታ መዘመሩም እግዚአብሔር ቃል የአዳም ተስፋ ከኾነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን እንደሚያድን በማስተዋሉ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነት መስክረዋል፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ሲል ይናገራል፤ ‹‹ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት ዐጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተንኮታኩቶ ወደቀ፡፡ በታቦቱ በተመሰለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድል ዐዋጅ ታወጀ፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንደዚሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሣ፡፡ ለነገር ጥላ አለውና እግዚአብሔር የማደሪያው ምሳሌ በኾነችው በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በዳጎን ጣዖት ላይ እንዳሳየ እንደዚሁ አጥፊያችንን በማጥፋት እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡ የእግዚአብሔር በግ በኾነው በክርስቶስ እኛን ያዳነን እግዚአብሔር አብ ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡››
ቅዱስ ጀሮም እንደዚሁ ‹‹ቅድስት ድንግል ማርያም ለጌታዋ በእርግጥ እውነተኛ አገልጋዩ ነበረች፡፡ እርሷ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሐሳብ አልነበራትም፡፡ በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ጽላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ንጽሕት ነሽ›› ሲል የእመቤታችንን ንጽሕና አስረድቷል፡፡ እስክንድርያዊው ዲዮናስዮስም ‹‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይኾን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንደዚሁ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የእርሱ ማደሪያ ይኾን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ማደሪያ የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስናና ንጽሕና ያውጅ ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትሞአል፤ ታትሞም ለዘለዓለም ይኖራል›› ይላል፡፡
የሚላኑ ቅዱስ አምብሮስ ደግሞ ‹‹ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በደስታ እየዘለለ ለአምላኩ ዘመረ፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌና ጥላ ካልኾነች የማን ምሳሌና ጥላ ልትኾን ትችላለች? ይህቺ ታቦት በውስጧ የሕጉን ጽላት እንደ ያዘች እንደዚሁ ቅድስት ድንግል ማርያምም የሕጉ ባለቤት የኾነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅፀኗ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የኦሪትን ሕግ በውስጧ እንደያዘች አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ወንጌል የተባለው ክርስቶስን ይዛዋለች፡፡ የመጀመሪያይቱ ታቦት የእግዚአብሔር ትእዛዛትን የያዘች ስትኾን ሁለተኛይቱና አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔር ቃልን በውስጧ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳን ታቦቱ በእርግጥ በውስጥም በውጪም በወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በውስጥም በውጪም በድንግልና የተጌጠች ናት፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የተጌጠችው ምድራዊ በኾነ ወርቅ ሲኾን አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ሰማያዊ በኾኑ ጸጋዎች የተሸለመች ናት፤›› በማለት እመቤታችን የታቦተ ጽዮን ምሳሌ ስለ መኾኗ አስተምሮናል፡፡
አባታችን አዳም ድኅነቱ የሚፈጸመው በሚስቱ ምክንያት እንደ ኾነ ተረድቶ ለሚስቱ ‹‹ሔዋን›› የሚል ስም እንደ ሰጣት ንጉሥ ዳዊትም በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ እመቤታችንን ‹‹አምባዬ መጠጊያ ነሽ›› ሲላት ‹‹ጽዮን›› በሚል ስም እመቤታችንን መጥራቱን ከመዝሙሩ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለ ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡ ‹‹ጽዮን›› ማለት ትርጕሙ ‹‹አምባ፣ መጠጊያ›› ማለት ነውና፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማስጠበቅ ሲሉ በክርስቶስ ስላላመኑ አይሁድ ሲናገር፡- ‹‹እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት አኖራለሁ፤›› አለ /ኢሳ.፰፥፮፬፤ ፳፰፥፲፮/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ትንቢት ስለ ክርስቶስ የተነገረ መኾኑን በሮሜ መልእክቱ ጽፎልናል /ሮሜ.፱፥፴፪-፴፫/፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መኾኑንም በዚህ ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ ዐለት የተባለው ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሹሞአል፤›› በሚለው ኃይለ ቃል ማረጋገጥ ይቻላል /ሉቃ.፪፥፴፬-፴፭/፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ ዐለት የኾነውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን ተብላ መጠራቷንም በእነዚህ ጥቅሶች እንረዳለን፡፡
ቅዱስ ዳዊትና ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኃጢአትን ያርቃል፤›› /መዝ.፲፫፥፲፤ ኢሳ.፶፱፥፳/ በማለት ስለ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒትነት አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ይህን ምሥጢርም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ፲፩፥፳፮ ላይ ጠቅሶታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም መኾኗን ለማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን የተወለደው ከእመቤታችን ነውና፡፡ ‹‹መድኀኒት›› የተባለው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹… በዳዊት ከተማ መድኀኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ፤›› /ሉቃ.፪፥፲/ በማለት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ገለጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ኢየሱስ›› ማለት ‹‹መድኀኒት›› ማለት ነው /ማቴ.፩፥፳፩/፡፡ በዚህ መሠረት ነቢያቱ ‹‹መድኀኒት ከጽዮን ይወጣል፤›› ሲሉ መናገራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች የሚኖሩባት ሥፍራ ናት፡፡ አንደኛው ሰው የሔዋን ዐይነት ዐይኖች ስላለው በእነዚህ ዐይኖቹ ድንጋዩንና እንጨቱን አምላክ ነው እያለ ይገዛለታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የቅድስት ድንግል ማርያም ዓይነት ዐይኖች ስላሉት ክርስቶስ ኢየሱስን ይመለከታል ለእርሱም ይገዛል›› ብሎ ያስተምራል /ውርስ ትርጕም/፡፡ እኛም የእመቤታችን ዓይነት ዐይኖች ስላሉን፤ እይታችንም ፍጹም፣ ንጹሕና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ስለ ኾነ ታቦታትን ስንመለከት እመቤታችንን፤ እመቤታችንን ስንመለከት ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመለከተዋለን፡፡ ምእመናን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች በመኾናችን በጸጋ የክርስቶስ ወንድሞች ተብለን ተጠርተናል፡፡ ይህም የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች መኾናችንን ያመላክታል፡፡ ‹‹ወላጁን የሚወድ ከእርሱ የተወለደውንም ይወዳል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /፩ኛዮሐ.፭፥፩/ እኛ ኦርቶዶክሳውያንም ቅድስት ድንግል ማርያምን ስለምንወዳት ከእርሷ በሥጋ የተወለደውን ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንወደዋለን፡፡ እግዚአብሔር አብን እንደምንወድና እንደምናመልከው ዅሉ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንደ ባሕርይ አባቱ እኩል እንወደዋለን፤ እናመልከዋለን፡፡ በአጠቃላይ ሥላሴን እንደምንወድ ዅሉ ከሥላሴ አብራክ የተወለዱ ክርስቲያኖችንና በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረውን የሰውን ፍጥረት እንወዳለን፡፡
በአጠቃላይ ስለ ታቦተ ጽዮን የተጻፉ ዅሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጥላና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ነገር ግን ጽዮን የሚል ንባብ ዅሉ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚናገር ነው ማለታችን አይደለም፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን ሲናገር ስለ እርሱ የተነገሩ ምሥጢራን ብቻ መርጦ እንደ ተጠቀመና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽዮን የሚል ምንባብ በሙሉ ስለ ጌታችንና ስለ እመቤታችን የተጻፈ ነው ብሎ እንዳልተረጐመ ዅሉ፣ እኛም ጽዮን የሚል ቃል ባገኘን ቍጥር ስለ ድንግል ማርያም የተጻፈ ነው ብለን አንተረጕምም፡፡ እንደዚህ የምንል ከኾነ ግን ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንገባለንና፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በዅላችን ላይ ይደር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡