ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ? የጾመ ፍልስታ ወቅት እንዴት ነበር? እንኳን አደረሳችሁ! የክረምት ወቅት አልፎ አዲሱን ዓመት ልንቀበል ቀናት ብቻ ቀርተውናል! እህቶቻችንን ለዚህ ያደረሰንን ፈጣሪ በዝማሬ ያመሰግናሉ፤ ልጆች! ለመሆኑ አበባ አየሽ ወይ? እያልን የምንዘምረው “የተዘራው ዘር በቅሎ ቅጠል ከዚያም ደግሞ አበባን ሰጥቷል፤ ቀጥሎ ደግሞ ፍሬን ይሰጣል” በማለት የምሥራችን እያበሠሩ ለዚህ ያደለንን ፈጣሪ ያመሰግናሉ፡፡ ልጆች! ሌላው ደግሞ መዘንጋት የሌለባችሁ ነገር ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባችሁ ነው፤ መልካም!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ ታሪክ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ነው፤ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እናትና ቅድስት እሌኒ አባቷ ቅዱስ ደረሳኒ ይባላሉ፡፡ የትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ በቡልጋ አውራጃ ነው፡፡ እናትና አባቷ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ መልካም ምግባር የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ግንቦት ፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ቀንም ቅድስት ከርስቶስ ሠምራን ወለዱ፡፡ በሥነ ምግባር እና ትምህርተ ሃይማኖት እያስተማሯት አደገች፡፡ ልጆች! በሥነ ምግባር ታንጾ ትምህርተ ሃይማትን ተምሮ ማደግ መልካም ነው፡፡ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቡ! ጨዋዎች፣ ታዛዦች ልጆች ሁኑ! ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለወላጆቿ እየታዘዘች በሥርዓት ካደገች በኋላ ትልቅ ሰው ስትሆን ሠምረ ጊዮርጊስ የተባለው ባል አገባች፡፡ ከዚያም ፲፩ ዐሥራ አንድ) ልጆችም ወለዱ፡፡ ከዚያም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በምግባር በሃይማኖት ጸንተው ኖሩ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጾመኛ፣ ጸሎተኛና ደግ ሴት ነበረች፡፡ ለሠራተኞቿም ታዝን ነበር፤ ለነድያንም ትመጸውት ነበር፤ አንድ ቀን ግን ከሠራተኛዋ መካከል አንዱ ድንገት ሞተባት፡፡ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፤ “ይህቺን የሞተች ሠራተኛዬን ካስነሣህልኝ ከአሁን በኋላ ዘመኔን ሙሉ ሳገለግልሀ እኖራለው” አለች፡፡ በጭንቀት ውስጥ ሆና በጾም፣ በጸሎትና በልቅሦ ተማጸነች፡፡ ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! በዚህን ጊዜ የሞተችው ሠራተኛዋ ተነሣች፤ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራም በዚህ ድንቅ ተአምር ተደሰች በገባችው ቃል መሠረት ያላትን ነብረቷን ሁሉ ጥላ ወደ ደብረ ሊባስ ገዳም ሄደች ቅዱስ ሚካኤል እየመራት ኅብስት ( የምትመገበው) ከሰማይ እያመጣላት በጾም በጸሎት ተጋድሎዋን ጀመረች፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ጣና ሐይቅ ቅዱስ ሚካኤል አደረሳት፡፡ ልጆች! በደስታ፣ ትኖርበት ከነበረበት ቤት ወጥታ እግዚአብሐርን ለማገልገል፣ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ ፍቅር ልትጸልይ ወደ ገዳም ሄደች፤ በጣም በደስታ በድሎት ይኖር የነበረው ሰውነቷ ተጎሳቆለ ያን ሁሉ መከራ ታግሣ ኖረች፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሰዎች ልጆች ድኅነት ፈጣሪን ተማጽና ምሕረትን አሰጥታለች፤ በዘመኗ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አድርጋለች፤ በአንድ ወቅት በክፉ ሥራው አጋንንት (ሰይጣን) ያስጨንቀውን ሰው ከእርኩስ መንፈስ እንዲላቀቅ፣ ፈጣሪውን ስለከዳው ሰው ጸልያ እግዚአብሔር ይቅር እንዲለው አደረገች፡፡ ልጆች! ይገርማችኋል እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በሰዎች ላይ ክፉ የሚያደርገውን ሰይጣን (ዲያቢሎስ) ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ጠይቃ ነበር፤ አይደንቅም! ልጆች! እኛ ዛሬ የተጣሉ ስንት ጓደኞቻችንን አስታረቅን? አስተውሉ ልጆች! እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን ክፉ የሚያደርግብንን ሰይጣን ከፈጣሪ ጋር ለማስታረቅ ሞክራለች፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ባሕር ውስጥ በመሆን ለዓለም ሰላምና ለሰው ልጆች ፍቅር እንዲኖር ለብዙ ጊዜ በጾምና በጸሎት ስትኖር ሰይጣን ከዚህ ምግባር ሊያስወጣት ሞክሮ አልተሳካለትም፤ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃት ድል አደረገችው፡፡ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እንግዳን ተቀባይ፣ በመከራም ታግሣ የኖረች፣ በትሕትና ሕይወት የኖረች እናታችን ናት፤ ከዚህም በኋላ ስድስት ክንፍ በጸጋ ተሰጣት፣ በጉድጓድ ውስጥ ገብታ በጸሎት፣ በስግደት፣ በጾም ለ፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ዓመታት የተጋደለች እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ገባላት ስሟ ጠርቶ የተማጸነ፣ ዝክሯን ዘከረ፣ በስሟ ከታነጸው ገዳማት ሄዶ የተሳለመን እንደሚምር ቃል ኪዳን ገባላት፡፡ በነሐሴ ፳፬ (ሃያ ዐራት) ቀንም ዐረፈች፤ መቃብሯም በጣና ደሴት በስሟ በታነጸው ገዳም( ቤተ ክርስቲያን) በክብር ዐረፈ፤ አምላካችን በረከት ረድኤቷን ያድለን!
ውድ የእገዚአብሔር ልጆች! ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ታሪክ ምን እንማራለን? ወላጆቻችንን እኛ በሥርዓት፣ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በንጽሕና አድገን የእኛን መልካም ነገር፣ ደስታ፣ ወግ፣ ማዕረግን ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ እኛም በጥሩ ሥነ ምግባር ራሳችንን ከከንቱና ከክፉ ነገር በመጠበቅ መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ወላጆቻችን ስለሚያደርጉልን ነገር ሁሉ ከእኛ ምንም ዓይነት ክፍያን አይጠብቁም፤ እነርሱ ደስታ የእኛ መልካም፣ ጎበዝ፣ ብልህ፣ በእምነቱ የጸና፣ በምግባሩ የጎለበተ ልጅ ሆነን ማየቱ ብቻ የእነርሱ ደስታ ነው፡፡ የተጣሉ ሰዎችን ማስታረቅ፣ ለሰዎች መልካም ማድረግ፣ ጸሎት አብዝቶ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡
እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን ታሪክ የሕይወት ተጋድሎና ስለ ክብራቸው የምንማረው እኛም እንደነርሱ ራሳችንን ከክፉ ነገር ጠብቀንና መልካም ሠርተን መኖር እንዲቻለን ነውና፡፡ በምንማረው ትምህርት ቅዱሳንን አርአያ ልናደርጋቸው ይገባል፤ ትሑታን፣ ሰዎችን አከባሪ፣ በመሆን በቤተ ክርስቲያን አያገለገልን ልናድግ ይገባናል፡፡ እንግዲህ ለዛሬ በዚህ አበቃን!
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ረድኤት በረከቷን ይክፈለን፡፡
መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ!
(ምንጭ፡- መዝገበ ቅዱሳን መጽፍ ገጽ ፫፻፶፰- ፫፻፷፫)
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!