ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት

ሐምሌ፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

አባታችን አብርሃም እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ድንኳን ሠርቶ እንግዶች እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን፣ ርኅራኄውን፣ ትሕትናውን አይቶ ሊፈትነው አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ የተጎዳ ሰው መስሎ፣ ራሱን ፈንክቶ፣ ከጎዳና ላይ ቆሞ አብርሃም ቤት ለሚመጡ እንግዶች “ወዴት ትሄዳላችሁ? እያለ ይጠይቃቸው ጀመር፡፡ እነርሱም ወደ አብርሃም ቤት እንደሚሄዱ በገለጹለት ጊዜ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደተወ፣ ልብሱን ገፎ እንደመለሰው ነገራቸው፡፡ እንግዶቹም እውነት መስሏቸው እያዘኑ ይመለሱ ነበር፡፡ በዚህ የተሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት መምጣት ቀረ፡፡ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔር ያለ እንግዳ አይበላምና ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡

በሦስተኛው ቀንም ይህን ደግነቱ እግዚአብሔር ተመልክቶ በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገለጡለት፡፡ አብርሃምም ከድንኳን ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሰገደና “አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈው” አለ፡፡ እነርሱም “ስለ ደከመን አዝለህ ውሰደን” አሉት፡፡ አንዱን አዝሎ ከገባ በኋላ በአምላካዊ ግብር ሁለቱም ገብተው ተገኙ፡፡ አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሚስቱ ሣራ ፈጥኖ ገባና “ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ” አላት፡፡ አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፤ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፤ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኮለ፡፡ እርጎና ማር፣ ያን ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፤ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም በፊታቸው ቆሞ ያሳልፍላቸው ነበር፤ እነርሱም በሉ፡፡

መብላታቸውም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃምም የበሉ መስለው ስለታዩት ተመግበዋል ተባለ እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ የሚስማማቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ሥላሴ ምግብ በሉ ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡ ከዚያም የታረደው ጥጃ ተነሥቶ “ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ” ብሎ አምላክን አመስግኗል፡፡
ሊሄዱም ሲሉ ከሦስቱ አንዱ እግዚአብሔር ቃል “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅ ታገኛለች” አለ፡፡ ለጊዜው ስለ ልጁ ይስሐቅ ሲሆን ፍጻሜው ግን እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው ሲነግረው ነው፡፡ ይህ ታሪክ የተፈጸመው ከ፳፻-፲፰፻፶ (2000-1850) ዓ.ዓ. አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ ብዙ ትምህርት እንማራለን፡፡ ለምሳሌ ያህልም የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡፡

ሀ. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት

አንድነቱና ሦስትነቱ እንዴት ነው? ቢሉ በዘፍጥረት ፲፰፥፪-፭ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል መመልከት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ “ዓይኑንም ባነሣ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳን ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፤ ወደ ምድርም ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “አቤቱ በፊትህስ ባለሟልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈው፤ ውኃ ላምጣላችሁ እግራችሁንም ታጠቡ” የሚለው ኃይለ ቃል ሦስትነቱ “ሦስት ሰዎች… ሊቀበላቸው፣ ወደ እነርሱ” የሚሉት ሐረጋት ሦስተነቱን ሲገልጽ “በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ” የሚለው ዓረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ሦስት መስፈሪያ የሦስትነት፣ እንጎቻው (ዳቦ) አንድ መሆኑ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡

ለ. እግዚአብሔር ለአብርሃም ልጅ እንደሚወልድ ያበሠረበት ቀን ነው፡፡

አባታችን ጻድቁ አብርሃም እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ አበ ብዙኀን (የብዙዎች አባት) እንደሚሆን ቢነግረውም ልጅ ግን አልነበረውም፡፡ በዚህ እንግዳ ተቀባይነቱና መልካም ሥራው እግዚአብሔር በእንግድነቱ ከቤቱ በገባ ጊዜ በእርጅናው ልጅ እንደሚወልድ (ልጅ እንደሚሰጠው) አበሠረው፡፡

እግዚአብሔር እንደ አብርሃም ቅን ልቡና ያላቸውና ለጋሾች ለሆኑ፣ ምጽዋት መስጠትና እንግዳ መቀበል የዘወትር ልማዳቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እንደሚገኝ እንዲሁም ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍት፣ ቤትንም በበረከት እንደሚሞላ እንዲሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ እንረዳለን፡፡

ሐ. የአብርሃም ድንኳን

አባቶቻችን ሊቃውንት እንደተረጎሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚ ያርፍበት፣ ይመገብበት እንደነበር ሁሉ እመቤታችን የነፍስም የሥጋም መድኃኒት፣ የዘለዓለም ማረፊያ፣ እውነተኛ መብልና መጠጥ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ቀትር በሆነ ጊዜም በስድስት ሰዓት አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በአብርሃም ድንኳን እንደገቡ፣ በስድስተኛው ወርም ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተልኳልና፡፡ (ሉቃ.፩፥፳፮)

በሐምሌ ሰባት (፯) ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት ተገኝቶ እንደባረከው ቅን ልቡና ያላቸውን፣ ለጋሾች ለሆኑ፣ ምጽዋትን ለሚያቀርቡ፣ እንግዳ መቀበል የዘወትር ልማዳቸው ላደረጉ ሰዎች በቤታቸው ይገባል፡፡ የተዘጋውንም ማኅፀን እንደከፈተ ቤቱንም እንደባረከ አይተናል፡፡ ዛሬም እኛም ለተራቡ በማብላት፣ ለተጠሙ በማጠጣት፣ ለታረዙ በማልበስ፣ በመመጽወትና በመሳሰለው ተግባር መኖር፣ በቀና አስተሳሰብ መጓዝ እንዳለብን መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

የአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ቸርነታቸውና ምሕረታቸው አይለየን፤ አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!!!