ቅዱስ ፓትርያርኩ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
ጳጉሜን 4 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ2006 ዓ.ም. አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡
ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚይዝ በመግለጽ ከ2005 ዓም. ዘመነ ማቴዎስ ወደ 2006 ዓ.ም. ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
አዲሱን ዘመን ሥራ በመሥራት ማሳለፍ እንደሚገባ ሲገልጹም “እያንዳንዱ ሰው ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዓብይ ነገር በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሓላፊነቴ ምን ሠራሁ፤ ምንስ ቀረኝ? ለአዲስ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፡፡ ሥራ መሥራት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ነውና፡፡ እያንዳንዱ ሰው ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ያለውንና በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ወጣቶች ፍልሰትና እልቂትን ለመከላከል ሕዝቡ ልጆቹን ማስተማር እንዳለበትም በመልእክታቸው ጠቁመዋል፡፡
በወሊድ ወቅት ለሞት የሚጋለጡ እናቶችና ሕፃናትን አስመልክቶም በሀገራችን የእናቶችና ሕፃናት ሞት ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ እየታካሔደ ያለውን እንክብካቤ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡