ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ
ግንቦት ፲፩ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም
ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ በየዓመቱ ግንቦት ፲፩ ቀን ከሚታወሱ ቅዱሳን መካከል የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና፣ ቅድስት ታውክልያ፣ ቅዱስ በፍኑትዩስ፣ አባ አሴር፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ብፅዕት አርሴማ፣ ቅድስት ኤፎምያ፣ ቅድስት አናሲማ፣ ቅድስት ሶፍያ፣ አባ በኪሞስ፣ አባ አብላዲስ እና አባ ዮልዮስ ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በዛሬው ዝግጅታችን የቤተ ክርስቲያን እንዚራ፣ የኢትዮጵያ ብርሃን እየተባለ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያናችን ድምቀት፣ የአገራችን ኩራት የሆነውን የጥዑመ ልሳን፣ ኢትዮጵያዊ ማኅሌታይ የቅዱስ ያሬድን ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤
በ፭፻፭ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) አንድ ቅዱስ ተገኘ፤ ይኸውም ቅዱስ ያሬድ ነው /ገድለ ቅዱስ ያሬድ/፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ ትምህርት ሊማር ቢሔድም ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ መምህሩ ይገርፉት፣ ይገሥፁት ነበር፡፡ እርሱም ከትምህርቱ ክብደት ባለፈ የመምህሩ ተግሣፅ ሲበረታበት ጊዜ ከአባ ጌዴዎን ቤት ወጥቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ደክሞት ከአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፡፡
ከዛፉ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንድ ትል ፍሬውን ለመመገብ ወደ ዛፉ ሲወጣ፣ ነገር ግን መውጣት ስለተሳነው በተደጋጋሚ ሲወድቅ ቆይቶ ከብዙ ሙከራ በኋላ ከዛፉ ላይ ሲወጣ፣ ፍሬውንም ሲመገብ ይመለከታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ትጋት ከአየ በኋላ እርሱም በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ ትምህርቱን እንደገና መቀጠል ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎት እየተማጸነ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜን አጠናቆ መዓርገ ዲቁና ተቀበለ፡፡
እግዚአብሔርም የክብር መታሰቢያ ሊያቆምለት ወዷልና ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ልኮ በሰው አንደበት እንዲያናግሩት አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ካናገሩት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡትና በዚያም የሃያ አራቱን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ማኅሌት ተማረ፡፡ ወደ ምድርም ተመልሶ በአክሱም ጽዮን በሦስት ሰዓት ገብቶ በታላቅ ቃል፡- ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፡፡ ዳግመኛም እንዴት መሥራት እንዳለበት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው፤ አስተማረው እያለ በዜማ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ድምፅ የሰሙ ሁሉ ጳጳሳቱና ነገሥታቱ ሳይቀሩ ካህናቱም ምእመናኑም ወደርሱ ተሰብስበው ሲሰሙት ዋሉ፡፡ ይህንንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራው፤ ይኸውም በዜማ ትምህርት ቤት ከቃል ትምህርቶች አንደኛው ሆኖ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
መጽሐፈ ስንክሳር ይህንን ሊቅ፡- አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው ይለዋል፡፡ ከመላእክት ወገን የሆኑት ሱራፌል እግዚአብሔርን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያለ በመላእክት ቋንቋ እግዚአብሔርን አመስገኗልና፤ ደግሞም የተማረው ከእነርሱ ነውና የሱራፌል አምሳላቸው ተባለ፡፡ እርሱም፡- ሃሌ ሉያ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሓቲከ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ የምስጋናህ ስፋት ሰማይና ምድርን መላ፤ÃÃÂ /ኢሳ.፮፥፫/እያሉ ሲያመሰግኑ ከመላእክት የሰማሁት ምስጋና ምንኛ ድንቅ ነው? በማለት ዜማውን የተማረው ከመላእክት መሆኑን በድርሰቱ መስክሯል፡፡
ከዚያ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በሰንበታት፣ እንዲሁም በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል በዓላት የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ፡፡ የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ሁሉ ከነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች እንደማይወጡ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡
በአንዲት ዕለት ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ፣ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን በዘመኑ ከነበረው ከንጉሥ ገብረ መስቀል ፊት ቆሞ ሲዘምር ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት (የሚያደርገዉን ባለማወቁ) የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው፡፡ ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ቢፈስስም ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር፡፡
ንጉሡም ያደረገዉን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎÃÃÂ ስለፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገዉን ሁል ለምነኝ እያለ ተማጸነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኩስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው፡፡ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘ፡፡ ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም ነገር ግን መሐላዉን ማፍረስ ስለከበደው እያዘነ አሰናበተው፡፡
ከዚያም ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ፡- ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት፤ ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽÃÃÂ እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን የእመቤታችን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ፡፡ ይህንን ጸሎት ሲያደርስም አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሔዶ (ሰሜን ተራሮች አካባቢ) በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን ለሚጠራ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፤ ከዚያም በሰላም ዐረፈ፡፡ /ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፩/
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በገድለ ቅዱስ ያሬድ ላይና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደመዘገቡልን ግንቦት ፲፩ ቀን ቅዱስ ያሬድ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ያረፈበት ቀን ነው፤ እዚህ ላይ ግን አከራካሪ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም አንደኛው ቅዱስ ያሬድ ሞቶ ተቀብሯል የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ እስከነ ነፍሱ ተሠወረ እንጂ አልሞተም የሚል ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሞተ የሚሉ ወገኖች ከሚጠቅሷቸው ማስረጃዎች ውስጥ በመጽሐፈ ስንክሳር፡- ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ያሬድ ማኅሌታይ፤ በዚህች ዕለት ማኅሌታይ ያሬድ ዐረፈ፤ እና ወእምዝ አዕረፈ በሰላም፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ዐረፈ የሚሉት ሐረጋት የሚገኙ ሲሆን፣ ተሠወረ የሚሉት ደግሞ እዚያው ስንክሳሩ ላይ፡- ወእምዝ ሖረ ሀገረ ሰሜን ወነበረ ህየ ወፈጸመ ገድሎ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሒዶ ገድሉን በዚያ ፈጸመ፤ ተብሎ የተገለጸውን እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡
በእርግጥ ቃሉን በትኩረት ለተመለከው ሰው ዐረፈ ማለት ሞትን ብቻ ሳይሆን እንደነ ሄኖክ ከዚህ ዓለም ጣጣና እንግልት ተለይቶ በሕይወት እያሉ (ሳይሞቱ) ተሠውሮ መኖርንም ያመለክታል፡፡ ገድሉን በሰሜን አገር ፈጸመ የሚለውም መሠወሩን ብቻ ሳይሆን መሞቱንም ሊያመለክት ይችላል የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደሚያስተምሩን እነእገሌ ቀበሩት የሚል ቃል ስለማይገኝ ቅዱስ ያሬድ ተሠወረ እንጂ ሞተ ተብሎ አይነገርለትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ እርሱ በተሠወረበት ተራራ እስከ አሁን ድረስ የከበሮ (የማኅሌት) ድምፅ ይሰማል፤ የዕጣን መዓዛ ይሸታል፡፡ ይህም ቅዱሱ ከሰው ዓይን ተሠውሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡
የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችም ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለአገርም ድንቅና ወደር የሌላቸው ሀብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዜማ ድርሰቶቹ (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት) እንደሌሎቹ ቅርሶች ሁሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ርብርብ በያደርጉ መልካም ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ ዜማ የሚደምቀው በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ ሲመዘገብ ዜማውን ከበዓሉ ለይቶ ማስቀረት የታሪክ ተወቃሾች ያደርገናልና ሁላችንም እናስብበት እንላለን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በአባታችን በቅዱስ ያሬድ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘለዓለም ትኑር፤ አሜን፡፡