ቅዱስ ማርቆስ
- ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ
- በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን በታላቅ ኃይልና ሥልጣን
- አሰሮ ለሰይጣን ሰይጣንን አሠረው
- አግዐዞ ለአዳም አዳምን ነጻ አወጣው
- ሰላም ሰላም
- እምይእዜሰ ከእንግዲህ
- ኮነ ሆነ
- ፍስሐ ወሰላም ደስታና ሰላም
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ለዚህ ዕለት አደረሳችሁ! በእግዚአብሔር ምሕረት፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችን ተበሥሮልን ከዛሬ ዕለት ደርስን! በቸርነቱ ለዚህ ያደረሰን ፈጣሪ ይመስገን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላቸሁ የወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስን ታሪክ ነው፡፡ በሚያዚያ ወር ዓመታዊ ክብራቸው ከሚከበርላቸው ቅዱሳን አንዱ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስ አባቱ አርስጦቡሎስ እናቱ ደግሞ ማርያም ይባላሉ፤ በልጅነቱም በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን የላቲን፣ ግሪክ፣ የዕብራይጥን ቋንቋዎችን ተምሯል፤ጌታችን በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቅዱስ ማርቆስ ገና ታዳጊ ወጣት ነበር፤ ወላጆቹን እየታዘዘና እያገለገለም አድጓል፡፡ ጌታችን በምሴተ (ጸሎተ) ሐሙስ የአይሁድን ፋሲካ ለማክበር ቤት እንዲያሰናዱለት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሲልክ ቤቱን የሚያሳያቸው ልጅ እንደሚያገኙ ነግሯቸዋል። ይህም ልጅ ቅዱስ ማርቆስ ነበር ፤ ‹‹…ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ያገናኛችኋል፤ ተከተሉት፤ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት…›› (ማር.፲፬፥፲፫ ) ሊቃውንት አባቶች በትርጓሜ ይህ ልጅ ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ተርጉመውልናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ማርቆስ ጌታችን በተያዘበት ምሴተ ሐሙስ ተከትሎትም ነበር ‹‹… ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር…..›› (ማር. ፲፬፥፶፩ ) ይህ ጎበዝ የተባለ ቅዱስ ማርቆስ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስ የቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር፤ጌታችን የሐዲስ ኪዳን ቁርባን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠበት ቤት እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ለአንድ መቶው ሃያ ቤተሰብ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሲልክ፤ ( ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት) በማርቆስ እናት በማርያም ባውፍልያ ቤት በነበሩ ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ቤታቸው የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ተብላለች፡፡
ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹…ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው፤ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› በማለት አዘዛቸው፤(ማቴ.፳፰፥፳) ቅዱሳን ሐዋርያትም ዓለምን ዞረው እንዲያስተምሩ ባዘዛቸው መሠረት ለማስተማር ሲሄዱ ቅዱስ ማርቆስ መጀመሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ከዚያም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር አብሮ ተጉዟል፤ ከእነርሱም የማስተማር ልምድን ከወሰደ በኋላ ወንጌልን ለመስበክ ለብቻው ወደ እስክንድርያ ተጓዘ፤ይገርማችኋል ልጆች! በዚያን ወቅት የእስክንድርያ ከተማ ነዋሪዎች የጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፤ ወደ ከተማው ከገባ በኋላ እንዴት አድርጎ ሕዝቡን እንደሚያስተምር ሲዘዋወር ያደረገው የጠፍር ጫማው ተበጠሰ፤ ወደ ሰፊም ሄደ፤ ጫማ ሠሪውም እየሰፋ ሳለ እጁን ወስፌ ወጋው፤ ከዚያም ‹‹ኤስታኦስ›› አለ ! ውድ የእግዚአብሔር ልጆች ምን ማለት መሰላችሁ? ዮናናውያን በሚባሉ ሰዎች ቋንቋ ‹‹ኤስታኦስ›› አንድ አምላክ ማለት ነው፤ ቅዱስ ማርቆስም ከጫማ ሰፊው ይህንን በመስማቱ ጠጋ አለና‹‹ አንድ አምላክን ታውቀዋለህ?›› አለው ሰውየውም ሲሉ እንደሚሰማ እንጂ ምን እንደሆነ እንደማያውቅ ገለጸለት፤ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ የታመመ እጁን በተአምራት ፈወሰለት፡፡
ከዚያም ወንጌልን አስተማረው፤ እውነትን አሳውቆ ከጣዖት አምልኮ መለሰው፤ ሰውየውም ደስ ብሎት ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ቤተሰቦቹንም አስተምሮ አጠመቃቸው፤ብዙዎችም ከተሳሳተ መንገድና ከጣዖት አምልኮ ተመለሱ፤ የዚህ ሰው ቤትም በእስክንድርያ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ሆነች፤ ጸሎት የሚጸልዩባት ወንጌል የሚማሩባት ሆነች፡፡ ብዙ ሰዎችም በክርስትና እምነት አመኑ፡፡ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሌላ ሀገርም ለማስተማር ተጓዘ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከብዙ ጊዜ በኋላ ያመኑት ምእመናን (ክርስቲያኖች) የትንሣኤን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በደረሰ ጊዜ አብሯቸው እንዲያከብር ቅዱስ ማርቆስን ጠሩት እርሱም በመጣ ጊዜ ጣዖት አምላኪዎች ያዙት፤ ጌታችን አስቀድሞ በእርሱ የሚያምኑትን መከራ እንደሚገጥማቸው መጽናትም እንዳለባቸው እንዲህ አስተምሯቸው ነበር፤ ‹‹…ይገድሉአችሁማል፤በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል..›› (ማቴ. ፲፥፳፪)፤ ከዚያም ጣዖት አምላኪዎቹ ቅዱስ ማርቆስን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሠረገላ ጋር አሥረውት መሬት ለመሬት ይጎትቱት ጀመር፤ ብዙ ካንገላቱት በኋላ ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) በ፷፰ (ስድሳ ስምንት) ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ልጆች! ጣዖት አምላኪዎቹ ይህ አልበቃ ብሏቸው የቅዱስ ማርቆስን አስክሬን ሊያቃጥሉ ሲሉ ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ በተናቸው፤ክርስቲያኖቹም በክብር አንሥተው በቤተ ክርስቲያን ቀበሩት፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል …›› ባለን መሠረት ምእመናን በረከቱን እናገኝ ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ማርቆስን የዕረፍት መታሰቢያ በዓል ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) ቀን ታከብረዋለች፡፡ (ማቴ.፲፥፵፪) በረከቱ ይደርብን፤
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ማርቆስ ከአራቱ ወንጌላት አንዱን የጻፈው እርሱ ነው፤የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር በነበረ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲያስተምር እርሱ ይጽፍ ነበር። (ማስታወሻ ይይዝ ነበር) አያችሁ ልጆች! ቃለ እግዚአብሔር ስንማር ከመምህራን አንደበት የሚወጣውን ትምህርት በማስታወሻ ልንመዘግብ ይገባል፤ ቅዱስ ማርቆስ ማስታወሻ በመያዙ ወደ መጽሐፍ ቀየረው፤ ለሌሎቻችንም ጠቀመን፤ ስንማር የምንጽፈው (የምንይዘው ማስታወሻ) ትምህርቱ ሲሰጥ በቦታው ላልነበሩ ይጠቅማል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከቅዱስ ማርቆስ ምን እንማራለን? ለወላጅ እየታዘዙ ማደግ፣ ከአባቶች ምንማራቸውን በማስታወሻ መመዝገብ፣ ያወቅነውን ለሌሎች ማሳወቅ፣ ሰዎችን መርዳት፣ ስለእውነት መመስከር እንማራለን!
አምላከ ቅዱስ ማርቆስ በረከቱን ያድለን አሜን!!! ቸር ይግጠመን ይቆየን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!