ቅዱስነታቸው የመጀመሪያ እንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላለፉ
የካቲት 28 ቀን 2005ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአብይ ጾምን በማስመልከት የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡
ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን ከፊታችን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓብይ ጾም ወራት ጎጂ ከሆኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የሆነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡
የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኃይል ለመታዘዝ መዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ በጾም ወራት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ያሏቸውንም ሲጠቅሱ “ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊሆን የሚችለው ርኅራኄን፤ ቸርነትን፤ ምጽዋትን፤ ፍቅርን፤ ስምምነትን፤ ትሕትናን፤ መረዳዳትን፤ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደሆነ ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡን የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢሆኑም በተለይ መሠረታዊ የሆነ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፤ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የሚቻለንን በመለገስ፤ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡