ቅዱሰ ኤጲፋንዮስ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፲፭ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? የዓመቱ የትምህርት ወቅት እየተገባደደ የፈተና ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ ተፈትናችሁ በጥሩ ውጤት ወደ ቀጣዩ ክፍል ለመዘዋወር እየበረታችሁ ነውን?
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች በርትቶ የተማረ ያጠና በመጨረሻ በጥሩ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል ይዘዋወራል፤ ውጤቱ ጥሩ ከሆነ ደግሞ ይሸለማል! እናንተስ ይህን ለማግኘት ዝግጁ ናችሁ? ከሆነ መልካም!
ልጆች! በቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ ‹‹ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና..›› (ማቴ. ፮፥፯) እንግዲህ በትምህርት ወቅት መምህራን ሲዘሩት የነበረውን እውቀት በአግባቡ የቀሰመ፣ ያጠና፣ያልገባውን ጠይቆ የተረዳ ተማሪ የሥራውን ውጤት የሚያይበት ወቅት የዓመቱ መጨረሻ ነውና እናንተም በርትታችሁ ተማሩ፣አጥኑ! ትላንት አልፏል ዛሬ ግን መበርታት አለብን፤ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች አባቶች ምን ይላሉ መሰላችሁ ‹‹ከትላንት ብንዘገይም ከነገ እንቀድማለን..›› ትላንትና ጨዋታ አታሎን በደንብ ያላጠናን ልጆች በቀሪው የትምህርት ጊዜ በርትተን በማጥናት ነገን መቅደም እንችላለን፡፡ መልካም !
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው…›› እንዳለን (ዕብ.፲፫፥፫) የኑሯቸውን ፍሬ ተመልክተን በእምነት እንመስላቸው፣ በምግባር እንከተላቸው ዘንድ ምሳሌ ከሚሆኑን ከቅዱሳን አባቶቻችን አንዱ ሰለሆነው ስለቅዱስ ኤጲፋንዮስ ታሪክ በጥቂቱ ልንነግራችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ!
ቅዱሰ ኤጲፋንዮስ ሀገሩ ቆጶሮስ ሲሆን ገና ሕፃን እያለ አባቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየበት፤ ስለዚህም እናቱ እርሱንና እኅቱን ማሰደግ ነበረባቸው፤ ነገር ግን ምንም ስላልነበራቸው አባታቸው የነበረችውን አህያ እንዲሸጠውና ገንዘብ ይዞ እንዲመጣ እናቱ ወደ ገቢያ ላከችው፤ ኤጲፋንዮስም የእናቱን ትእዛዝ ተቀብሎ አህያዋን ለመሸጥ ወደ ገበያ ሄደ፡፡
በገበያም ስፍራ ክርስቲያን የሆነ ፊላታዎስ የሚባል ሰው አገኘው፤ አህያዋም ክፉና አስቸጋሪ ስለነበረች ኤጲፋንዮስን ረገጠችውና ወደቀ፤ አባ ፊላታዎስም በመስቀል ምልክት አማተበና ጸልዮ አዳነው (ፈወሰው)፡፡ ኤጲፋንዮስም አባ ፊላታዎስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ሲጠራ በሰማ ጊዜ ‹‹በስሙ ተአምራት የምታደርግበት አምላክህ ማነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ አባ ፊላታዎስም ስለ ጌታችን ታሪክ ነገረው፤ ክርስትናንም አስተማረው፡፡
ከዚያም አንድ ባለፀጋ (ሀብታም) ሰው ኤጲፋንዮስን ወስዶ ማሳደግ ጀመረ፤ ሀብቱንም ሁሉ አወረሰው፤ በአንድ ወቅትም በመንገድ ሲሄድ ሉኩያኖስ የተባለ መነኩሴ ጋር ተገናኝተው ሲሄዱ ችግረኛ ሰው ሲለምን አገኙ፤ አባ ሉክያስም የለበሰውን ልብስ አውልቆ ለችግረኛው ሲያለብሰው ለእርሱ ደግሞ የብርሃን ልብስ ከሰማይ ሲወርድለት ኤጲፋንዮስ ተመለከተ፡፡ ከመነኩሴው እግር ሥር ሰግዶም ‹‹አንተ ማነህ? ሃይማኖትህስ ምንድነው?›› በማለት ጠየቀው፤ አባ ሉኩያኖስም ክርስቲያን እንደሆነ ነገረው፤ አስተማረውም፤ ከጳጳሱም ዘንድ ወሰደው፤ ትምህርት አስተምሮ አጠመቀው፤ ባለጸጋ አሳዳጊው ያወረሰውን ንብረቱን ለችግረኞች መጽውቶ (ለግሶ) መነኰሰ፤ እኅቱንም በክርስትና ሃይማኖት እንድታምን አደረገ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ኤጲፋንዮስ በፊት ስለክርስትና ሃይማኖት ሰምቶ አያውቅም ነበር፤ ሆኖም ግን ተአምር ሲደረግ አይቶ አመነ፤ ተጠመቀም፤ መነኩሴም ሆነ፡፡ በዚህ የምንረዳው እግዚአብሔር ሰዎችን በተለያየ መንገድ እንደሚጠራ ነው፤ ታሪካቸውን ቀይሮ ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡ ኤጲፋንዮስ አባ ኢላርዮስ አስተማረው፤ ሥርዓተ ምንኩስናን አሳወቀው፤ የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ተማረ፤ ለቅድስና ሕይወትም በቃ፤ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ጀመር፤ ሰይጣንን ከሰዎች ማስወጣት፣ ድውያንን መፈወስ፣ ሙት ማንሣት፣ ከደረቅ ቦታ ውኃ ማፍለቅ፣ ዝናም ማዝነም ጀመረ፤ በገድል በቱሩፋት ፍጾም ሆነ፤ ብዙዎችን አስተምሮ ወደ ክርስትና ሃይማኖት መለሰ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሃይማኖት ስንጸና፣ በምግባር ስንጎለብት መንፈሳዊ ሕይወታችን ሲጠነክር፣ጾመኞ፣ ጸሎተኛ ስንሆን፣መታዘዝ፣ ትሕትና፣ ቅንነት፣ አስተዋይ ስንሆን፣ ሰዎችን ስንወድ እንዲሁም መልካም ነገር ስናደርግ የእግዚአብሔር ፀጋ ያድርብናል ለክብርም እንበቃለን፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መምህሩ ቅዱስ ኢላርዮስ ወደ ቆጵሮስ እንዲሄድና እንዲቀመጥ በዚያም ኤጲስ ቆጶስ እንደሚሾም ነገረው፤ ሄዶም በዚያ ተቀመጠ፤ ሊቀ ጳጳሱም ባረፈ ጊዜ እርሱ የቆጵሮስ ኢጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾመ፤ መልካም ሥራውንም አበዛ፤ ብዙ መጻሕፍትንም ደረሰ (ጻፈ)።
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ትምህርት ሃይማኖተ አበው በተባለው ታላቅ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቧል፤ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ካሉ ዐሥራ ዐራቱ ፍሬ ቅዳሲያት አንዱን እርሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ ‹‹የቆጵሮስ ደሴት ኤጲፋንዮስ የተናገረው የቁርባን ምሥጋና…››
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! አባታችን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ታሪኩ ያደረጋቸው ተአምራት፣ የጻፋቸው መጻሕፍት ብዙ ናቸው፤ እኛ ግን በጥቂቱ ብቻ ገለጽንላችሁ፤ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ግንቦት ዐሥራ ሰባት ቀንም በክብር ዐረፈ፡፡ ከቅዱሳን አባቶቻችን ሕይወት ብዙ እንማራለን! እናንተስ ከቅዱስ ኤጲፋንዮስ ምን ምን ተማራችሁ!!! ታዛዥነትን፣ ጉብዝናንን፣ አባቶችን ማከበርን፣ እግዚአብሔርን ድንቅ ጥሪ፣ ያወቁትን የተማሩትን ለሌላው ማካፈል፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፤… መልካም!
ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከቅዱስ ኤጲፋንዮስ ረድኤት በረከቱን ይክፈለን! ቸር ይግጠመን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!