ቅርሶችን በተመለከተ ዐውደ ጥናት ተካሔደ

ኅዳር 22/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች አያያዝ /አተገባበር/ ስምምነት በሀገር አቀፍ ደረጃ /Implementation of the Intangible cultural Heritage convention at national level/ በሚል ርዕስ ዐውደ ጥናት ተካሔደ፡፡ ዐውደ ጥናቱ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም /UNESCO/ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን፤ ከኅዳር 4-8/2004 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ለመካሔድ ችሏል፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ የዩኒስኮ ተወካይ በሆኑት በፕሮፌሰር አማርሰዋር ጋላ እና በቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ የየክልሉ የቅርስና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ተወካዮችና ባለሙያዎች የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከልና የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን፤ በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የማይዳሰሱ /Intangible/ ቅርሶችን ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸው እንዲጠብቃቸው፣ እንዲያስተዋውቃቸውና በዓለም ቅርስነት እንዲያስመዘግባቸው ከዓለም አቀፍ የቅርስና ጥበቃ ስምምነት ጋር በተጣጣመ መልኩ ለማራመድ እንዲቻል ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች በዐውደ ጥናቱ ላይ በሰፊው ተዳሰዋል፡፡

 

ዐውደ ጥናቱ ያተኮረባቸው መሠረታዊ ነጥቦችን ስንመለከት፣ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የማይዳሰሱ /intangible/ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበትን የቅዳሴ፣ የያሬድ ዜማዎች፣ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ እንዲሁም ሌሎች የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶቻችንን ለማየት ተሞክሯል፡፡ ለትውልድ ለማስተላለፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማን ምን ያድርግ? ለሚለው ጥያቄ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሙያዎችና የጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ማከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት በስፋት የተዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የማይዳሰሱ በተሰኙ ቅርሶች ዙሪያ ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት ለይቶ ማውጣትና መለካት፣ ማኅበረሰቡን ማሳተፍ፣ ቀጣይነት ያለው ጥበቃና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

የማይዳሰሱ /Intangible/ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶችን በተመለከተ የወጡ ፖሊሲዎችንና አዋጆችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ጥናትና ጥበቃ የሚደረግላቸውን ቅርሶች ለመንከባከብ እንዲቻል የተለያዩ ተደራሽ አካላትን መምረጥ፣ ማደራጀትና ማዋቀር፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት ድጋፎችን ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ማመቻቸት እንደማገባ ተገልጿል፡፡

ዐውደ ጥናቱ በባህልና ቱሪዝም የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ እንደመሆኑ በቡድን በቡድን በመሆን አሉ የተባሉ ጠቃሚና ጎጂ ተጽዕኖዎች በማይዳሰሱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ዙሪያ /positive and negative impacts to Implement Intangible cultural heritage/ በዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱም ከተለያዩ የቅርስና ጥበቃ ባለሙያዎች ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማዕከል የተለያዩ ተሞክሮዎችን ለታዳሚው ማካፈል የተቻለ ሲሆን በቀጣይነትም በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ በጎ ገጽታዎችን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያሏትን የማይዳሰሱ /Intangible/ ቅርሶች ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚረዳና መንገዶችንም ያመቻቸ ዐውደ ጥናት በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል፡፡ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተካሔደው ዐውደ ጥናት ኅዳር 8/2004 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡