ስማችን!
ዓይናለም ሽመልስ
ሐምሌ ፲፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ሕፃን ሆኖ አባቷ፣ አባት ሲሆን ልጇ
በእምነት ያበረታት ወርዶ ከእቅፍ እጇ
ወደ ሞት እንዳትሄድ ሥቃይን ተሰቅቃ
ለልጄ እንዳትል የመከራ እሳት ሞቃ
ቆሞ መሰከረ ድምጹን አሰምቶ
ከአላዊው ንጉሥ በመንፈስ ተሞልቶ
ብልጭልጭ አይደለም መጫወቻ ክበብ
የጌታዬ ፍቅር በየዕለት የሚያብብ
ሹመት ሽልማት አያሻኝም ዛሬ
ስማኝ የእውነት ጠላት . . .
የዲያብሎስ ጭፍራ ይኸው ነው ነገሬ
እባክህን ፍጠን ፍቅሩ እንደ እሳት እያቃጠለኝ ነው
ላከኝ ወደ አምላኬ እጅግ ናፍቄያለው
እኔ የማመልከው እኔ የምኖረው
ለፈጠረኝ አምላክ ለአንድ እርሱ ብቻ ነው
ደስ ተሰኝቼ የምመሰክርለት ለዓለሙ አስገኚ
ለፍጥረት ፈጣሪ አንተንም እኔንም በእኩሉ ዳኚ
ስምህ ማነው ላልከኝ ስሜ ክርስቲያን ነው
ከውኃ ከመንፈስ ዳግም የተወለድኩ . . .
አዎ ስሜ ክርስቲያን ነው
መጠሪያ ከፈለክ ምድራዊ ማንነት….
ቂርቆስ ብለህ ጥራኝ
ሦስት ዓመቴም ቢሆን ዛቻህ የማይገድበኝ
እናቴም እርሷ ናት አንጌቤናዊቷ ቅድስት ኢየሉጣ
ስሟ ክርስቲያን ነው ሺህ ፍርሀት ቢመጣ
በኩራት አንተ ፊት እንዲህ የምናገረው
ልቤ ውስጥ ጽኑ እምነት እውነት ስላለ ነው
እለ እስክንድሮስ እጅጉን ቢቆጣ ትእዛዝን ዐወጀ
ለ፵ ቀን ተሠርቶ በፈላ ጋን ብረት ጨምሯቸው አለ እሳት በእሳት ፈጀ
ድምጽ ተሰማ ከላይ ከአርያም
ክንፉን እያማታ ገብርኤል ወረደ በምሕረት ወዳለም
ታላቁ መልአክ ምሥራች ነጋሪ
የአምላክ ባለሟል ልደቱን አብሣሪ
ደርሶ ከመቅጽበት እንደ እምነታቸው
አንዳች ሳይነካ ከእሳት አወጣቸው
ቅዱስ ገብርኤል
በነደ እሳት ስሑል
በጌራ ብርሃን ክሉል
መልአከ መዊዕ ወኃይል
ገብርኤል ነዓ ለሣህል
ኦ ገብርኤል መልአከ ራማ
እሳቱ የሚበርድ ድምጽህ ሲሰማ
ኦ ገብርኤል መልአከ ፍሥሓ
እንዴት ደስ ያሰኛል….
በእሳቱ መካከል በደስታ መዘመር
ቂርቆስ እየሉጣ ታምነው በአምላክ ፍቅር
አትፍሪ እናቴ እያለ ያስገባት
ትንሹ ቂርቆስ ነው መድኃኒት የሆናት
ግን ዛሬ ስማችን ማነው?
እውን ክርስቲያን ነው?
የዘሬ ያንዘርዝረኝ
ሥልጣኔ ይቅደምልኝ
ትምህርቴ ይታወቅ
ማህተቤ ይደበቅ
ሆኖ ነገራችን
እስካልተመለስን
ወደ ቀደምታችን
መንፈስ ቅዱስ ታርቆን
ከልብ ከራሳችን
ቀስመን ከዋኖቹ ከአባቶቻችን
ደግሞም ከሕፃኑ ቂርቆስ ሰማዕቱ
በእምነቷ ከጸናች ከእየሉጣ እናቱ
ከቅዱስ ገብርኤል መልአክ ያዳናቸው
ከድርሳን ገድላቸው
አሁንስ . . .
ማነው ስምህ?…
ማነው ስምሽ?…
ስማችን ለጠፋን ጥያቄው ጠጥሮ
ሳንፈተን በሞት ከብዶን ያለም ኑሮ
አይደለም ከእቶን ከሰው አፍ ላንገባ
እጅጉን ስንፈራ ታፍረን በእውቀት ካባ
ምስክርነቱ ዓላማው ካልገባን
ፈጣሪ ላንድ አፍታ ሰማዕቱን አሳየን
ጽናት በረከቱ ቃል ኪዳኑ ይጎብኘን
እንድንማፀነው ቅንጣት እምነት ኖሮን
እናቱን እንዳለ አትፍሩ እያለን
ወደ ሕይወት መንገድ ያሳየን ፍኖቱን
እባክህ መልአኩ እምነታችን ይስፋ
አማልደን ከአምላክህ ፍርሃታችን ይጥፋ
ውኃውም ቢዘልል ቢፍለቀለቅ ጸንቶ
ከኃጢአት ማዕበል አትተወን ከቶ
ገብርኤል . . . ገብርኤል . . . ገብርኤል….
እያልን ስምህን ጠርተን
በትድግናህ ታምነን ድርሳንህን ደግመን
የእየሉጣ ዕድል የልጇን ተአምር
ሥራልን ሁልጊዜ ዕለት ዕለት ክበር
እኛም ስንጠየቅ ስማችንን በውል
በልበ ሙሉነት ክርስቲያን እንድንል
አክመን አበርታን አድነን ፈውሰህ
ከጥርጥር ዓለም በክንፎችህ ጋርደህ
የክርስትናን ግብር የማይጠፋውን ስም
እባክህ አድለን በልባችን አትም!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!