ስያሜ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

የማኅበሩ ርእይ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊ አቅም ተጠናክሮ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌል በመላው ዓለም ተስፋፍቶ በሃይማኖት ጽኑዓን የሆኑ ምእመናን በመላው ዓለም በዝተው ማየት፡፡

ተልእኮ

ማኅበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን የተለያዩ ትምህርተ ሃይማኖት ማስፋፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ግቢ ጉባኤያትና ምእመናን የወንጌልን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ትውፊት፣ እንዲያቆዩና እንዲጠበቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲጠናከር አቅሙ እንዲያድግ ማድረግና በየዘመኑ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመቃኘት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር፡፡

አስፈላጊነት

የቤተ ክርስቲያቱ መዋቅር ያልሸፈነችውን ክፍተቶች በመሙላት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማ የሚገቡትን የዘመኑን ትውልድ ከመንፈሳዊነትና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር በማዋሐድና ከአበው በማቀራረብ ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅበትን ድርሻ እንድንወጣ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡

ዓላማ

ማኅበሩ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዐበይት ዓላማች አሉት፡፡

  • በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን በማኅበሩ ሥር አደራጅቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት እንዲማሩ እና የአባቶች ተተኪ እንዲሆኑ ማድረግ፣

  • የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሳይለውጥ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለዘመኑ ትውልድ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲዳረስ ማድረግ፣

  • ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴት እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ ማድረግ፣

  • የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘብ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት፣

  • ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ወጣት ምሁራንን ማበረታታና በሚቻለው ሁሉ መርዳት፡፡

አቋም

በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡

አመሠራረት

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠረራት ጥቂት ነጥቦችን እናስታውስ፡፡ በ1980ዎቹ የጋንቤላና የመተከል የሠፈራ ዘመቻ ጥቂቶቹን አገናኘ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ሌሎችን በጥበቡ እየጠራ በክረምት ጊዜ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ሲዘጉ በዝዋይ ገዳም እንዲገናኙ አደረገ፡፡ በመጨረሻም አብዛኛዎቹን ወጣቶች በ1983 ዓ.ም በብላቴ ካምፕ አገናኛቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ሆኑላቸውና የተለያዩ ማኅበራትን እያቋቋሙ ወጣቱ ትውልድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የማስተዋወቁን ሥራ አፋፍመው ቀጠሉበት፡፡ በዚህ የተሰበሰበው ኃይል አሁንም ተደራጅቶ ጠንካራ አገልግሎት የሚሰጥበትን አንድ ማኅበር እየፈለገ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት የተለያዩ ማኅበራትን በመመሥረት የየአቅማቸውን አገልግሎቶች ሲፈጽሙ የቆዩት ወጣቶች በአንድ ማኅበር ቢሰባሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገነዘበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በመላእክት ስም፣ በእመቤታችን ስም፣ በቅዱሳን ስም የተሰበሰቡት ሁሉ ለመታሰቢያነት የሚጠሯቸውን ቅዱሳን የማያስቀርና ተልእኮአቸውን የማይለውጥ አንድ ማኅበር ለመመሥረት የወሰኑት፤ ወስነውም አልቀሩ መሠረቱት፤ ማኅበረ ቅዱሳንን፡፡

ውኃ ልትቀዳ ወርዳ ጌታችንን አግኝታ እንደተመለሰችው ሰማርያይቱ ሴት፤ ከሄዱበት ምድራዊ ዓላማ ተጨማሪ ሰማያዊ ዓላማን አንግበው መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥ ማኅበር ለመመሥረት ምክንያት የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንደሙያ ዝግጅታቸውና ስጦታቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል አደራ ተቀበሉ፡፡ /ዮሐ. 4፤7/ ስለዚህም ማኅበሩ ሐዋርያዊ ተልእኮን ለማስፋፋትና ግቦቿን አሳክታ ከችግሮቿ ወጥታ ለሕዝቦቿ ማኅበራዊ ሕይወት ለውጥ የመሪነት ሚና የምትጫወት ቤተ ክርስቲያንን ለማየት የሚያስችል የአገልግሎት ስልት ነድፎ ብቅ አለ፡፡