‹‹ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ›› (መሓ.፩)

ክፍል አራት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ጥቅምት ፳፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ከዚህ በፊት የእመቤታችንን የስደቷን ነገር አንሥተን ‹‹ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ፥ ተመለሽ›› በሚል ርእስ ከክፍል አንድ እስከ ሦስት አድርሰናችሁ ነበር፡፡ ጥሩ ትምህርት እንዳገኛችሁበት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የዛሬው ትኩረታችን ያን ሁሉ መከራ የተቀበለችበት የስደቷን ምክንያትና ዓላማ መዳሰስ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ስለ ግብጻዊው ወንበዴ ማለትም በጌታ ቀኝና በግራ ስለተሰቀለው ፈያታዊ ዘየማን ትንሽ ታሪክ እንጨምርና ወደ ዋናው ሐሳባችን እንገባለን፡፡

ጥጦስና ዳክርስ የተባሉት ሁለት ወንበዴዎች እመቤታችንን በመንገድ አግኝተው እንደዘረፏት፣ በኋላ ጥጦስ አዝኖላት ንብረታቸውን እንደመለሰና ጌታን አቅፎ እንደሸኘ በክፍል ሦስት ቀንጨብ አድርገን አቅረበንላችሁ ነበር፡፡ ይህ ፈያታዊ ዘየማን ጥጦስ ጌታን አቅፎት ሲሸኛቸው ሳለ ሰይፉ ከእጁ ወድቃ ተሰበረችበትና በጣም አዘነ፡፡ ጌታም ‹‹ኦ ጥጦስ አስተጋብእ ስባራተ ሰይፍከ፤ ጥጦስ ሆይ፥ የሰይፍህን ስባሪ ወደ ሰገባው ክተተው›› አለው፡፡ ሰብስቦ ቢያቀርብለት እንደ ነበረ አድርጎ ሰጠው፡፡ ጥጦስም ደስ ብሎት ‹‹ዝንቱ ሕፃን እምደቂቀ ነቢያት፤ ይህ ሕፃን ከነቢያት ልጆች አንዱ ነው›› አለ፤ ዳክርስ ግን ‹‹እውነትም ከነቢያት ወገን ቢሆን አይደል አንተን ቀማኛውን ገነት ትገባለህ ማለቱ!›› ብሎ ዘበተበት፡፡

የዳክርስ ክፋቱ እስከ መስቀልም አብሮት ዘልቆ በግራው በተሰቀለ ጊዜ ፀሐይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ደም ስትለብስ፣ ከዋክብት ሲረግፉ፣ መቃብራት ሲከፈቱ፣ ሙታን ሲነሡ፣ ተአምራቱን አይቶ እንኳን አላመነም፡፡ ይልቁንም ‹‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን ራስህንም አድን፤ እኛንም አድን›› እያለ ይሰድበው ነበር፡፡ (ሉቃ.፳፫፥፴፱) የጥጦስ ግን ወሮታው እንዳይቀርበት ጌታን የታቀፈበትን ልብሱን ቢያጥበው ከወዙ ፫፻ ወቄት የሚያወጣ ሽቱ አግኝቷል፡፡ ጌታን ማርያም እንተ ዕፍረት በ፫፻ ወቄት ገዝታ የቀባችውና ይሁዳ ‹‹ይህስ ተሸጦ ለድሆች ይሆን ነበር›› ብሎ ያንገራጎረበት ሽቱ ይህ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፪፥፫ እና ማቴ.፳፮፥፮)

ምክንያተ ስደት፡- በቤተ ልሔም ሲወለድ አጋንንትን በእሳት ፍላጻ የነደፋቸውን፣ አሳዳጆቹን እንደ ፈርዖንና ሠራዊቱ የውኃ ሽታ ሊያድረጋቸው የሚቻለውን፥ ሁሉ በእጁ የሆነ ልጇን ይዛ ስለምን እመቤታችን በረሃ ለበረሃ ተንከራተተች? ግብጽስ ለምን ለስደቷ ተመረጠች?

‹‹እንዘ ኪሩቤል አፍራሲሁ ወሱራፌል ላእካኒሁ ወክነፈ ነፋስ ሠረገላሁ፤ ኪሩቤል ፈረሶቹ ሱራፌልም መልእክተኞቹ የነፋሳት ክንፎቹም ሰረገላዎቹ››  የተባለለት ጌታስ ስለምን  ከናዝሬት እስከ ቁስቋም ተራራ በእግሮቹ ሄደ? (መጽሐፈ ሰዓታት)

ሀ. አንዱና ዋናው ስለምን ተሰደደ ቢሉ የቤዛነት ሥራውን የሚፈጽመው ገና በቀራንዮ ነውና ጊዜው ሳይደርስ እንዳይሞት ወደ ግብጽ ነው፡፡

ለ. ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡

ትንቢቱ፡- በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ሊፈጸም ነው፡፡ (ኢሳ.፲፱፥፩) ‹‹እምግብጽ ጸዋእክዎ ለወልድየ፤ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት›› የሚልም አለና ‹‹ትንቢት ይቀድሞ ለነገር›› እንዲሉ አስቀድሞ ይህ ትንቢት ተነግሮ ስለነበር፣ ትንቢትን የሚያናግር ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ አናጋሪነት የተነገረ ትንቢት ሳይፈጸም አይቀርም፤ ጌታ ደመና ቀሊል በተባለች ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ምድረ ግብጽ ወረደ፡፡ ደመና ያላት እመቤታችንን ነው፡፡ ዝናመ ሕይወት ክርስቶስን ያዘለች እውነተኛ ደመና እርሷ ናትና፡፡ ‹‹አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ ለነ ማየ ዝናም፤ የዝናም ውኃ የታየብሽ እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም፡፡

ምሳሌው፡– ዮሴፍን ወንድሞቹ ‹‹ሊሾምብን ሊገዛን ነው›› ብለው በክፋት ተነሥተውበት ሸጠውት ወደ ግብጽ ወርዶ ነበር፡፡ (ዘፍ.፴፯፥፩-፳፰) ጌታም ‹‹ሊሾምብን ሊነግሥብን ነው›› የሚሉ አጋንንትና ሄሮድስ በክፋት ተነሥተው አሳድደውት ወደ ግብጽ ወርዷልና ነው፡፡

ሐ. ክህደት በግብጽ ጸንቶ ነበርና ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡

ክህደት ወደ ጸናበት መሄድ ልማድ ነውና፡፡ በግብጽ አምልኮ ጣዖት የተስፋፋበት ነበር፡፡ ክህደትም በሰው ልቡና የጸናበት እንደነበረ አጋንንንትም በሰው ልቡና ሠልጥነው እንደነበር እና ቁራሽ ኀብስት፣ ጽዋዕ መጠጥ ከልክለዋት እመቤታችን እንዴት እንዳዘነች ቀድመን አይተናል፡፡

መለኮት ዕጓላ ሶበ ጸምዐ ከመ ደቂቅ——-ዘይሰፍሮ በኅፍኑ ለማየ ባሕር ዕሙቅ

በከየት ወትቤ ማርያም ማዕነቅ————አልቦ እምሰብአ ሀገር ዘየአምራ ለጽድቅ

ሶበ ሰአልክዎሙ ማየ ኢወሀቡኒ በሕቅ———ወአህጎልኩ ለወልድየ አሳዕኖ ዘወርቅ፡፡

‹‹ጥልቅ የሆነ ባሕርን በእጁ የሚሰፍረውንና የማይመረመር መለኮት የተባለ የባሕርይ አምላክ ልጇ በተጠማ ጊዜ ከዚህች ሀገር ሰዎች ቸርነትን የሚያውቃት የለም፤ ውኃን በእጅጉ ለመንኋቸው፤ አልሰጡኝም፤ የልጄን የወርቅ ጫማውን አስጠፋሁ እያለች ዋኖስ ማርያም አለቀሰች፤›› (ሰቆቃወ ድንግል) በዚህም ወደ ግብጽ በመሰደዳቸው ጣዖታትን አፈራርሷል፤ አጋንንትን ከግብጽ ከሰው ልቡና አሰድዷል፡፡ ‹‹…በዚያች ሀገር ያሉ ጣዖታትም ወድቀው ተሰባበሩ፤ አማልክቱን የሚያመልኩትም ሁሉ ፈሩ፡፡ ወደ ቤታቸውም ገብተው ተደበቁ፤ ….ብዙ ሰዎችም አመኑ፤ የሀገር ሽማግሌዎቹም ጣዖት የሚያመልኩትን ለምን ተሰወራችሁ? አማልክቶቻችሁንስ ለምን ተዋችሁ? አሏቸው፡፡ ይህች ሴት ከልጇ ጋር በገባች ጊዜ ጣዖታቱ ተሰበሩ፤ የአማልክቶቻችን ቤቶችም ወደቁ፤ ሌሊት ሠርተናቸው ሲነጋ ተሰባብረው እናገኛቸዋለን አሉ›› ትላለች እመቤታችን፡፡ (ድርሳነ ማርያም ገጽ ፪፻፰)

. ገዳማተ ግብጽን ለመባረክ ወደ ግብጽ ተሰደድዋል፡፡

በግብጽ ታላላቅና ደጋግ ገዳማት እነ ገዳመ ሲሐት፣ እነ ገዳመ አስቄጥስ አሉና ገዳማትን ለመባረክ ወደ ግብጽ ተሰድደዋል፡፡

ሠ. መልኩን አይተው የሚያምኑ አሉና ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡

‹‹ወተበሀላ አዋልደ ሲሐት፤ ንዑ ንርአዮ ለወልደ መንክራት፤ የሲሐት ልጅ ተባለ፤ የወልድን ተአምር ኑ እዮ›› እንዲል፤ (ትርጓሜ ማቴ.፪፥፲፭)

ረ. ሃይማኖት ከሁሉ ቢጠፋ ከግብጽ አይጠፋም ሲል ወደ ግብጽ ተሰደዋል፡፡

እስከ ዕለተ ምጽአት ወልድ ዋሕድ ስትል ትኖራለችና፡፡

ሰ. የበደለ አዳም ከገነት ተሰዶ ነበርና ያልበደለ ክርስቶስ ስለ አዳም ካሣ ሊሆን ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡

ሸ. ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ ተሰደደ/ተሰደደች፡፡ እመቤታችን ‹‹ሰማዕት ዘእንበለ ደም ናት፤ ሰማዕት ያለ ደም መፍሰስ›› ሰማዕትነት በእሳቱ መበላት፣ በስለቱ መወጋት ብቻ አይደለም፡፡ ስደቱ፣ ረኃቡ፣ ጥሙ፣ እርዛቱ፣ እንግልቱ ሁሉ ሰማዕትነት ነውና ለሰማዕታት ስደትን ልትባርክላቸው/ሊባርክላቸው ተሰደደች/ተሰደደ፡፡ ‹‹ወሶበ ይሰድዱክሙ እምዛቲ ሀገር ጒዩ ኀበ ካልእታ፤ …በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ ..›› እንዳለ ጌታ በወንጌል፡፡ (ማቴ.፲፥፳፫) በዚህም ብዙ ሰማዕታት ክብር አግኝተዋል፤ እመቤታችንና አብረዋት የነበሩት ዮሴፍና ሰሎሜ ሰማዕት ዘእንበለ ደም መሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ሰማዕት በደም የሆነው ጊጋር መስፍነ ሶርያንም እናገኛለን፡፡

መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ‹‹እናቱንና ሕፃኑን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና››  ባለው ጊዜ በስደታቸው መጀመሪያ መሽቶባቸው ያደሩት ከጊጋር መስፍነ ሶርያ እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ (ማቴ.፪፥፲፫) ገሥግሰው የደረሱ የሄሮድስ ሠራዊት ግን ጊጋርን በሰይፍ ቀልተው ገድለውታልና፡፡ የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሰማዕት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በኢትዮጵያ የቅኔ ጉባኤ ቤቶች በትልቁ ከሚተረኩ ታሪኮችና ብዙ የቅኔ ተማሪዎች ቅኔ ከሚቆጥሩበት አንዱ ጊጋር ሰማዕት ነው፡፡

የተወዳጆችሁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! መቼም የስደቷን ታሪክ ተርከን አንዘልቀውምና ከዚህ በላይ ልንጓዝበት አንችልም፡፡ ይሁን እንጂ የእመቤታችንን ስደትና የኢትዮጵያን ግንኙነት ሳይዳስሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ ቸር ብንሰነብት፣ የእመቤታችን ከስደት መመለስ ከኢትዮጵያ ጋር አገናኝተን ክፍል አምስትና የመጨረሻውን ክፍል ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡

ይቆየን!