ሰዋስወ ግእዝ
ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በቅድሚያ በሕያውና ዘለዓለማዊ በሆነ በእግዚአብሔር ስም የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ ስለ ግእዝ ቋንቋ አጠር ባለ መልኩ እገልጻለሁ፡፡
የግእዝ ቋንቋ ቀዳማዊነት
ቋንቋ ማለት መግባቢያ መተዋወቂያ መነጋገሪያ አሳብ ለአሳብ መገላለጫ ወዘተ…… ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ባለበት ቦታ ሁሉ ቋንቋ አለ፤ ቋንቋም ባለበት ቦታ ሕዝብ አለ፤ ያለ ሕዝብ ቋንቋ ያለ ቋንቋ ሕዝብ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ስለ ግእዝ ቋንቋ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ስንነጋገር፡-
ከአንዳንድ ቀደምት የታሪክ ጸሐፊዎችና የግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፈው ካስረከቡን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የቋንቋው ባለቤቶች እንደምንረዳው፡- የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ በኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ከስምንተኛው ምዕተ ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ ጀምሮ ነገደ ሴም /የሴም ዘሮች/ወገኖች/ ቋንቋቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሴማዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ቋንቋ ሆነ፡፡ ነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋቸውን በመግባቢያነት አሳድገው፣ ሥነ ጽሑፋቸውን አስፋፍተው፣ በባቢሎን በአካድና፣ በአሶር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለሁለት ተከፍለው ግማሾቹ ሴማውያን ሰሜንና ምስራቅ እስያን፣ ግማሾቹ ሴማውያን ደግሞ ደቡቡ እስያን ይዘው ይኖሩ ነበር፡፡
የሰሜን እስያ ሴማውያን ቋንቋ /የአካድ ቋንቋ/ አማራይክ፣ ዕብራይስጥንና ፊንቄን ሲያስገኝ የደቡብ እስያ ሴማውያን ቋንቋም /አካድ ቋንቋ/ ሳባን ግእዝንና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቢያነት የምንጠቀምባቸውን ሴማውያን ቋንቋዎች አስግኝቷል፡፡ በደቡብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ነገደ ሴም በተለያየ ምክንያት እየፈለሱ ወደ ደቡብ ዐረብ፣ ወደ የመንና ወደ አካባቢዋ መጥተዋል ከዝያም ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአክሱምና በአካባቢዋ ሰፍረው ይዘዋቸው ከመጡት ቋንቋዎቻቸው መካከል በታሪክ ጎልተው የሚታወቁና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓትም በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ቋንቋዎች የሳባ እና የግእዝ ቋንቋዎች ናቸው፡፡
ነገደ ሴም /ሴማውያን/ ቋንቋዎቻቸውን /ሳባና ግእዝን/ ከነገደ ካም ቋንቋ ጋር አስማምተው በመያዝ ሁሉንም ቋንቋዎች ሲናገሩዋቸው ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳባና ግእዝ እየተለመዱና እየተስፋፉ እየዳበሩም ከመሄዳቸው የተነሣ የነገደ ካምን ቋንቋ እየዋጡት መጥተው ሁለቱ ሳባ እና ግእዝ ቋንቋዎች ብቻ ሀገራዊ ቋንቋዎች ይሆኑ ጀመር እየቆዩ ግን ሁለቱ /ሳባና ግእዝ/ በጣም ተመሳሳይና ተቀራራቢ በመሆናቸው እንደ አንድ ቋንቋ ሆነው ይነገሩ ጀመር፡፡ ይኸም ጽሑፉ /ፊደሉ/ በሳባ እንዲጻፍ እና መነጋገሪያ ቋንቋውን ደግሞ በግእዝ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ነገደ ሴም በሳባ ቋንቋቸው ሳባውያን፣ በግእዝ ቋንቋቸው ደግሞ አግአዝያን ተብለው የሚጠሩት ከዚህ መነሻነት ነበር፡፡
ለዚህም መረጃ የሚሆኑን ሳባና ግእዝ ቋንቋዎች ተጽፈውባቸው የሚገኙት ጥንታውያን የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደ የአክሱምና የላሊበላ ሐውልቶች በየሐ እና በአዱልስ ወዘተ….. የተለያዩ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ቅርጻ ቅርጾች እስከ አሁን ቆመው የሚገኙ የዚህ ቋሚና ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሳባና የግእዝ ቋንቋዎች በዚህ ሁኔታ እስከ 324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. አካባቢ ድረስ አብረው ሲነገሩ ቆይተዋል በኋላ ግን የሳባ ንቋ እየተዳከመና በግእዝ ቋንቋ እየተዋጠ ይሄድ ጀመር እንደ ምንም እየተንገዳገደ እስከ 350 /፫፻፶/ ዓ.ም. ቆይቶ ከዚህ በኋላ ከሥነ – ጽሑፍ ከመነጋገሪያነትም ፈጽሞ ቀረ የግእዝ ቋንቋ ግን ከ324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. ጀምሮ ብቸኛ ሀገራዊ ቋንቋ በመሆን እስከ ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም የአማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደ ነበር የታሪክ ጸሐፊዎች በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡
፩.፪. የግእዝ ፊደላት አመጣጥ
ስለ ግእዝ ቋንቋ ስንነጋገር በመጀመሪያ ለማንኛውም ቋንቋ መሠረት ስለሚሆነው ስለ ፊደል አመጣጥ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ስለ ፊደል አመጣጥ ሊቃውንት ብዙ ትንታኔ ይሰጡበታል ይኸውም ፊደል ማለት ጽሑፍ ነው ምክንያቱም “ፈደለ” ጻፈ ከሚለው ከግእዝ ቃል የወጣ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ “ፈደለ” የሚለውም ቃል የሦስት ፊደላት ጥምረት በመሆኑ እነዚህ ፊደላት ከየት እንደመጡ መነሻቸውን /ምንጫቸውን/ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ለዚህ በቂ የሆነ መረጃ እናገኛለን፡፡ የፊደል ስልት አንድም ቅርጽ የተጀመረው የአዳም ሦስተኛ ትውልድ በሆነው በነቢዩ በሄኖስ ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔርን በማገልገል የታወቀ ደግ ስለ ነበር ለደግነቱ መታወቂያ /መታሰቢያ/ ይሆነው ዘንድ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሕግ ማሰሪያ የሚሆነውን ፊደል በጸፍጸፈ ሰማይ /በሰማይ ገበታነት/ ተገልጦ ታይቶታል፡፡
ስለዚህ የፊደል ቅርጽ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሥነ-ጽሑፍ በር መክፈቻ በማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ መጠሪያ ስሙንም ጽሑፍ ለማለት ፊደል ብለውታል፡፡ ይኸስ እውነትነቱ ምን ያህል ያገለግላል ቢሉ በዚያን ጊዜም በጸፍጸፍ ሰማይ ታየ የሚባለው ፊደል የእብራይስጥ ፊደል እኛ አሁን አሌፉት እያልን የምንጠራው ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ፊደል ከፊደልነት ጥቅሙ ጋር እንደ ኅቡዕ ስም ይገመታል /ይታመናል/ ምክንያቱም የእያንዳንዱ ፊደል ትርጒም ከእግዚአብሔር ህልውና እና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካደረጋቸው የቸርነት ሥራዎች ጋር የተዛመደ ትርጒም ስለሚሰጥ (ስለአለው) ነው፡፡ ይህ እውነታ እና የስም አጠራር ትርጒም ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት አባቶች የፊደላት ትርጒም አሰጣጥ ላይ በግልጽ ተጽፎ የሚገኝ ነው /ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ/ በተጻፈው መጽሐፍ በግልጽ እንረዳዋለን ይህን መነሻ በማድረግ የሥነ-ጽሑፋችን በር መክፈቻ የአሌፋቶችን ስም ፊደል የሚል ስያሜ በመስጠት እንጠቀምበታለን፡- ስለዚህ ማንኛውንም ነገር ለመጻፍ ለመጪውም ትውልድ ለማስተላለፍ በጽሑፍ መቀረጽ ስላለበትና ራሱ ፊደሉ የሥነ-ጽሑፍ መጀመሪያ ስለሆነ ጽሑፍ ለማለት ፊደል ተብሎ ተጠርቷል፡፡
ለዚህም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት አጽንዖት ሰጥተው ሲያስቀምጡት “ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል” ይላሉ ይህ ማለት ወንጌል ሳይቀር የሚጻፈው /የሚተረጎመው/ በፊደል አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ስለ ፈደል ጠቃሚነት የሚሰጡትን ሐተታዎች ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት፡-
፩. ፊደል- ብሒል ነቅዓ ጥበብ ውእቱ፡፡
ፊደል የአእምሮ መገመቻ የምሥጢር መመልከቻ ነው ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም አይታወቅምና ፡፡
፪. ፊደል – ብሂል ነቅዓ ጥበብ ውእቱ፡፡
ፊደል የጥበብ ሁሉ መገኛ ምንጭ ነው፡፡
፫. ፊደል – ብሂል መራሔ ዕውር ውእቱ፡፡
ፊደል የእውር መሪ ነው፤ ምክንያቱም ሰውን ሁሉ ከድንቂርና አውጥቶ ወደ ብርሃን ይመራልና፡፡
፬. ፊደል – ብሂል ጸያሔ ፍኖት ውእቱ፡፡
ፊደል ማለት መንገድ ጠራጊ ነው፤ ምክንያቱም አላዋቂነትን /ድንቁርናን/ ከሰው ልጅ ጠርጎ /አጽድቶ/ ከፍጹም ዕውቀት ያደርሳልና፡፡
፭. ፊደል ብሂል -ርእሰ መጻሕፍት ውእቱ፡፡
ፊደል ማለት የመጻሕፍት ሁሉ ራስ /አናት/ ነው ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም ነገር መጻፍ አይቻልምና፤ /ኢተወልደ መጽሐፍ ዘእንበሌሁ ለፊደል/ ያለ ፊደል ምንም ነገር ሊጻፍ አይቻልምና
የግእዝ ቋንቋ ከሴማውያን ፊደሎች መካከል አንዱና ዋናው ጥንታዊ ቋንቋ ስለሆነ፣ የራሱ የሆነ ብዙ ቃላትን ከነፍቺዎቻቸው ይዞ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር ፊደል የማንኛውም ጽሑፍ መነሻ ስለሆነ፣ ጽሑፍ ብሎ ለመጥራት መጠሪያውን ፊደል ብለውታል፡፡ በአጠቃላይ ቋንቋ እንደ ማንኛውም ቋንቋ የራሱ የሆነ የአጻጻፍን ሥልትና ቅርጽ የተከተለ ጥንታዊና መሠረታዊ ቋንቋ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን