ሰኔ ሚካኤል – ካለፈው የቀጠለ
ከመጽሐፈ ስንክሳር
ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት፡፡ በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንደህ ብሎ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን፣ ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን፣ ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም እገሌ ሆይ! በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት፡፡›› ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ‹‹ወደ ባለ ጠጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፡፡ በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፡፡ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ›› አለው፡፡ ባሕራንም ‹‹እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ዅሉ አደርጋለሁ›› አለ፡፡
ባሕራንም ወደ ባለ ጠጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፡፡ በአነበባት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ፡፡ አስተውሎም እርግጠኛ እንደ ኾነ ዐወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለ ጠጋውን ልጅ አጋቡት፡፡ ዐርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ባለ ጠጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ኾኖ በደስታ የኾነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ‹‹ይህ የምሰማው ምንድነው›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹‹ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ እነሆ ለዐርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ዅሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝኽ ሰጥተውታል›› አሉት፡፡ ይህንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ፡፡
ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ኾነ፡፡ የተገለጠለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል እንደ ኾነ፤ ሊገድለው የሚሻውን የባለ ጠጋውን ጥሪቱን ዅሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ኾነ ተረዳ፡፡ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው፡፡ ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ኾኖ ኖረ፡፡ በዚህ በከበረ የመልአክት አለቃ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ፣ ከልጆቹም ጋራ የዘለዓለም ሕይወትን ወረሰ፡፡
መድኃኒታችን በተነሣባትም ቀን ይህ ክቡር መልአክ ሚካኤል ከውስጠኛው መጋረጃ ውስጥ ገብቶ በክብር ባለቤት ፊት እንዲህ እያለ ይለምናል፤ ‹‹እውነት ስለ ኾነ ቃል ኪዳንህ በምድር መታሰቢያዬን የሚያደርጉትን ትምርልኝ ዘንድ፤ ፈጣሪዬ ሆይ! እኔ አገልጋይህና መልእክተኛህ ከቸርነትህ እለምናለሁ፡፡ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና፡፡›› የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፤ ‹‹የመንፈሳውያን ሰማያውያን መላእክት አለቃቸው ሚካኤል ሆይ! መታሰቢያህን የሚያደርገውን ዅሉ መሸከም እንደምትችል ከሲኦል ሦስት ጊዜ በክንፎችህ ተሸክመህ እንድታወጣ እነሆ እኔ አዝዤሃለሁ፡፡›› ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት የበዓሉን መታሰቢያ ከሚያደርጉት በክንፎቹ ተሸክሞ የእሳቱን ባሕር አሳለፋቸው፡፡ እነርሱንም ከብቻው ጌታ በቀር የሚቈጥራቸው የለም፡፡
ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል፡፡ እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ዅሉም ይጠብቀን ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይ ዘንድ፤ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፤ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፤ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም፣ በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፤ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፤ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፤ የክርስቶስ ወገኖች የኾኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ፤ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡
ዳግመኛም በዚህች ቀን እግዚአብሔርን የሚፈራ አስተራኒቆስ የሚስቱ የቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ መታሰቢያ ኾነ፡፡ ይህም ሰው በየወሩ ሦስት በዓላቶችን እያከበረ ኖረ፡፡ እሊህም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በየወሩ በሃያ ዘጠኝ፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል መታሰቢያ በየወሩ በሃያ አንድ፤ የከበረ የመላእክት አለቃ የኾነ የቅዱስ ሚካኤል በዓል መታሰቢያም በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ናቸው፡፡ የሚሞትበትም ጊዜው ሲቀርብ እርሱ ሲሠራው የነበረውን ምጽዋት ይልቁንም እሊህን ሦስቱን በዓላት እንዳታስታጉል ሚስቱን ቅድስት አፎምያን አዘዛት፡፡
እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባሏን ለመነችው፡፡ እርሱም አሠርቶ ሰጣትና በቤቷ ውስጥ በክብር አኖረችው፡፡ ባሏም ከዐረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረ፡፡ ሰይጣን ግን ቀናባት፡፡ በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋር ተነጋገረ፡፡ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ አዝንልሻለሁ፤ እራራልሻለሁም፡፡ ገንዘብሽ ሳያልቅ፣ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅ ትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ፡፡ ባልሽም መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል፡፡ ምጽዋትም አይሻም፡፡›› አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ ‹‹እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገናኝ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ፡፡ ርግቦችና መንጢጦች እንኳ ሌላ ባል አያውቁም፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህ ሊኾን እንዴት ይገባል?››
ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርአያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት፡፡ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ፡፡›› እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን የከበረ የመልአኩ የሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት ስታዘጋጅ ሳለች ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ ‹‹አፎምያ ሆይ! ሰላም ላንቺ ይኹን! እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፡፡ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምእመን ሚስት ትኾኚ ዘንድ አዞሻል፡፡›› ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ፤ እንደ አብርሃምና ያዕቆብ እንደ ዳዊትም እንደነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገባ፤ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ያመጣላት ጀመረ፡፡
ቅድስት አፎምያም መልሳ ‹‹አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከኾንኽ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋር ወዴት አለ? የንጉሥ ጭፍራ የኾነ ዅሉ የንጉሡን ማኅተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድምና›› አለችው፡፡ ሰይጣኑም ይህንን በሰማ ጊዜ መልኩ ተለወጠና አነቃት፡፡ እርሷም ወደ ከበረው መልአክ ወደ ሚካኤል ጮኸች፡፡ ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት፡፡ ያንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ፡፡ ሰይጣኑም ጮኸ፡፡ ‹‹ማረኝ፤ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ፤ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና›› እያለ ለመነው፡፡ ከዚያም ተወውና አባረረው፡፡
የከበረ መልአክ ሚካኤልም እንዲህ አላት፤ ‹‹ብፅዕት አፎምያ ሆይ! ሒደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ፡፡ አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለዪአለሸና፡፡ እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል፡፡›› ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት፡፡ ወደ ሰማያትም ዐረገ፡፡ የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋለ ወደ ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ ዅሉ ላከች፡፡ ወደ እርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ዅሉ አስረከበቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች፡፡ የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንሥታ ታቅፋ ሳመችው፡፡ ያን ጊዜም በሰላም ዐረፈች፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፡፡ የዚህም የከበረ መልአክ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ዅላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡– መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፪ ቀን፡፡