ሰባቱ ኪዳናት፡- ኪዳነ ምሕረት
ክፍል አራት
የካቲት ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
በድንቅ ጥበቡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ያደነው እጅጉን መሐሪ ስለሆነ ነው፡፡ የቀደሙት የብሉይ ኪዳን ኪዳናት ሕዝቡን ከሲኦል መታደግ አልቻሉም ነበር፡፡ ፍጹም የሆነው ኪዳን የተደረገው በሰባተኛው ኪዳን ይህም ለሰው ዘር ምሕረትን ባስገኝች በንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡
የምሕረት ቃል ኪዳን የተሰጠችውን እናታችንንም ‹‹ኪዳነ ምሕረት›› እያልን የምንማጸናት ለዚህ ነው፡፡ ለአዳም የተገባለት የምሕረት ቃል በእርሷ ተፈጽሟልና፡፡ እመቤታችን አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልዳዋለችና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን ተቀብሎ እንዲሁም በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነው ከእርሷ በነሣው ሥጋና ነፍስ ነውና፡፡
በነገረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ልጇ መቃብር ቦታ ጎልጎታ እየሄደች ትጸልይ ስለ ነበር በየካቲት ፲፮ ቀን በጸለየችው ጸሎት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ ጸሎቷም እንዲህ የሚል ነበር፤ ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ፥ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡››
ጌታችንም ምን ሊያደርግላት እንደምትሻ ሲጠይቃት በስሟ ለሚማጸኑ፣ መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ፣ ለችግረኛ ለሚራሩ፣ በስሟ ቤተ ክርስቲያን ለሚያንጹ፣ ዕጣን፣ ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን ለሚሰጡ ምሕረትን እንዲያደርግላቸው ጨምራ ጠየቀችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በየካቲት ፲፮ ዕለት የገባላትን ቃል ኪዳን እንዲህ በማለት በመሐላ አጽንቶታል፡፡ ‹‹መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው፤ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ፡፡››
የምሕረት ቃል ኪዳን የተሰጠበት ይህ ዕለት ታላቅ ነውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቅት ታከብረዋለች፡፡ ቀድሞ ለነበሩ ኪዳናት ማለትም ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ኖህ፣ ኪዳነ መልከ ጸዴቅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ሙሴና ኪዳነ ዳዊት መደምደሚያ ነውና፡፡ ዘለዓለማዊ ስለ ሆነው የማያልፍ የምሕረት ቃል ኪዳን እየታሰበም በመዝሙር፣ በማኅሌትና በቅዳሴ ይከበራል፡፡
በክርስቶስ ክርስቲያን ለምንባል ለእኛ የሐዲስ ኪዳን የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ይህ አዲስ ውል የተደረገልን ለነፍሳችን ድኅነት በመሆኑ በስሟ እየተማጸንን እንዲሁም መታሰቢያዋን እያደረግን ለተራቡት ማብላት፣ ለተጠሙት ማጠጣትና ችግረኛ መርዳት ይገባናል፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን!