ሰበካ ጉባኤው ለካህናት ደመወዝ ለመክፈል እንደተቸገረ አስታወቀ
ሠኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
ሠኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተደረገው ጉባኤ ላይ የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ለካህናት ደመወዝ ለመክፈል በመቸገሩ በቤተ ክርስቲያኑ ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ችግር እያጋጠመው መሆኑን ገለጠ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያንና የርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከግቢያቸው አጥር ውጭ ምንም ይዞታ የሌላቸው በመሆኑ እና ቀደም ሲል የነበረው 270.9 ሄክታር ይዞታ በመነጠቁ ምክንያት አልምተን የገቢ ምንጭ የምንፈልግበት ሁኔታ የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው ደብሩ ይዞታው ከተመለሰ የልማት ሥራ በመሥራት ከችግር መላቀቅ የሚቻል መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩንም ለሚመለከተው አካል ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ወንዳፍራሽ ኃይሉ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ቁጥር ከ150 የማይበልጡ በመሆናቸው ከምእመናኑ በሚገኘው አስተዋጽኦ የካህናቱን ደምወዝ መክፈል አልተቻለም፡፡ የቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ወዳጆች በሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንጂ ደብሩ ከከተማ ራቅ ያለ በመሆኑ ምንም የገቢ ምንጭ የለውም ብለዋል፡፡
ደብሩ በአሁኑ ሰዓት 51 አገልጋዮች አሉት፡፡ አገልጋዮቹ ቀን ከሌሊት በትጋት ቢያገለግሉም ሰበካ ጉባኤው ካለው ዐቅም አንጻር ደምወዝ ከከፈላቸው ሦስት ወር እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡ አገልጋዮቹም በችግር ምክንያት የቀን ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ ፀሐፊ የሆኑት መጋቤ ምሥጢር አባ ፍሬ ስብሐት አድማሱ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኑ ከተተከለ መቶ ሠላሳ ዐራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በዐፄ ምኒልክ ዘመን የመጻሐፍት፣ የቅኔና የድጓ መምህራን እንዲሁም ሦስት መቶ ሊቃውንት የነበሩት መሆኑን ጠቁመው፣ ዛሬ ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ፈራርሰዋል፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ፈልሰዋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሊቃውንት አብዛኛዎቹ ከእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት የተገኙ ናቸው ያሉት ጸሐፊው በአሁን ሰዓት ጉባኤዎቹ ታጥፈዋል፡፡ ይህ የሆነው ከገንዘብ ማጣት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገራችን ነግሠው የነበሩት ዐፄ ዳዊት በእንጦጦ ተራራ ላይ መናገሻ ከተማቸውንና ቤተ መንግሥታቸውን አድርገው ይኖሩ ነበር፡፡ ንጉሡ ከቋጥኝ ድንጊያ ዋሻ ፈልፍለው ቤተ መቅደስ አሠርተው ሲያስቀድሱ ነበር፡፡ በ1860 ዓ.ም መጨረሻ ዐፄ ምኒልክ እንጦጦ ከተማ ከቆረቆሩ በኋላ፣ የልዑል እግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማሳነጽ በነበራቸው ምኞት ከደብረ ሊባኖስ ገዳም አባቶችን አስመጥተውና ቦታውን አስባርከው የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽ መቻሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ በውስጡ የቋጥኝ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ፣ የነገሥታት ዘውድና አልባሳት፣ የወርቅ፣ የብር፣ የነሀስና የዕፅ ንዋያተ ቅድሳትንና ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ ደብሩ እነዚህን ቅርሶች ሙዝየም በማስገንባት ለጎብኚዎች ክፍት ያደረገ ሲሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደዚህ የተቀደሰ ቦታ በመምጣት፣ በመሳለምና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የበረከቱ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ደብሩን መርዳት ለምትፈልጉ የልማት ባንክ ቁጥርን ይጠቀሙ፡፡ 0173060913900