ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል መታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው
ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም በድምቀት ይመረቃል፡፡
ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
ለሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በጎሬ ከተማ ላይ የተሠራላቸው መታሰቢያ ሐውልት ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም በድምቀት እንደሚመረቅ መታሰቢያ ሐውልቱን በማስገንባት ላይ የሚገኘው ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የሐውልቱ ምርቃት ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና የጎሬ ሕዝብ በተገኙበትይመረቃል፡፡
ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጎንደር ጠቅላይ ግዛት በደብረ ታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ ልጫ መስቀለ ክርስቶስ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከቄስ ገብረ ክርስቶስና ከእናታቸው ወ/ሮ ትኩዬ በ1874 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ከፊደል ጀምሮ ጸዋትወ ዜማ፣ ዝማሬና መዋስዕት፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዝገበ ቅዳሴ ከነትርጓሜው፣ አቋቋምና ቅኔ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ከታላላቅ መምህራን ተምረዋል፡፡
ግንቦት 25 ቀን 1921 ዓ.ም ከዐራት አባቶች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ በማቅናት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ተብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ ከብፁዕነታቸው ጋር ጵጵስናን የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡
ከግብፅ እንደተመለሱም ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የምዕራብ ኢትዮጵያ /የጎሬና የወለጋ ጠቅላይ ግዛት/፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የትግራይና የሰሜን ኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጎንደርና የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተሹመው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን አገልግለዋል፡፡
በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ ከፈፀሙ አባቶች መካከል ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል አንዱ ናቸው፡፡ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ላይ በፋሺስት ኢጣሊያ ከተገደሉ ከዐራት ወራት በኋላ ጎሬ ላይ ፋሺስትን አውግዘው ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡