ርኅሩኁና የይቅርታ መልአክ

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ሰኔ ፲፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

የርኅራኄ መዝገብ፣ ትሑት፣ ታዛዥና ለዘለዓለም ፈጣሪውን አመስጋኝ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጌታ በሚያደርገው ቸርነት ላይ ለሰው አንድ ወገን የሚሆን መልአክ ነው፡፡ (ሄኖ.፮፥፭፣፲፪፥፭፣፲፥፲፪)

አምላካችን እግዚአብሔርን የሚፈሩትን እንደ አጥር ሆኖ የሚጠብቃቸው፣ የመልእክት አለቃቸው፣ ምሕረት ማድረግን የተሰጠው፣ የክብር አክሊልን የተቀዳጀ፣ በግርማው የተፈራ፣ የቅዱሳን ወዳጅ፣ የኃጥአን የምሕረት አማላጅ፣ በብርሃን መጎናጸፍያ የሚጎናጽፍ፣ ከክብሩ ብርሃን የተነሣ ምድርን በብርሃን የሚሞላት፣ የቅዱሳንን ጸሎት ከዕጣኑ ጢስ ጋር ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርግ፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ የመለከት ድምጽ የሚያሰማ፣ በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ በማዕረግ የከበረ፣ ድንቅ ተአምራትን የሚያደርግ ቅዱስ ሚካኤል በዚህ ቀን ያደረገውን ነገር እወቁ!

ኪልቂያ በምትባል አገር ሃይማኖቱ የጸና አስተራኒቆስ የሚባል ታላላቅ መኮንን ነበር፡፡ የሚስቱም ስም አፎምያ ይባላል፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የመላእክት አለቃ የሚሆን ቅዱስ ሚካኤልንም በፍጹም ልቡናቸው የሚወዱ በየወሩ በቅዱስ ሚካኤል ስም ለነዳያን የሚመጸውቱ፣ የበዓሉን መታሰቢያ የሚያደርጉ፣ ለተራበ የሚያበሉ፣ ለተጠማ የሚያጠጡ፣ በፍቅርና በመከባበር የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ።

ቅድስት አፎሚያ ባሏ አስተራኒቆስ በታመመ ጊዜ እንዲህ አለችው፤ ‹‹ሴት ባሏ በሞተ ጊዜ ቤተ ፈት፣ ጋለሞታ፣ ሴተኛ አዳሪ እንደምትሆንና የዕለት ምግቧንም ለማግኘት ልዩ ልዩ ፈተና እንደሚደርስባት አንተ ታውቃለህ። እናም አንተ በምትሞትበት ጊዜ ከኀዘኔ የሚያረጋጋኝ፣ እንደ አባት እንደ እናት የሚሆነኝ፣ የሚያጽናናኝ በመዓልትና በሌሊት ከሰይጣን ጠብ የሚያድነኝ የምማፀንበት የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ታሠራልኝ ዘንድ እጠይቅሃለሁ›› አለችው። አስተራኒቆስም የጠየቀችውን በወርቅና በብር አሠርቶ አስመጣላት።

ቅድስት አፎምያ ባሏ አስተራኒቆስ ካረፈ በኋላ ዘወትር በቅዱስ ሚካኤል ፊት እየሰገደች ‹‹ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ጠብቀኝ፤ አትለየኝ፤ ይቅር ይለኛና ይምረኝ ዘንድም ወደ እግዚአብሔር ጸልይልኝ›› በማለት ትለምነው ጀመረ። በጎ ሥራዋንም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረች ሄደች። ለነዳያንና ለችግረኞች ምጽዋት መስጠትንም የየዕለት ተግባሯ አደረገች። ‹‹ምጽዋት ከርኅራኄ የምትበልጥ ርኅራኄ፣ ሰው ፈጣሪውን የሚመስልባት፣ ለአምላክ የሚያበድሯት ብድር፣ ወደ አምላክ የሚነግዷት የታመንች ንግድ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖሯት አደራ፣ እግዚአብሔር የሚቀበላት ቁርባን ናትና›› እንዲል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ አንቀጽ ፲፮) ቅድስት አፎሚያ የሚበላውን የሚጠጣውን በከርሠ ነዳያን፣ የሚለበሰውን በዘባነ ነዳያን በእግዚአብሔር ዘንድ አደራዋን ማስቀመጥን አበዛች።

ከዚህ በኋላ የሰው ልጆችን ድኅነት የማይወድ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ በምቀኝነት ተነሣባት። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና›› እንዳለ የብርሃን መልአክ መስሎ ወደ እናታችን ቅድስት አፎምያ ቀረበ። (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፲፬) ቀርቦም “አፎምያ ሆይ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጸሎትሽ፣ በጎ ምግባርሽ ወደ ሰማይ ዐርጎ ከእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቀርቦአል፤ ፈጣሪሽም ከመላእክቶቹ ጋር በጣም ተደስቶአል። እኔንም ስለ በጎ ሥራሽ ባለ ዘመንሽ ሁሉ እጠብቅሽ ዘንድ ወደ አንቺ ላከኝ” አላት። ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ›› እንዳለ ቅድስት አፎምያ ‹‹አንተ ማን ነህ? ስምህስ ማን ይባላል?›› አለችው፤ (፩ኛ ዮሐ.፬፥፩) የሐሰት አባተ ዲብሎስም “እኔ የመላእክት ሁሉ አለቃ ሚካኤል ነኝ” በማለት መለሰላት። የቤተ ክርስቲያን ልጆች አስተዋላችሁን? ሐሰተኛውና ተንኮለኛው ዲያብሎስ ዛሬ ላይስ ማን ነኝ እያል እያታለለን ይሆን? ሲያሻው ባሕታዊ፣ አጥማቂ፣ “ነጻ አውጭ ጳጳስ”፣ መነኩሴ፣ መምህር በመምሰል፣ በእኛ ዘመን “እኔ ክርስቶስ ነኝ” እስከ ማለት ደርሶአልና መመርመርና በጸሎት መበርታት ያስፈልጋል።

ቅድስት አፎምያ “እኔ የመላእክት ሁሉ አለቃ ሚካኤል ነኝ” ሲላት ‹‹በቤቴ ውስጥ እንዳለው በዘንግህ ጫፍ ላይ ትእምርተ መስቀል ለምን የለበትም? ትሳለመውም ዘንድ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አመጣዋለሁ›› ብላ ወደ ቤት ስትገባ አንቆ ያዛት። ዲያብሎስ ምንም እንኳን ዓይኑን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጥጦ ሊይዛት ቢመጣም ‹‹ሚካኤል! ሚካኤል ብላ ስትጣራ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› እንዳለ (መዝ.፴፫፥፯) ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ ደርሶ አዳናት፤ ከዲያብሎስ እጅም አወጣት።

የቤተ ክርስቲያን ልጆች! ዛሬም በእኛ ዘመን “እኔ መልአክ ነኝ፤ ሰማዕት ነኝ፤ መነኩሴ ነኝ፤ ጳጳስ ነኝ…” ሲላችሁ የመነኮሳትንና የጳጳሳትን ግብር ንገሩት፤ “አንተ ለምን እንደ እነርሱ አልሆንክም” በሉት። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ›› እያለ በሐዋርያት እግር በአንብሮተ እድ ተሹሞ “የእኔ ይሹም ይግዛ” ሲላችሁ እንደ ቅድስት አፎምያ “አባ አስኬማከ ሠናይ ወቃልከሰ እኩይ ወኢሠናይ ውእቱ፤ አባ አስኬማህስ መልካም ነው፤ ቃልህ ግን መጥፎ ነው” እንበለው። (፩ኛ ጴጥሮስ ፩፥፳፫)

ቅድስት አፎሚያ ተጋድሎዋንም ጭርሳ በዚች ቀን በሰላም ዐረፈች። የእግዚአብሔር ምስክርም ሆነች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል ጸሎት፣ ምልጃና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!!!

ወብስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

ምንጭ፡- ድርሳነ ሚካኤል ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን