ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ የሚጠራውን ቡድን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አገደ
ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም.
በዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ
በጠቅላይ ቤተ ክህነት አካባቢ ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ የሰየመውን ቡድን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የእገዳ ደብዳቤ ጣለበት፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጉባኤው ዓላማና ፍላጎት ምን እንደሆነ እንደማይታወቅና እንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖደስ ካለመቋቋሙም በላይ እውቅና ሳያገኝና ሳይፈቀድለት በራሱ ተነሳሽነት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትም የማያውቀውና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊና የከፋ ሸካ ቤንች እና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፊርማ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቁጥር 486/836/2004 ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. በተጻፈው ደብዳቤ መታገዱ ተገልጿል፡፡
“ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” በማለት ስለ ተቋቋመው ቡድን ያነጋገርናቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አንዳንድ የመምሪያ ሓላፊዎች ቡድኑ በምን ምክንያት እንደተቋቋመና ለምንስ በኅቡዕ መንቀሳቀስ እንደፈለገ እንዳልተረዱ ጠቅሰው ጉዳዩን ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነት ሲባል በአንክሮ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረው በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ሆነው የዚህን ሕገ ወጥ ቡድን አባላት በሆኑ ግለሰቦች ላይ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች በቀጣይ እንደሚወስድም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ገልጸውልናል፡፡
ጉባኤውን እያደራጁ የሚገኙ ግለሰቦች አብዛኛዎቹ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ተቀባይነት እያጡ የመጡ ግለሰቦች እንደሆኑ የሚናገሩት የቤተ ክህነቱ ምንጮች ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህ ግለሰቦች ሊፈጥሩት ካሰቡት ከፍተኛ አደጋ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጋት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የዚህ የእገዳ ደብዳቤ ግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ለሃይማኖትና ሥነ ሥርዐት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት፣ እንዲሁም ለፌደራል ፖሊስ ኮምሽን እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ግልባጭ የተደረገ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡