ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – የመጨረሻ ክፍል
በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳን መላእክት በምስጋናቸው የተናገሩለትን ሰላም ያስተማረውና የተረጐመው ከድኅነት ጋር አያይዞ ነው። የመላእክቱን አዲስ ምስጋና በተረጐመበት አንቀጸ ብርሃን በተባለው የድርሰቱ ክፍልም፡- ‹‹ወዓዲ ርእዩኪ በውስተ በዓት ለኪ ለባሕቲትኪ ምስለ ሕፃንኪ ወይቤሉ ሰላም በዲበ ምድር ወሶበ ርእዩ እንዘ ይለብስ ሥጋ ዚአነ ዘነሥአ እምኔኪ ሰገዱ እንዘ ይብሉ ለእጓለ እመሕያው ሠምሮ፤ እንደ ገናም ከሕፃኑ ልጅሽ ጋር አንቺን ብቻሽን በበረት ውስጥ ባዩሽ ጊዜ ‹በምድር ላይ ሰላም [ኾነ]› አሉ፤ ከአንቺ የነሣውን የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ባዩት ጊዜም ‹የሰውን ልጅ ወደደው› እያሉ ሰገዱ፤›› ሲል ተናግሮአል (መጽሐፈ ምዕራፍ፣ አንቀጸ ብርሃን፣ ገጽ ፻፳፯)። በዚህ ድርሰቱም የመላእክቱን ምስጋና፣ የሰው ልጆችን ድኅነት እንድንረዳ ቅዱስ ያሬድ በጥልቀት አስተምሮናል።
ቅዱስ ያሬድ ስለ ሰላም ሲነግረን ስለ ድኅነት እየመሰከረ እንደ ኾነ እና ከልደተ ክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት እያስረዳን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን የቅዱሳንን ልቡና ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ሊቃውንትን በመጠየቅ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን ማገናዘብ እጅግ ጠቃሚ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎችን፡- ‹‹አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ኾናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤›› በማለት በክርስቶስ የተገኘውን ሰላም አስተምሯቸዋል (ኤፌ. ፪፥፲፫-፲፭)፡፡ በዚህም የሐዋርያው መልእክት ክርስቶስ የሰጠንም ድኅነት ሰላም እንደተባለ እናስተውላለን።
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐርበኛ ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስም፡- በማቴዎስ ወንጌል ፲፩፥፳፰ ላይ በሚገኘው ‹‹ወደ እኔ ኑ፤›› እና በሉቃስ ወንጌል ፲፥፳፪ ላይ በተጻፈው፡- ‹‹ዅሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል›› በሚሉት ጌታችን ባስተማራቸው የወንጌል ቃላት ላይ ተመሥርቶ ባቀረበው ትምህርት የድኅነትን ሰላምነት እንዲህ በማለት ያስረግጥልናል፤ ‹‹አስቀድሞ ሰው አልነበረምና በኋለኛው ዘመን ግን ሰውን ያድን ዘንድ ሰው ኾነ። በመጀመርያው ቃል ሥጋ አልነበረም፤ ከዘመናት በኋላ ሥጋ ኾነ እንጂ፡፡ ሐዋርያት እንደ ነገሩን ከእርሱ ጋር የነበረብንን ጠላትነት ያስታረቀልን፣ በእኛ ላይ ተቀምጠው የነበሩትን ትእዛዛት ያጠፋልን በዚህ ሥጋ ነው፡፡ ይህን በማድረጉም ሁለቱን አንድ አዲስ ሰው ያደርግ ዘንድ፣ ሰላምን ያሰፍን ዘንድ፣ ሁለቱንም አንድ አድርጎ ከአብ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፤›› (NPNF V2-04፣ ገጽ 300-301)።
ስለ ኾነም ቅዱስ ያሬድ በክርስቶስ ልደት የተቀበልነውን ሰላም እንድንከተል፣ በክርስቶስ ሥጋ መልበስ ያገኘነውን ድኅነት ገንዘብ እንድናደርግ በምስጋናው ዅሉ ይመክረናል፡፡ ዘማሪው በተጨማሪም ክርስቶስ ይህን ሰላም የሰጠን በደላችንን ይቅር ብሎ፣ … ከኃጢአት በስተቀር ሰው የሚኾነውን ኾኖ እንደ ኾነ በማስረገጥ፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ሰውን ለማዳን ያበቃው ይቅር ባይ ባሕርዩ እንደ ኾነ እንድናምን ያስረዳናል። በሌላኛው የምስጋና ድርሰቱም ‹‹ብርሃን መጽአ ኀቤነ ከመ ያርኢ ምሕረቶ በላዕሌነ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ … ርእዩ ዘከመ አፍቀረነ እግዚአብሔር፤ በእኛ ላይ ምሕረቱን ያሳይ ዘንድ ብርሃን ወደ እኛ መጣ፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምንኛ እንደ ወደደን ተመልከቱ፤›› በማለት ሊቁ ዘምሯል (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡ ይህም እግዚአብሔር ሰዎችን እንዲያድን ያደረገው ለሰው ልጆች ያለው ልዩ ፍቅር እንደ ኾነ የሚያስገነዝበን ድንቅ ትምህርት ነው። በሊቁ ትምህርት መሠረት የሰው ልጆችን ለድኅነት ካበቁት የእግዚአብሔር ባሕርያት መካከል ይቅር ባይነት እና ፍቅር ዋና ዋነኛዎቹ እንደ ኾኑ ለመረዳት እንችላለን፡፡
በአጠቃላይ የሰዎችን ሥጋ ተዋሕዶ ሰዎችን እንዲያድን የፈቀደ ራሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው። ይህ ደግሞ አምነን የምንቀበለውና በተወደደው የድኅነት መንገድ ለመጓዝ መንገዳችንን የሚያቀናልን እንጂ መርምረን የምንደርስበት ምሥጢር አይደለም። ይልቁንም እኛ ድነን ለዘመናት አጥተናት ወደ ነበረችው ገነት እንድንመለስ እና በራሳችን ስሕተት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥል ግድግዳ ፈርሶ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንኖር የእግዚአብሔር ሰው መኾን (ሥጋዌ) እጅግ አስፈላጊ እንደ ነበረ፣ እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ሰውን እንዲያድን ካገበሩት ባሕርያቱ መካከልም ይቅር ባይነቱ (መሐሪነቱ) እና ፍቅሩ መኾናቸውን እያሰብን ከቅዱስ ያሬድ ጋር ‹‹አናኅስዮ አበሳነ አፍቂሮ ኪያነ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ፤ በደላችንን ይቅር ብሎ እኛን ወዶ አዳኝ ልጁን ወደኛ ሰደደልን፤›› እያልን በማመስገን የመድኃኒታችንን በዐለ ልደት በደስታ እናከብራለን።
በዐሉን ስናከብርም እንደ መላእክቱ እና እንደ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አዲስ ምስጋናን ለእግዚአብሔር በመቀኘት እንጂ ከእግዚአብሔር በሚለዩን በዓለም ዳንኪራዎች እንዳይኾን ራሳችንን መግዛት ይኖርበታል፡፡ ሥጋችንን ተዋሕዶ ለድኅነት የተገለጠልንን መድኃኒታችንን እያሰብን ድኅነታችንን ገንዘብ በምናደርግበት በታላቁ በዓላችን ወቅት ዘመን በወለዳቸው ኃጢአቶች ድኅነታችንን እንዳናጣ ከመጠንቀቅ ጋርም በዓሉን የበረከት በዓል ልናደርገው እንደሚገባን አንርሳ፡፡ አምላካችን ከጥልቅ ፍቅሩ የተነሣ ለድኅነታችን የተገለጠውን መድኅን የምንዘክርበትን በዓላችንን ዓለም ዅሉ ወደ ድኅነት የሚቀርብበት በዓል ያድርግልን፡፡
በማይጠቀለል ሦስትነት፣ በማይከፋፈል አንድነት ጸንቶ የኖረ እና የሚኖር፤ አስቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረውን ሥጋ በመዋሐድ ለሰው ልጆች ያለውን የማይለካና በቃላት ሊገለጥ የማይችል ፍቅር ያሳየ፤ በእያንዳንዷ ቅጽበት ከቸርነቱ ብዛት፣ ከጸጋው ምልአት የተነሣ ፍጥረታትን የሚመግብ፤ ልሳናት ዅሉ የሚያመሰግኑት፤ ጕለበቶች ዅሉ የሚንበረከኩለት ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው! ተወልዶ እንዲያድነን አንድያ ልጁን ለላከልን ለእግዚአብሔር አብ፤ ከአባቱ ዕቅፍ ሳይለይ ሥጋችን ተዋሕዶ ላዳነን ለእግዚአብሔር ወልድ፤ በዅሉም የሚኖር፣ ዅሉንም ለሚያከናውን ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር፣ ምስጋና ይዅን፤ አሜን፡፡
ማስገንዘቢያ፡-
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ይህ ትምህርት ከታኅሣሥ ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በወጣው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዓውደ ሃይማኖት ዓምድ ሥር ‹‹አዳኝ ልጁን ወደ እኛ ሰደደልን›› በሚል ርእስ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡