‹‹ሥዕሏ ሥጋን የለበሰች ትመስል ከሠሌዳዋም ቅባት ይንጠፈጠፈ ነበር››
መስከረም ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ሕዝበ ክርስቲያን ከሚያከብሩት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፴፫ቱ በዓላት አንዱ ጼዴንያ ማርያም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመስከረም ፲ ቀን ይከበራል፡፡ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ቡራዮ አካባቢ ጼዴንያ ማርያም በምትባል ቤተ ክርስቲያን በዕለቱ ታቦተ ክብሩ ከመንበሩ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ጼዴንያ በምትባል ሀገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገልጧልና፤ ይህችን ድንቅ ሥዕልም ቅዱስ ሉቃስ እንደሣላት ይነገራል።
በዚህች የተባረከች ቀን የሚከበረው የእመቤታችን የጼዴንያ ማርያም ሥዕል ታሪክም ይዘከራል፡፡ ጼዴንያ በምትባል ሀገር ስሟ ማርታ የተባለችው ሴት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ወዳጅ የነበረችና ቅዱስ ሉቃስ የሳለውንም ሥዕሏም አባ ቴዎድሮስ የተባለ ኢትዮጵያዊ ከእየሩሳሌም ገዝቶ እንደሰጣት ይነገራል፡፡ እርሱም መነኮስ እንደነበርና ወደ ኢየሩሳሌም በሚጓዝበት ጊዜ በእርሷ ቤት እንዲያርፍ ስለፈደችለት ውለታዋን ይከፍል ዘንድ ሥዕሏን የሰጣት ነው፡፡ ሆኖም ግን በመጀመሪያ አባ ቴዎድሮስ ሥዕሏን መግዛት በመርሳቱ የማያውቀው አንድ አስደንጋጭ ድምጽ ሥዕሉን እንዲገዛ አስታውሷት ሊገዛት ችሏል፡፡ ከገዛትም በኋላም ወደ ማርታ ወስዶ እንዳይሰጣት ብዙ ችግሮች እንደገጠሙትና በሥዕሏም የተነሣ እንዳለፋቸው በታሪኩ ላይ እናነባለን፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር) ይህም ሥዕሏ በእርሱ እጅ ሳለች በሚያስፈራ ጫካ በሚጓዝበት ጊዜ ሽፍቶችን ተመልክቶ ሲፈራ ሥዕሏ ድምጽ አውጥታ ‹‹አትፍራ›› በማለት ያለ ምንም ጉዳት ስታሳልፈው ዳግመኛም አንበሳ ሊበላው በነበረበት ጊዜ ሥዕሏ በሚያስፈራ ድምጽ ከእርሱ አርቃለታለች፡፡ ስለዚህም አባ ቄዎድሮስ ሥዕሏን ለማርታ መስጠን ስላልወደደ ይዟት ለመጥፋት ቢጥርም የእግዚአብሔር ፈቃድ አልሆነምና በተደጋጋሚ ሙካረው ስለከሸፈበት ለራሱ ሊያደረጋት አልቻለም ነበር፤ ሥዕሏንም ለማርታ ሊሰጣት ተገዷል፡፡
እርሷም በእጅጉ ተደንቃ ተቀብላ ከቤተ ጸሎቷ አስገብታ አኑራታለች፤ እርሱ የሸፈነባትንም መሸፈኛ ብትገልጠው ግሩም መዓዛ ያለው ዘይት ከሥዕሊቱ ሲፈስ አግኝተዋል። መነኰስ አባ ቄዎድሮስም ሥዕሏን እስከ ዕለተ ሞቱ ሲያገለግል እንደኖረ ገድሉ ይመሠካራል፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩት የሀገሩ ኤጲስ ቆጶሳት ነገሩን ሰምተው ከካህናትና ከሕዝቡ ጋራ መጥተው በሚመለከቱ ጊዜ ሥዕሏ ሥጋን የለበሰች ትመስል ነበር፤ ከፊቷም ወዝ ሲወጣ ይታይ ነበር፤ ለበረከትም ከሥዕሏ ከሚወጣው ዘይት ወስደዋል፤ በሌላም ጊዜ ሥዕሏን ወደሌላ ቦታ ሊወስዱ በፈለጉ ጊዜ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነው ትተዋታል፤ እስከዛሬም በዚያው አለች።
ከሥዕሏ የሚወጣውንም ዘይት ብዙዎች እየተቀቡ ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር፡፡ ማርታም የነሐስ መስኮት የሐር መጋረጃ የሚበሩ መቅረዞች ሠርታ በክብር አስቀምጣታለች፤ ሥዕሏም እስከዛሬም ትገኛለች፤ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጋለች::
ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ያሳትፈን፤አሜን፡፡