ሥርዓተ አምልኮ

ክፍል ሁለት

ታኅሣሥ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሥርዓተ ጾም

ጾም

ጾም ‹‹ጾመ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን የቃሉ ፍቺም ‹‹መተው፣ መከልከል፣ መጠበቅ›› ማለት ነው፡፡ ጾም ለተወሠነ ጊዜና ሰዓት ሥጋችን ከሚፈልጋቸው መብል፣ መጠጥ እንዲሁም ማንኛውም ሥጋዊ ፍላጎት መከልከልና መወሰን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስትምህሮ ‹‹ጾም በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል›› እንደሆነ እንማራለን፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፥፲፭)

በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ጾም ለአምላካችን እግዚአብሔር ፍቅር ስንል ሥጋችንን ለርኃብና ለጥማት አሳለፈን በመስጠትና በመትጋት የምንኖረው በመሆኑ የአምልኮት መገለጫ ነው፡፡ ጠላት ዲያብሎስ ከሚያመጣብን ፈተናም ለማለፍ ይረዳናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ››  በማለት እንደተናገረው ለአምላካችን እግዚአብሔር መገዛታችንን አምልኮታችንን ከምንገልጽባቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት መካከል አንዱ ጾም ነው፡፡ (መዝ.፪፥፲፩)

በመጽሐፈ ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕራፍ ፮ ላይም እንደተለገጸው ‹‹ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ወገን የምታሠጥ፣ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፣ ለጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው፣ የንጽሕህና መገለጫ፣ የጸሎት ምክንያት እናት፣ የዕንባ መገኛ መፍለቂያዋ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡››

በክርስቶትስ ክርስቲያን የተባልን ሰዎች በሙሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታወጁትን ሰባቱን አጸዋማትን ማለትም ‹‹ጾመ ነቢያትን፣ የነነዌ ጾምን፣ ዐቢይ ጾምን፣ ጾመ ድኅነትን (ረቡዕና ዓርብ)፣  ጾመ ሐዋርያትን፣ የገሃድ ጾምን  እና ጾመ ፍልሰታ ለማርያምን›› ጠንቅቆ በማወቅ ወቅቶቹንና ሥርዓቱን ጠብቀን ልንጾም ይገባል፡፡

የጾም ሥርዓት

በአጽዋማት ወቅት ልንጠብቃቸው የሚገባን ሥርዓቶች የክርስቲያናዊ ምግባራችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይህም የጸሎት ሰዓታትን ጠብቆ ከመጸለይ በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን በመገኘት ጸሎት ማድረስ፣ ቅዳሴ ማስቀደስና ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህን ተግባራት በሌሎች ወቅቶችም ልንተገብራቸው ቢገባም በጾም ወቅት ግን ጾማችን በእግዚአብሔር አንድ ይታሰብልንና ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ከጾማችን ጋር እነዚህን ተግባራት ልንፈጽማቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአጽዋማት ወቅት ከጾሎታችን ጋር አብዝተን መስገድና መመጽወት ይገባናል፡፡

በጸሎትና በስግደት እንዲሁም በምጽዋት የታገዘ ጾም በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ በመሆኑ ድኅነትን ማሰጠት ብቻም ሳይሆን በረከትን ያስገኛል፡፡ በዚህም የተነሣ ሥራችን፣ ትዳራችን እንዲሁም አገልግሎታችን ይባረክልናል፡፡

ሥርዓተ ምጽዋት

ምጽዋት ሥርወ ቃሉ የግእዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ስጦታ፣ችሮታ፣መለገስ›› ማለት ነው፡፡

ለተቸገሩ ሰዎች የምናደርገው ማንኛውም የገንዝብም ሆነ ቁሳዊ ርዳትን መመጽወት ይባላል፡፡ ይህም በተለይ የሚበሉትና የሚለብሱት ላጡ ነዳያን የሚደረግ ችሮታን ያመለክታል፡፡  በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ ፻፳፭-፻፳፯ እንደተገለጸው ‹‹ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ፣ ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል፣ በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡››

ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል›› በማለት እንደተናገረው ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ለእግዚአብሔር መስጠት ነው፡፡ (ምሳ.፲፱፥፲፯)

ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ ተናግሯል፡፡ ‹‹እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?›› እንዲል፤ (ኢሳ.፶፯፥፯)

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሲያስተምርም ‹‹ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ›› ብሏል:: (ሉቃ.፫፥፲፩)

ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን በእግዚአብሔር ፊት ምጽዋትን እናደርግ ዘንድ በዕለት ከዕለት ከምናገኘው መብልና መጠጥ እንዲሁም አልበሳት ግምሹን ማካፈል ይጠበቅብናል፡፡ ሁለት እንጀራ ካለን አንዱን ለሌለው መስጠት እንዲሁም ትርፍ ልብስ ካለን በተመሳሳይ መልኩ ልብስ ለሌለው ማልበስ እንዳለብን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ምግባራችን አምላካችን ደስ ይሰኛልና ለእርሱ ምጽዋትን እያቀረብን በአምልኮተ እግዚአብሔር እስከ ሕልፈተ ሕይወታችን ኖረን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡

ሥርዓተ ስግደት

ስግደት ማለት ‹‹ማጎንበስ፣ መንበርከክ፣ በግንባር መውደቅ፣ ግንባርን ምድርን አስንክቶ መሬት ስሞ መመለስ›› ማለት ነው።

ስግደት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ እነርሱም የአምልኮት ስግደትና የጸጋ ስግደት (ለእመቤታቸን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰገድ ስግደት እንዲሁም ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታተ የሚሰገድ ስግደት ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ርእሰ ጉዳያችን ላይ የምናየውና ከሥርዓተ አምልኮ ጋር የምንማረው ስለ የአምልኮተ ስግደተ ነው፡፡

የአምልኮት ስግደት

ለአምላካችን እግዚአብሔር የሚሰገድ ስግደት የአምልኮት ስግደተ ነው፡፡  በሉቃስ ወንጌል  ‹‹ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ›› ተብሎ እንደተጻፈው በአርአያውና በአምሳሉ ለፈጠረን ፈጣሪያችን ስግደት እናቀርባናለን፡፡ (ሉቃ.፬፥፰)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ‹‹ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደት እሰግዳለው›› እያልን ለአምላካችን እንድሰግድ ታስተምረናለች፡፡ ሰዎች ሰማያውያን መላእክትን ምሳሌ በማድረግ በፍርሃትና አክብሮት ለአምላካችን እንሰግዳለን፡፡

የአምላኮተ ስግደት ሥርዓት

ለልዑል እግዚአብሔር የሚሰገድ ስግደት በንጹሑ ስፍራና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሥዕሉ ፊት የሚደረግ ነው፡፡ በምንሰግድበት ጊዜም ኅሊናችን ከክፋት ሁሉ ነጻ አድረገን በንጹሕ ልቡናና በፍርሃት ሆነን ግንባራችንን መሬት በማስነካት ልንሰግድ ይገባል፡፡

በምንሰግድበት ጊዜም ‹‹ለአብ እሰግዳለሁ፣ ለወልድ እሰግዳለሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ፣ ለአብ ምስጋና ይሁን፤ ለወልድ ምስጋና ይሁን፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን፤  በረከት ለሰጠኸን፣ እስኪዘህ ሰዓት ላደረስከን፣ በቸርነትህ ላኖርከን፣ በብርሀንህ ኃይል ለመራኸን ላንተ ክብር ምስጋና ይግባል፡፡ ሃሌሉያ ለአብ፣ ሃሌሉያ ለወልድ፣ ሃሌሉያ ለመንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው የማይሞት›› እያልን እንሰግዳለን::

ይቆየን!