ሥርዓተ ንባብ
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
…ካለፈው የቀጠለ
ውድ አንባብያን በአለፈው ትምህርታችን ከምንባቡ ላይ ተነሽ ንባባትን እንድትጽፉ መልመጃ መስጠታችን ይታወቃል። እንደሠራችሁትም ተስፋ እናደርጋለን። ለማረጋገጥ ያህል ምንባቡንና መልሱን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር ኀበ አሐቲ ሀገር ዘገሊላ እንተ ስማ ናዝሬት ኀበ ድንግል እንተ ተፍኅረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ ዘእምቤተ ዳዊት ወስማ ለይእቲ ድንግል ማርያም። ቦአ መልአክ ኀቤሃ ወይቤላ ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ ቡርክት አንቲ እምአንስት ወርእያ ደንገጸት እምቃሉ ወኀለየት ወትቤ እፎኑ ከመዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ። ወይቤላ መልአክ ኢትፍርሂ ማርያም እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምይዮ ስሞ ኢየሱስ። ዐቢይ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል። ወይሁቦ እግዚአብሔር አምላክ መንበረ ዳዊት አቡሁ። ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ። ትቤሎ ማርያም ለመልአክ እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ እፎኑ ይከውነኒ። አውሥአ መልአክ ወይቤላ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኀይለ ልዑል ይጼልለኪ። ዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል። ወናሁ ኤልሳቤጥኒ እንተ እምአዝማድኪ ይእቲኒ ፀንሰት ወረከበት ወልደ በልኅቃቲሃ ወበርስዓቲሃ። ወናሁ ሳድስ ዝንቱ ወርኅ ለእንተ ይብልዋ መካን እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር። ትቤሎ ማርያም ለመልአክ ነየ አመቱ ለእግዚአ ኵሉ ነየ አመቱ ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ።
በግእዝ የሚነገር ተነሽ……..ተፈነወ፣ ቦአ፣ ሞገሰ፣ ወልደ፣ አውሥአ፣ ነየ በካዕብ የሚነገር ተነሽ……..ይትአምኁ፣ ውእቱ በሣልስ የሚነገር ተነሽ……..ለይእቲ፣ ተፈሥሒ ምስሌኪ፣ አንቲ፣ ኢትፍርሂ፣ ረከብኪ፣ ትፀንሲ፣ ወትወልዲ፣ ይከውነኒ፣ ላዕሌኪ፣ ይጼልለኪ፣ እምኔኪ፣ እምአዝማድኪ በራብዕ የሚነገር ተነሽ… ይብልዋ በሳብእ የሚነገር ተነሽ… ወትሰምይዮ
ውድ አንባብያን የመልመጃውን መልስ በዚህ መልኩ እንደሠራችሁት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቀጥሎ ተጣይንና ሰያፍን እንመለከታለን።
ተጣይ፡– ተጣይ ማለት በአነባበብ ሥርዓቱ ጣል ተደርጎ የሚነበብ ማለት ነው። ከመጨረሻው ፊደል ቀድሞ የሚገኘውን ፊደል ያዝ አድርጎ ይጣልና ይነበባል። ተጣይ በሳድስ ፊደል ብቻ ይጨርሳል። መምህር ዘርዐ ዳዊት መርኆ ሰዋስው ዘልሳነ ግእዝ በሚባል መጽሐፋቸው(ገጽ.፴፪) “ተጣይና ሰያፍ ንባብ ሁለቱም በሳድስ ፊደል ይደርሳሉ። ነገር ግን ተጣይ ንባብ የመድረሻውን ተከታይ ፊደል ያዝ በማድረግ ይነበባል” በማለት ያስረዳሉ። ስለዚህ በአነባበብ ሥርዓቱ ጣል አድርገን የምናነበውና በሳድስ ፊደል የሚጨርስ ንባብ ተጣይ ንባብ ይባላል።
ምሳሌ፡- ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል
ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ።
ወናሁ ሳድስ ዝንቱ ወርኅ ለእንተ ይብልዋ መካን
ትቤሎ ማርያም ለመልአክ
ወትሰምይዮ ስሞ ኢየሱስ
ሰያፍ፡– ማለት በአነባበብ ሥርዓቱ በሰያፍ የሚነበብ ማለት ነው። ይህ ማለት ቀና ተደርጎ ወይም ተነሥቶ የሚነበብ እንደማለት ነው። ከመጨረሻው ፊደል ቀድሞ ከሚገኘው ጀምሮ በማንሣት ይነበባል። እንደተጣይ ሁሉ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል (ይነገራል)።
ምሳሌ፡- ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ
እንተ ተፍኅረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ
ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል
ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም
ይእቲኒ ፀንሰት ወረከበት ወልደ
የበለጠ ግልጽ እንዲሆን የሚከተለውን ሰንጠረዥ በትኩረት ይመልከቱ ።
ተ.ቁ | ተጣይ | ሰያፍ |
፩ | ሕይወት | የሐውር |
፪ | ማርያም | ማርቆስ |
፫ | ሚካኤል | ገብርኤል |
፬ | ማዕበል | ማቴዎስ |
፭ | ምሁራን | ይገብር |
፮ | ሕዝብ | ይነውም |
፯ | መጽሐፍ | ይጽሕፍ |
መልመጃ
ውድ አንባብያን ከላይ ያቀረብነው ማብራሪያ ግልጽ ሆኖላችሁ ከሆነ የሚከተለውን ምንባብ በማንበብ ተጣይና ሰያፍ ንባባትን አውጡ።
አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ ትምጻእ መንግሥትከ። ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ ሀበነ ዮም። ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ። ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት። አላ አድኅነነ ወባልሐነ እምኵሉ እኩይ እስመ ዚኣከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም።
ተጣይ…….
ሰያፍ…….